ረሐብ የተጫናቸው የትግራይ ሕፃናት በአይደር ሆስፒታል | ኢትዮጵያ | DW | 23.09.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ረሐብ የተጫናቸው የትግራይ ሕፃናት በአይደር ሆስፒታል

ሰውነቱ የሳሳ፣ አይኑ የጎደጎደና የቆዳ መገርጣት የሚታይበትን የአራት አመት ልጅ ጨምሮ ረሐብ ለጤና ዕክል የዳረጋቸው ሕፃናት በአይደር ሆስፒታል ይገኛሉ። ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ስድስት ዕድሜያቸው ከ5 አመት በታች የሆኑ ሕፃናት በረሐብ ምክንያት መሞታቸውን የሚገልጽ መረጃ የዶይቼ ቬለ ዘጋቢ መቐለ ከተማ ከሚገኘው አይደር ሆስፒታል አግኝቷል

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:23

ረሐብ የተጫናቸው የትግራይ ሕፃናት በአይደር ሆስፒታል

ግርማነሽ መለስ በትግራይ ክልል ከሚገኘው ከእንድርታ ወረዳ በረሐብ ክፉኛ የተጎዳ የአንድ አመት ከስድስት ወር ሕፃን ይዛ ወደ አይደር ሆስፒታል ያቀናችው ለልጇ ምግብ ከተገኘ በሚል ተስፋ ነበር። "አይደለም ሕፃን ልጅ እኛም ብንሆን የነበረን ስለተዘረፈ ካገኘን እንበላለን ከሌለ ጦማችንን ነው የምናድረው" ስትል ለመቀሌው ወኪላችን ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ የተናገረችው ግርማነሽ ግን በሆስፒታሉ ብቻዋን አይደለችም። 

ሰውነቱ የሳሳው፣ አይኑ የጎደጎደው እና የቆዳ መገርጣት የሚታይበት የአራት ዓመቱ ክብሮም ፈቃዱ በዚያው በአይደር ሆስፒታል ይገኛል። አባቱ አቶ ፍቃዱ ገብረእግዚዓብሔር በጦርነቱ ምክንያት ከእጅ ወደ አፍ የነበረ ኑሯቸውን መሙላት ተስኗቸው ለርዳታ ጠባቂነት መጋለጣቸውን ተናግረዋል። 

"በየቤቱ የምግብ እጥረት አለ። ሕፃናት ሊመገቡት የሚችሉ ወተት ይሁን አምባሻ ወይም ሌላ ነገር የለም። እንደ አባት የቀን ሥራም ቢሆን ሠርተን ገንዘብ አግኝተን ቤተሰብ እንዳንመራ ሥራ የለም። እጃችንን እና እግራችንን አጣጥፈን ቁጭ ብለን ነው ያለንው" ሲሉ አቶ ፍቃዱ ያሉበትን ሁኔታ አስረድተዋል።

ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ስድስት ዕድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ ሕፃናት በረሐብ ምክንያት መሞታቸውን የሚገልጽ መረጃ ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ መቐለ ከተማ ከሚገኘው አይደር ሆስፒታል ማግኘቱን ዘግቧል። በአይደር ሆስፒታል መረጃ መሠረት በተመሳሳይ ጊዜ 111 ዕድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ በረሐብ የተጎዱ ሕፃናት ለሕክምና ወደ ሆስፒታሉ አቅንተዋል። በትግራይ ሽረ፣ ቆላ ተምቤን፣ ኦፍላ፣ ሓውዜን እና ሌሎች አካባቢዎች በረሀብ ምክንያት ሞት መከሰቱ የክልሉ አስተዳደር ዐስታውቋል። 

ሚሊዮን ኃይለ ስላሴ  
እሸቴ በቀለ 
ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች