ራሄል እና ሰለሞን እንደቀልድ የጀመሩት በጎ አድራጎት | ወጣቶች | DW | 01.09.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ወጣቶች

ራሄል እና ሰለሞን እንደቀልድ የጀመሩት በጎ አድራጎት

ኢትዮጵያ ውስጥ ወቅቱ ክረምት ነው ፤ በተለይ አዲስ አበባ ውስጥ ይዘንባል፣ ይበርዳልም። የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት እንግዶቻችን ክረምቱን ከግምት አስገብተው ጎዳና የሚያድሩ ልጆችን አቅማቸው እስከፈቀደ ድረስ በመርዳት ላይ ያሉ ናቸው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:26
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:26 ደቂቃ

በጎ አድራጊዎች

ጓደኛሞቹ ራሄል ገብረ- እግዚያብሄር እና ሰለሞን መንገሻ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ናቸው። በተለይ የክረምት ወቅት እንዴት እንደሚቀዘቅዝ ያውቃሉ። ታድያ አንድ ቀን አንድ ካፌ ተቀምጠው ሻይ ቡና ሲሉ፤ አንድ ሀሳብ መጣላቸው። እንዴት ብለው ጎዳና ላይ ዝናብ የሚመታቸውን የጎዳና ተዳዳሪዎች መርዳት እንደሚችሉ። ይህንም ሀሳብ ወዲያው መተግበር ጀመሩ። ያገኙትም ድጋፍ በአይነት እና በክብደቱ የተለያየ ነበር። 
በጎ አድራጊዎቹ በፌስ ቡክ አማካኝነት ልብስ ብቻ ሳይሆን፤ የጎዳና ተዳዳሪዎቹ ዝናብ የሚከላከሉበት ዉሐ የማያስገባ ላስቲክም አሰባስበዋል።ከዛም የአልባሳት መረጣ እና ማከፋፈል ጀመሩ። ራሄል ጋዜጠኛ ናት። ሰለሞን በግል ስራ ይተዳደራል። ሁለቱም ወጣቶች ርዳታውን በማስተባበራቸው ደስተኛ ናቸው። ምክንያቱም ይላሉ፤ ይህንን ስራ መስራት በጀመሩበት ወቅት የታዘቡት ነገር ፤ ሰዎች ምን ያህል ለመርዳት ፍቃደኛ እንደሆኑ ነው።

 Addis, Straßenkinder Hilfe (S.Mengesha)

ለጎዳና ተዳዳሪዎች የተሰበሰቡ ልብሶች


ጎዳና የሚተዳደሩ ሰዎችን የሚረዱት ወጣቶች የማህበረሰቡን  አመኔታ ጠብቀው የሚያቆዩት ደግሞ ኃላፊነቱን ለሁሉም በመስጠት ነው። « በተቻለን መጠን ከሌሎች ድጋፍ ሰጪዎች ጋር ሆነን ነው የተሰበሰበውን ልብስ የምናከፋፍለው» ይላል ሰለሞን።
ወጣቶቹ ጎዳና አዳሪዎችን በአልባሳት፣ በዝናብ መጠለያ እና በደብተር ከመርዳት አልፈው፤ ዘንድሮ ለሶስት የጎዳና ተዳዳሪዎች ቤት ተከራይተዋል። ሶስቱ የጎዳና ተዳዳሪ የነበሩት ተማሪዎች አንድ ላይ መኖር ከጀመሩ አሁን ሁለት ሳምንት ሆናቸው።

 Addis, Straßenkinder Hilfe (S.Mengesha)

የዝናብ መጠለያ ላስቲኮች

ወደ 9ኛ ክፍል ያለፈው ኤርሚያስ  አንዱ ነው። «አሁን የተሻለ ውጤት እንደማመጣ ተስፋ አለኝ ይላል» ኤርሚያስ ለትምህርት ልዩ ፍቅር እንዳለው ይናገራል። የ18 ዓመቱ ወጣት ወደ ጎዳና የወጣው ገና በ9 ዓመቱ ነበር። የኤርሚያስ እናት በህይወት የሉም። ከክፍለ ሀገር የተለያዩ ከተሞችን አቋርጦ አዲስ አበባ የደረሰው ኤርሚያስ በጓዳና ህይወቱ ብዙ ችግሮችን አሳልፏል።
በራሄል እና ሰለሞን አማካኝነት ቢያንስ ሶስት የጎዳና ተዳዳሪዎች አሁን መጠለያ አግኝተዋል። ይሁንና ልጆቹ ከቤት እና ቁሳቁስ ርዳታ ባሻገር ሞራላዊ ድጋፍም ምን ያህል እንደሚያስፈልጋቸው ሰለሞን ገልጾልናል።
ተማሪዎቹ ያለ ስጋት ትምህርታቸውን ተምረው እንዲጨርሱ ግን ሰለሞን እና ራሄል የጀመሩት እቅድ ዘላቂነት ሊኖረው ይገባል። ይህንንስ እንዴት ነው ተግባራዊ ለማድረግ ያሰቡት? ራሄል ለልጆቹ ኃላፊነት ወስዶ ትምህርታቸውን እስኪያጠናቅቁ ድረስ የሚረዳቸው ሰው ቢገኝ የተሻለው አማራጭ እንደሆነ ትናገራለች።
እንደ ተቋም ሳይደራጁ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ፌስ ቡክን ብቻ ተጠቅመው ምን ያህል የጎዳና ተዳሪዎችን አስተባብረው መርዳት የቻሉት ሰለሞን እና ራሄል ከዶይቸ ቬለ ጋር ያደረጉትን ቆይታ ድምጹን ተጭነው ማድመጥ ይችላሉ። 


ልደት አበበ 
ነጋሽ መሀመድ
 

Audios and videos on the topic