ረጅም ልብ ወለድን ፍለጋ | ባህል | DW | 13.02.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

ረጅም ልብ ወለድን ፍለጋ

አዳም ረታ፤በውቀቱ ስዩም ፤እንዳለጌታ ከበደ፤ስንቅነህ እሸቱ ፤አለማየሁ ገላጋይ ፤ግርማ ተስፋው ፤ እንዬ ሺበሺ ባለፉት አስር አመታት ረጅም ልብ ወለድ ለህትመት ካበቁ የኢትዮጵያ ደራስያን መካከል ይገኙበታል።

በየመንገዱ፤ምግብ ቤቶች እና መጠጥ ቤቶች መጻሕፍት በደረት እና ጀርባቸው ተሸክመው የሚያዞሩ ወጣቶች፤የመንገድ ላይ መጻሕፍት ነጋዴዎች፤አነስተኛ መጻህፍት አከፋፋዮች ባለፉት አሥር አመታት አዲስ አበባ እና በፌደራል መስተዳድሮች ርእሰ-ከተሞች ተበራክተዋል። የመጻሕፍት ምረቃ እና ውይይቶች እዚህም እዛም ይደረጋሉ። የህይወት ታሪኮች፤ማስታዎሻዎች፤የጦርነት ተጋድሎዎችን የሚተርኩ መጻህፍት ደግሞ ይበልጥ ተቀባይነት አግኝተዋል።

በዚህ መካከል የሚነሳው አንድ ክርክር በኢትዮጵያ የማንበብ ባህል ከምን ደርሷል የሚለው ይሆናል። አቶ አይናለም መዋ የመጻሕፍት አሳታሚ እና አከፋፋይ ናቸው።«ሰዎች በታክሲ ወይም በአውቶቡስ ሲሄዱ ያንቀላፋሉ እንጂ እጃቸው ላይ ጋዜጣ፤መጽሔት ወይም መጽሐፍ ሲይዙ አይታይም።» የሚሉት አቶ አይናለም «በአሁኑ ወቅት አንድ መጽሐፍ የሚታተመው ከሶስት ሺ እስከ አምስት ሺ ቅጂ ነው።» በማለት 90 ሚሊዮን ይደርሳል ከሚባለው ህዝብ አኳያ በቂ አለመሆኑን ያስረዳሉ።ከእነዚህ መካከል የይድረስ ይደረስ የተሰሩ በወሲባዊ እና ብልጽግና ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ መጻሕፍት በጀማሪያ አንባብያን ዘንድ ተመራጭ መሆናቸውን ይናገራሉ።

እንዳለጌታ ከበደ የረጅም ልቦለድ ደራሲ፤የጋዜጣ እና መጽሄት አምደኛ ናቸው። በኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ውስጥም ተሳትፎ አላቸው። በእርሳቸው ግምገማ የንባብ ባህል አድጓል የሚለው ሃሳብ ጉንጭ አልፋ ክርክር ነው። «ሰላሳ አመት በፊት በ1970ዎቹ ውስጥ የሚወስደው ጊዜ እና ጉልበት እና ከታተመ በኋላ አንባብያን ዘንድ ያለው ተቀባይነት አሁን ካለው አንጻር ሲታይ ድካሙ የበረታ ነው።» ይላሉ። እንደ አቶ እንዳለጌታ ከበደ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ከሰላሳ አመታት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በከፍተኛ ደረጃ በማደጉ የሚታተሙ የመጻሕፍት ቅጂ ብዛት አብሮ ማደግ ነበረበት። የኃይለመለኮት መዋዕል ‘የወዲያነሽ’እና በዛ ዘመን የታተሙ እንደ ሰመመን፤ወንጀለኛው ዳኛ እና የእልም ዣትን የመሳሰሉ መጻሕፍት ከሰባ እስከ ሰማኒያ ሺህ ቅጂዎች መሸጣቸውን የሚያስታውሱት አቶ እንዳለጌታ ከበደ አሁን አስር ሺ ቅጂ ከፍተኛው ቁጥር ለመሆን መብቃቱ ያስቆጫቸዋል።

«ወታደሩ አንባቢ ነበር።አሁንስ ለሰራዊቱ መጽሐፍ ይቀርብለታል ወይ?» የሚል ጥያቄ የሚያነሱት ደራሲው የመጽሐፍት አሳታሚ እና አከፋፋይ ድርጅቶች አለመኖርንም እንደ ተጨማሪ ችግር ያነሳሉ።

