ሩሲያና ያንሠራራው የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖቷ፣ | ዓለም | DW | 11.12.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ሩሲያና ያንሠራራው የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖቷ፣

የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ አሌክሴይ ዳግማዊ፣ ሞስኮ በሚገኘው መድኀኔ-ዓለም ቤተ-ክርስቲያን፣ ፍትሓት ከተደረገላቸው በኋላ ፣ በኢጲፋንያ ካቴድራል የቀብራቸው ሥነ-ሥርዓት ተከናውኗል።

default

ለሟቹ ፓትሪያርክ አሌክሴይ ዳግማዊ፣ የመጨረሻ የስንብት ሥነ-ሥርዓት፣

ከትናንት በሰቲያ ሞስኮ ውስጥ ለፓትሪያርክ አሌክሴይ ዳግማዊ፣ በተካሄደው ጸሎተ-ፍትኀት፣ ከአገሪቱ መሪዎች፣ ከፕሬዚዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭና ጠ/ሚንስትር ቭላዲሚር ፑቲን ሌላ፣ እንዲሁም በሩሲያው የጥቀምት አብዮት የተገደሉት የዛር (ንጉሥ) ዳግማዊ ኒኮላስ የቅርብ ዘመድ ልዕልት ማሪያ ቭላዲሚሮቭና ሌላ፣ ከውጭ ሀገር መሪዎች ፣ የሰርቢያ፣ የአርመንና የቤላሩስ፣ ፕሬዚዳንቶች፣ ቦሪስ ታዲች፣ ሴርዝ ሳርግስያንና አሌክሳንደር ሉካሼንኮ፣ ተገኝተው ነበር። ከሃይማኖት መሪዎችም፣ በቀድሞዋ ቆስጥንጥንያ፣ በአሁኗ ኢስታንቡል የሚገኙት የኦርቶዶክሳውያን አብያተ- ክርስቲያን የአንድነት ፓትሪያርክ፣ በርጦሎሜዎስ ቀዳማዊ፣ የጂዎርጂያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን መሪ፣ ኢልያ ዳግማዊ፣ ከዓለም ዙሪያ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን ተጠሪዎች፣ እንዲሁም፣ ከሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የአብያተ ክርስቲያን የአንድነት ጉዳይ ምክር ቤት ኀላፊ ካርዲናል ቫልተር ካስፐር፣ የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ተወካይ፣ የለንደን ጳጳስ ሪቸርድ ቻርተርስና የኢራን እስላማዊ የባህልና የመገናኛ ድርጅት ኀላፊ፣ አያቶላህ ሙሐመድ አሊ ታስኪሪ ተግኝተዋል።

በ 6 ወራት ውስጥ፣ አዲስ ርእሰ-ሊቃነ-ጳጳሳት መምረጥ ቢቻልም፣ ከጥር 19-21,2001 ዓ ም፣ ለ 3 ቀናት በሚካሄደው አጠቃላይ የሲኖዶስ ጉባዔ፣ አዲስ ፓትሪያርክ የሚመረጥ መሆኑን ነው ፣ ዐቃቤ-ፓትሪያርክ፣ ሊቀ-ጳጳስ ኪሪል ያስታወቁት።

ባለፈው ሳምንት ዓርብ ፣ በ 79 ዓመታቸው ያረፉት ፓትሪያርክ፣ አሌክሳይ ዳግማዊ፣ ከ 4 ዓመት በፊት 75 ኛ ዓመት የልደት በዓላቸው ሲከበር ፣ ለኅብረተሰቡ ዐቢይ ድርሻ ማበረከታቸው ተመሥክሮላቸው፤ ከያኔው ፕሬዚዳንት፣ ካሁኑ ጠቅላይ ሚንስትር ቭላዲሚር ፑቲን ፣ ለአናት ሀገር ሩሲያ አግልግሎት የሚሰጠውን ከፍተኛ ሽልማት - ሜዳሊያ መቀበላቸው ይታወሳል። ሽልማቱን ሲቀበሉም እንዲህ ብለው ነበር።

«ይህን ዐቢይ ሽልማት፣ ለራሴ ብቻ ሳይሆን፣ ለሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን የአግልግሎት ዋጋ አድርጌ ነው የምቀበለው። ቤተ ክርስቲያኒቱ በአንድ ሺ ዓመት ታሪኳ፣ በደስታም፣ በኀዘንም ፣ ዘወትር ከህዝቡ ጎን ከመቆም የቦዘነችበት ጊዜ የለም። እንዲህ ነው የቆየው ምግባርዋ፣ ወደፊትም በዚሁ መቀጠል ይኖርበታል።»

በሩሲያ ኅብረተሰብ ውስጥ ሰፊ ተቀባይነት ያላት የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን 72 ዓመታት በኮሚኒስቶች ብርቱ ጭቆና ደርሶባት ብትንገላትም፣ የሶቭየት ኅብረት ኮሙዩኒስታዊ አገዛዝ ከተወገደ ወዲህ በ 18 ዓመታት ገደማ ውስጥ እጅግ አንሠራርታ፣ የአብያተ-ክርስቲያኑ ቁጥር ተበራክቶ፣ 30,000 መድረሱ፣ ገዳማቱም ከ 18 ወደ 700 ከፍ ማለታቸው ታውቋል። የቤተ ክርቲያኒቱ አባላት ቁጥርም፣ በሩሲያ ፌደሬሽን ብቻ፣ ከ 70-80 ሚልዮን እንደሚደርስ ነው የሚነገረው። ቤተ ክርቲያኒቱ፣ ለመንፍሳዊ ልጆቿ፣ መንፍሳዊ አግልግሎት ብቻ ሳይሆን ፣ በትምህርት፣ በጤና አጠባበቅና ፣ በማኅበራዊ ኑሮ ሰፊ ግልጋሎት ትሰጣለች።

የሶቭየት አገዛዝ ካከተመ ወዲህ፣ በሩሲያ ፌደሬሽን ውስጥ፣ በመንግሥትና በቤተ ክርስቲያን መካከል ያለው ግንኙነት ያማረ-የሠመረ መሆኑ ይነገራል።

የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ሲኖዶስ ፤ እ ጎ አ ከ 1589 ዓ ም ወዲህ ፣16ኛውን ፓትሪያርክ ፣ማለትም ሟቹን ፓትሪያርክ አሌክሴይ ዳግማዊን፣ እንዲተኩ የሚመርጣቸውን አዲስ ፓትሪያርክ በዓለ- ሲመት ጥር 24 ቀን 2001 ዓ ም፣ ያከብራል።