ርሃብ የጠናባት ሶማሊያ | አፍሪቃ | DW | 21.09.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ርሃብ የጠናባት ሶማሊያ

ሶማሊያ ዉስጥ አምስት ሚሊየን የሚሆን ሕዝብ በቂ ምግብ በማጣት ለረሃብ መጋለጡን አንድ የቅኝት ዉጤት አመለከተ። ናይሮቢ እና መቅዲሹ ላይ ትናንት የተመድ፣ የምግብ ዋስትናና የተመጣጠነ ምግብ ትንተና ዘርፍ እና ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ይፋ ባደረጉት መሠረት ከ40 በመቶ የሚበልጠዉ የሶማሊያ ዜጋ የሚበላዉ አጥቷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:41

ርሃብ በሶማሊያ

ምንም እንኳን የምግብ እጥረቱ በቂ ዝናብ ባለመገኘቱ ቢሳበብም፤ ሀገር ዉስጥ የሚፈናቀሉት መብዛትና በአፍሪቃ ቀንዷ ሀገር የሚንቀሳቀሰዉ አሸባሪ ቡድን አሸባብ የሚፈጽማቸዉ ድርጊቶች ችግሩን ካባባሱት ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

ትናንት በኬንያዋ ዋና ከተማ ናይሮቢ ይፋ የተደረገዉ የተመድ የምግብ ዋስትና እና የተመጣጠነ ምግብ ትንተና ዘርፍ እንዲሁም የከፋ ርሃብ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስልት ሠንሠለት የቅኝት ዉጤት ከአንድ ሚሊየን የሚበልጡ ሶማሊያዉያን በከፋ የምግብ ዋስትና ቀዉስ ዉስጥ እንደሚገኙ አመልክቷል። በተጨማሪም አምስት ሚሊየን የሚሆኑት የዚችዉ ሀገር ዜጎች የምግብ ዋስትና እንደሌላቸዉም ዘርዝሯል። ሶማሊያ ዉስጥ የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ተጠሪ ሪቻርድ ትሬንቻርድ በበኩላቸዉ ሁኔታዉ ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ ቀስ በቀስ እየተባባሰ እና እየከፋ መሄዱን አስረድተዋል።

«አሁን አስከፊ ሁኔታ ነዉ፤ እናም የዛሬ ስድስት ወር ከነበረዉ 20 በመቶ ተባብሷል። የተመጣጠነ ምግብ እጥረትም እንዲሁ ቅኝት በተካሄደባቸዉ አካባቢዎች የከፋ ሆኗል፤ ቀላሉ የሆነዉ እዉነታም ዛሬ ሶማሊያ ዉስጥ የአየር ጠባይ መለዋወጥ፤ ግጭት እና መፈናቀል ያስከተሉት ጫና ሕዝቡ ወደነበረበት የቀድሞ አኗኗሩ ለመመለስ ከሚያደርገዉ ጥረት እጅግ መብለጡን ያሳያል።»

ሶማሊያ ዉስጥ በሚሠሩበት ወቅት ድርቅ እና የከፋዉ ረሃብ ያደረሱትን ተፅዕኖ እራሳቸዉ በዓይናቸዉ የተመለከቱ መሆናቸዉን የሚናገሩት ትሬንቻርድ አፋጣኝ ርምጃ እንዲወሰድም ጥሪ አቅርበዋል።

«በዉኃ እጦት የደረቀዉን መልክዓ ምድር፣ የሞቱ የቤት እንስሳትን እንዲሁም በየመኖሪያዉ እንዳልነበረ የሆነዉን ንብረት ስትመለከቱ፤ በጣም ያስገርማል። በእርግጥም እነዚህን በተደጋጋሚ የደረሰ አስደንጋጭ ክስተቶች ማንም ቢሆን መቋቋም መቻሉ ተዓምር ነዉ።»

ትናንት ይፋ በተደረገዉ ዘገባ ካለፈዉ ዓመት የካቲት ወር ጀምሮ አስተማማኝ ምግብ ማግኘት የማይችሉት የሶማሊያ ዜጎች ቄጥር በ300 ሺህ መጨመሩንም ጠቅሷል። ከ300 ሺህ የሚበልጡ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትም ለአስከፊ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መዳረጋቸዉንም ገልጿል። እንደዘገባዉ በቂ ምግብ እንዳጡ ከተነገረላቸዉ የዞማሊያ ዜጎች ከግማሽ የሚበልጡት ከመኖሪያ ቤትና መንደራቸዉ በተደጋጋሚ የተፈናቀሉ ናቸዉ። የከፋ ርሃብ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስልት ሠንሰለት የተሰኘዉ ድርጅት ባልደረባ አብዲረዛክ ኑር የምግብ ርዳታ ለሚያስፈልጋቸዉ የሶማሊያ ዜጎች ዓለም አቀፍ ለጋሾች እጃቸዉን በመዘርጋት ያንዣበበዉን የከፋ ችግር በመለወጡ እንዲራዱ ጥሪ አቅርበዋል።