ደራሲ እና ሃያሲው አለማየሁ ገላጋይ ግን «የማንበብ ባህል አሁን ጥሩ ነው።» በማለት ለየት ያለ ሃሳብ ይሰነዝራሉ።«በየቦታው እየተዟዟሩ መጽሐፍ የሚሸጡ ልጆች ሁለት መቶ እና ሶስት መቶ ሳይሆኑ አይቀሩም። እነዚህ ሁሉ ህይወታቸውን መጽሐፍ ላይ መሰረት አድርገው እየኖሩ አይደል እንዴ።» አቶ አለማየሁ ገላጋይ ደራሲዎችም በአዲስ አበባ ብቻ መወሰናቸውን በኢትዮጵያ ግን ከሁለት መቶ አምሳ በላይ ከተሞች መኖራቸውን ይናገራሉ። እናም ደራሲዎች በየከተሞች በመዘዋወር ስራዎቻቸውን ማስተዋወቅ እና መወያየት እንደሚገባቸው ይከራከራሉ።

አቶ አለማየሁ አጥቢያ፤ቅበላ እና የብርሃን ፈለጎች የተሰኙ ሶስት ረጃጅም ልብ ወለዶችን ለህትመት አብቅተዋል። አለማየሁ በጋዜጣ እና መጽሔት በሚጽፏቸው በውይይት መድረኮች በሚያቀርቧቸው ሂሶች ይታወቃሉ። ከዚህም ባሻገር ሰላሳ ያህል ፀሐፊያን፣ ገጣሚያንና ሰዓሊያን ስለ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ያላቸውን የተለያየ አመለካከት አጣምረው መልክዓ ስብሃት በተሰኘ መድበል አቅርበዋል። ይህ ስራቸው ለሥነ-ፅሑፋዊ ሆነ ለማህበራዊ ሂስ በር ከፋች ተብሎለታል።

ባለፉት አስር ዓመታት በአማርኛ ስነ-ጽሁፍ በርከት ያሉ ስራዎችን ለህትመት ካበቁ ደራሲዎች መካከል አዳም ረታ ይጠቀሳል። አዳም ከ1997 ጀምሮ ግራጫ ቃጭሎች፤አለንጋናምስር፤እቴሜቴ ሎሚ ሽታ፤ከሰማይ የወረደ ፍርፍር፤ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ፤ሕማማትና በገና እና መረቅ የተሰኙ ስራዎችን አበርክቷል። በ1997 ዓ.ም. ለህትመት የበቃውና በሥነ-ጽሑፍ ባለሙያዎች ብሉይ (Classic) ነው የተባለለት ግራጫ ቃጭሎች በአንባቢያን ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ሶስት አመታት ወስዶበታል። የኢትዮጵያ መጻህፍት ገበያን በቅርበት የሚያውቁት አቶ አይናለም መዋ አሁን አሁን ለህትመት የሚበቁ ረጅም ልብ ወለድ ስራዎች ገበያውን መቆጣጠር እንደተሳናቸው ይናገራሉ።

ለመሆኑ የዚህ ትውልድ ረጅም ልብ ወለድ ጸሐፍት እነማን ናቸው? ትውልድ የሚለውን ጉዳይ ትንሽ እናጥብበውና ባለፉት አስር አመታት አንድ ሁለት ተብለው የሚቆጠሩ ስራዎች ለህትመት ያበቁ ደራሲዎች እነ ማን ናቸው?የዛሬ ጸሐፍት ካለፈው ትውልድ ጸሐፊያን የሚጋሩት እና የሚለዩበት በምንድነው? ልንጠቅሰው የምንችለው ጥናታዊ ጽሁፍ አላገኘንም።

የአዳም ረታ -ግራጫ ቃጭሎች፤ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ እና መረቅ፤ የበውቀቱ ስዩም- እንቅልፍ እና እድሜ እና መውጣት እና መግባት፤ የእንዳለጌታ ከበደ -ደርሶ መልስ እና ዛጎል፤ ኦታም ፑልቶ በሚል የብዕር ስም የሚታወቀው የስንቅነህ እሸቱ -የሲሳይ ልጆች እና የኦዞ ኮሌጅ፤ የአለማየሁ ገላጋይ -አጥቢያ፤ቅበላ እና የብርሃን ፈለጎች፤የግርማ ተስፋው -ሰልፍ ሜዳ፤ የእንዬ ሺበሺ -የገቦ ፍሬ ባለፉት አስር አመታት ለአንባቢያን ከደረሱ ረጅም ልብ-ወለዶች ይጠቀሳሉ።

አቶ አለማየሁ ገላጋይ እነዚህ መጻሕፍት በቋንቋቸው፤የገጸ-ባህርያት አሳሳላቸው፤በሚያነሱት ጭብጥ እና አለምን የሚተረጉሙበት መንገድ የተለያየ መሆኑን ያስረዳሉ።

እሸቴ በቀለ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic