ሩስያ፥ ተጠርጣሪዉ የኔምትሶቭ ገዳይ ወንጀለኛ ተባለ | አውሮጳ እና ጀርመን | DW | 08.03.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ እና ጀርመን

ሩስያ፥ ተጠርጣሪዉ የኔምትሶቭ ገዳይ ወንጀለኛ ተባለ

የክሬምሊን ቤተ-መንግሥት ተቺ ቦሪስ ኔምትሶቭን ሩስያ መዲና ሞስኮው ክሬምሊን ቤተመንግሥት አጠገብ በጥይት ገድለዋል ተብለው በጥርጣሬ ከተያዙት ኹለት ሰዎች መካከል አንደኛው ግድያውን መፈፀሙን አምኗል መባሉ ተዘገበ። ኹለቱ በግድያ ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ከሌሎች ሦስት ተጠርጣሪዎች ጋር ሞስኮው በሚገኝ አንድ ፍርድ ቤት መቅረባቸው ተጠቅሷል።

በጥይት ሞስኮ ጎዳና ላይ የተገደሉት የክሪምሊኑ ቤተ-መንግሥት የሰላ ትችት አቅራቢ ሩስያዊው ቦሪስ ኔምትሶቭ ተጠርጣሪ ገዳይ የፈፀመዉን ወንጀል ማመኑ ተዘገበ ። የሩስያ ብዙኃን መገናኛዎች የሞስኮዋን ዳኛ ናታልያ ሙሽኒኮቫን ዋቢ በማድረግ ነዉ ይህን ዘገባቸዉን ይፋ ያደረጉት። ቀደም ሲል ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ታዋቂዉን የሩስያ ፖለቲከኛ ገድለዋል በሚል ከቺችንያ የመጡ ሁለት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር መዋላቸዉን ይፋ አድርጎ ነበር። ተጠርጣሪዎቹ በርካታ ሙስሊሞች ከሚኖሩበት የሩስያ ግዛት ከሰሜናዊ ካቭካዝ የመጡ ናቸዉ። እንደ ሩስያ ባለስልጣን መሥርያ ቤት በኔምሶቭ ግድያ እስላማዊ ፅንፈኛ እጅ ሳይኖርበት አልቀረም። ምክንያቱም እንደ ባለስልጣን መስርያ ቤቱ የሩስያ መንግሥት ተቃዋሚ ፖለቲከኛዉ ቦሪስ ኔምትሶቭ ከዝያ አካባቢ አንድ የዛቻ ደብዳቤ ደርሷቸዉ ነበር። የ55 ዓመቱ የሩስያ ታዋቂ ፖለቲከኛ የካቲት 20 ክሪምሊ ቤተ-መንግሥት አጠገብ ጎዳና ላይ ካልታወቀ ሰዉ በተተኮሰ ጥይት መገደላቸዉ ይታወቃል።

ቦሪስ ኔምትሶቭን ገድለዋል በሚል ከተያዙት ተጠርጣሪዎች አንደኛው

ቦሪስ ኔምትሶቭን ገድለዋል በሚል ከተያዙት ተጠርጣሪዎች አንደኛው

የሩስያ መንግሥትን በመተቸት የሚታወቁት ሩስያዊው ፖለቲከኛ ቦሪስ ኔምትሶቭን ገድለዋል በሚል የተጠረጠሩ ሰዎች ማሰሩን የሩስያ ፖሊስt ይፋ ያደረገው ትናንት ነበር። የሩስያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንን በግልፅ አጥብቆ በመተቸት የሚታወቁት የ55 ዓመቱ የተቃውሞ ፖለቲከኛ ከአንድ ሣምንት ግድም በፊት ክሬምሊን ግንብ አቅራቢያ የተገደሉት ከጀርባቸው በጥይት ተደብድበው ነው። የሩስያ ባለሥልጣናት ከግድያው ጀርባ የፖለቲካ እጅ እንዳለበት ተናግረዋል። ግድያውን ብሔርተኞች አለያም ፅንፈኞች ሳያቀነባብሩት እንዳልቀሩም ባለሥልጣናቱ አስታውቀዋል። የመንግሥት ተቺዎች እንደሚሉት ከሆነ ግን ከግድያው ጀርባ እጁ ያለበት ራሱ የሩስያ መንግስት ነው። ግድያው በሩስያም ሆነ በመላው ዓለም በበርካቶች ዘንድ ድንጋጤን ፈጥሯል። የቀድሞ የሩስያ ምክትል ጠቅላይ ሚንሥትር የነበሩት የ55 ዓመቱ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ኔምትሶቭ፤ ሩስያ በዩክሬይን የሚገኙ ተገንጣዮችን ትረዳለች በሚል ከፍተኛ ነቀፌታ ያሰሙ ነበር። የሩስያ መንግሥት በግድያው ተጠርጣሪ የሆኑ ሰዎችን ማንነት ለጠቆመ 43 ሺህ ዩሮ ገደማ ወሮታ ለመክፈል መድቦ እንደነበረም ተገልጧል።

መንገድ ላይ በጥይት ለተገደሉት ቦሪስ ኔምትሶቭ የመታሰቢያ ጉንጉን ሞስኮ ከተማ ውስጥ

መንገድ ላይ በጥይት ለተገደሉት ቦሪስ ኔምትሶቭ የመታሰቢያ ጉንጉን ሞስኮ ከተማ ውስጥ

አምስቱ የግድያ ተጠርጣሪዎች ዛሬ ሞስኮ በሚገኘው ፍርድ ቤት ቀርበዋል። የሩስያ ፖሊስ ከግድያው ጀርባ ፅንፈኛ ሙስሊሞች ቡድን እጅ አለበት ብሏል። ፖሊስ ለእዚህ ምክንያቴ ብሎ ያቀረበው ደግሞ መንግሥትን በጥብቅ ይተቹ የነበሩት ተቃዋሚው ፖለቲከኛ ቦሪስ ኔምትሶቭ ከቡድኑ ተደጋጋሚ ዛቻ ይደርስባቸው የነበረ መሆኑን ነው። የሩስያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ተቺዎች ግን ይህን የፖሊስ መላ ምት ውድቅ አድርገውታል። እንደውም እንደተቺዎቹ አባባል ይኽ ሁሉ «አሻጥር ነው፤ ከግድያው ጀርባ የሩስያ መንግሥት እጅ አለበት» ብለዋል። ለእዚህ እንደማጠናከሪያ ያቀረቡት ምክንያት ደግሞ በግድያ ወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ከቀረቡት ሰዎች መካከል ሦስቱ ቺቺንያ ውስጥ ከደህንነት ሰዎች ጋር ግንኙነት ነበራቸው መባሉን ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

ተዛማጅ ዘገባዎች