«ዝናብ ዘግይቶ ጀምሮ፤ ያበቃዉም አስቀድሞ ነዉ። በዚያም ላይ መጠኑ ከአማካኙ እጅግ ያነሰ ነዉ። አስቸኳይ የምግብ ርዳታ ከሚያስፈልጋቸዉ በከፋ የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ከሚሰቃዩት ከ50 ሺዎቹ በተጨማሪ 300ሺህ የሚሆኑ ሕፃናት ለባሰ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንደሚዳረጉ እንገምታለን። በዚያም ላይ በቅኝታችን እጅግ በከፋ መልኩ ለባሰ የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ለተጋለጡ ለአቅመ ሔዋን የደረሱ ሴቶች አፋጣኝ አቅርቦት እንደሚያስፈልግ ተረድተናል። አፋጣኝ ሰብዓዊ ርዳታ ያስፈልጋቸዋል።»

የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት በእንግሊዝኛ ምሕጻሩ FAO ከምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ማለትም IGAD ያገኘዉን የአየር ጠባይ ትንበያ መሠረት በማድረግ ይፋ እንዳደረገዉ፤ አሁን በሶማሊያ የሚታየዉ ድርቅ ገና በሌላ የዝናብ እጥረት ይጠናከራል። ሪቻርድ ትሬንቻርድ ይህ በሶማሊያ የሚታየዉን የከፋ ርሃብ ወደጠኔ እንዳያሻግረዉ ስጋት አላቸዉ።

«ወደፊት የሚመጣዉን እልቂት ከወዲሁ ለማስቀረት በዕድል ላይ መተማመን አንችልም። በሶማሊያ የምግብ ዋስት እና የተመጣጠነ ምግብ ይዞታ በመጪዎቹ ወራት እንደሚባባስ ነዉ ከወዲሁ ተገምቷል። ሚሊየን እና አምስት ሚሊየን የሚሆን ሕይወት ዳግም አደጋ ላይ ይወድቃል፤ ይህ ደግሞ ጥሩ አይደለም።»

ሶማሊያ ዉስጥ ባለዉ ግጭት ጦርነት ምክንያት ተሰደዉ ኬንያ በሚገኘዉ የስደተኞች መጠለያ የቆዩትም፤ የኬንያ መንግሥት የዳዳብን መጠለያ ለመዝጋት በመወሰኑ ወደ ሀገራቸዉ መመለስ በመጀመራቸዉ የምግብ ርዳታ ፈላጊዎችን ቁጥር እንዳይጨምር ስጋት አለ። በዳዳብ ከ329 ሺህ የሚበልጡ ሶማሊያዉያን ተጠልለዉበት ቆይተዋል። አብዲረዛክ ኑር ግብረ ሰናይ ተቋማት የሶማሊያን ዜጎች ወደ ሀገራቸዉ የመመለሱ ርምጃ የምግብ ዋስትን ይበልጥ በማሳጣት በመቶ ሺዎች የሚገመቱት ለጠኔ እንዲዳረጉ ያደርጋል የሚል ማስጠንቀቂያ ማስተላለፋቸዉን ይናገራሉ።

«አስቸኳይ ሰብዓዊ ርዳታ ከሚያስፈልጋቸዉ መካከል 1,1 ሚሊየን ገደማ የሚሆኑት እዚያዉ በሀገር ዉስጥ ከመኖሪያቸዉ የተፈናቀሉ ናቸዉ፤ የዳዳብ የማይቀር መዘጋት ማለት ደግሞ ይህን ቁጥር ከፍ ያደርጋል፤ እናም የስደተኞቹ ፍሰትም ሁኔታዉን ሊያባብሰዉ ይችላል።»

ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እንደሚሉት ምንም እንኳን የሶማሊያ ዜጎች የአሸባብ ታጣቂዎች በሚያደርሱት ጥቃት ከየመኖሪያ ቀያቸዉ ቢፈናቀሉም፤ የሶማሊያ መንግሥት ሕዝቡን መመገብ እና ከገጠመዉ አስደንጋጭ ችግር እና ቀዉስ ለማዉጣት የሚያስችል የእርሻ ስልት መቀየስ ይኖርበታል።

ሸዋዬ ለገሠ/ አንድሪዉ ዋሲኪ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic