ረሃብ የሚፈታተነው የአፍሪቃ ግብርና | አፍሪቃ | DW | 20.01.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ረሃብ የሚፈታተነው የአፍሪቃ ግብርና

በጎርጎሮሳዊው 2030 ማለትም የዛሬ 15 ዓመት በዓለማችን አንድም ረኃብተኛ እንዳይኖር እቅድ ተይዟል። ይህን ለማሳካት ደግሞ የዓለማችን የምግብ ምርት አሁን ካለው መጠን በእጥፍ መጨመር ይኖርበታል። በዚህ በኩል ከአፍሪቃ ብዙ ጥረት ይጠበቃል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:50
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:50 ደቂቃ

ረሃብ የሚፈታተነው የአፍሪቃ ግብርና

የዶቼ ቬለዋ ዛቢነ ኪንካርትስ እንደዘገበችው ግን ይህ እቅድ በጣም የተለጠጠ ምኞት ነው። በአሁኑ ጊዜ ከዓለማችን ህዝብ ወደ 800 ሚሊዮን የሚጠጋው ረኃብተኛ ነው። በአፍሪቃም ከአምስቱ ሰዎች አንዱ ይራባል። የህዝብ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ፣ ረኃብ ፣የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ፣የጤና ችግሮች፣ የምርታማነት መቀነስና ድህነት የሚደጋገሙ ክስተቶች ናቸው። ግራ አጋቢው ነገር ደግሞ ለረኃብ የሚጋለጠው፣ እህል የሚመረትበት የገጠሩ አካባቢ መሆኑ ነው። 60 ሚሊዮን እንደሚሆን ከሚገመተው የአፍሪቃ የእርሻ ይዞታ ከሚገኘው ምርት ሶስት አራተኛው ለአራሹ ፍጆታ ብቻ የሚውል ነው። ለምሳሌ ከዓለማችን ድኃ ሃገራት አንዷ በሆነችው በዛምቢያ ገበሬው መሬቱን የሚያርስው በዶማ ነው። 15 ሚሊዮን ከሚገመተው የዛምቢያ ህዝብ 80 በመቶው በአነስተኛ እርሻ ነው የሚተዳደረው። ገበሬው ሥራውን የሚያከናውነውም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ነው። የዛምቢያ ችግር ከሰሃራ በስተደቡብ ከሚገኙ ሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት ጋር የሚመሳሰል መሆኑን የሃገሪቱ የግብርና ሚኒስትር ጊቭን ሉቢንዳ «አረንጓዴው ሳምንት» በተሰኘው በርሊን ውስጥ በተካሄደ የግብርና ዓዉደ ርዕይ ላይ ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ በዛምቢያ የመሬት ችግር አለመኖሩን ጠቁመው፣ ባለኃብቶች በሃገሪቱ እርሻ ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን ቢያፈሱ ዛምቢያውያንን ብቻ ሳይሆን የአካባቢውን ሃገራትም ሊጠቅሙ እንደሚችሉ አሳስበዋል ።
«ከዛምቢያ 75 ሚሊዮን ሄክታር መሬት 58 በመቶው ለእርሻ የሚሆን ለም መሬት ነው። 15 ሚሊዮን ህዝብ ብቻ ባላት ዛምብያ፣ ለእያንዳንዱ ዜጋ 5 ሄክታር መሬት ሊደርስ ይችላል። ባለኃብቶች በዛምቢያ የሚያመርቱት ሰብል ለ15 ሚሊዮን ዛምብያውያን ብቻ አይደለም። ይልቁንም በዛምቢያ ዙሪያ ለሚኖረው 400 ሚሊዮን ህዝብ እንጂ ።»
ሚኒስትሩ እንደሚሉት ዛምቢያ ከሌሎች የተፈጥሮ ኃብቶችዋ ተጠቃሚ መሆን ባለመቻልዋ ራስዋን በድላለች። የተፈጥሮ ኃብትን በአግባቡ አለመጠቀምና የኃብት ብክነት በዘርፉ የሚታዩ ዋነኛ ችግሮች ናቸው። በዚህ ረገድ ጥቅም ላይ ሳይውል የሚባክነው የሃገሪቱ የውሃ ኃብት ተጠቃሽ ነው። የዛምቢያ የውኃ ኃብት መጠን በአጠቃላይ በደቡባዊ አፍሪቃ ሃገራት ከሚገኘው የውኃ ሀብት 40 በመቶ ገደማ ይሆናል። ይህን የተፈጥሮ ኃብት ለመስኖና ለአሳ ምርት ማዋል ይቻል ነበር። ይሁንና 100 ቢሊዮን ሊትር የሚገመት ውኃ ጥቅም ላይ ሳይውል በየዓመቱ ወደ ህንድ ውቅያኖስ ይፈሳል። ላለፉት በርካታ አሥርት

ዓመታት የአፍሪቃን ግብርና ማሻሻል በሚቻልበት መንገድ ላይ ውይይቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል። በክፍለ ዓለሙ አረንጓዴ አብዮት ማካሄድ እንደሚገባ ሁሉም ይስማማል። ጥያቄው ግን ይህ እንዴት ሊሳካ ይችላል የሚለው ነው። በየዓመቱ በሚካሄደው የአረንጓዴው ሳምንት ዓዉደ ርዕይም ሆነ በግብርና ሚኒስትሮች ጉባኤ አለያም በዓለም የእርሻ ድርጅት ስብሰባዎች ላይ ክርክር የሚካሄድበት አንድ ነጥበ አለ። የአፍሪቃን ግብርና የሚያሳድገው በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ አነስተኛ ገበሬዎች የሚደረግ እገዛ ወይስ ትላልቅ የውጭ የእርሻ ድርጅቶችን ማስገባት የሚለው ቀድሞም ሆነ አሁን የሚያከራክር ጉዳይ ነው። የጀርመን የግብርና ሚኒስትር ክርስቲያን ሽሚት ይህ እንደ የሃገሩ ሁኔታ ሊለያይ እንደሚችል ያስረዳሉ። ሆኖም በርሳቸው አስተያየት በመስኩ የግል ባለሃብቶች ካልተሰማሩ በስተቀር ለችግሩ መፍትሄ ሊገኝ አይችልም። ሆኖም አተገባበሩ ላይ ጥንቃቄዎች ሊደረጉ እንደሚገባ ግን ሳያሳስቡ አላለፉም ።
« የሚሸጠው መሬት ገበያ የሚያስገኘው ብቻ እንጂ ኤኮኖሚያዊ ጥቅሙ እየታየ አይደለም። በዚህም ምክንያት በአቅርቦቱ ረገድ ዘላቂ የሆነ ትስስር እንዲፈጠር የሃገሪቱን የመሬት ይዞታ በአዲስ መልክ የሚያዋቅር ፖለቲካዊ ዓላማ ሊኖረን ይገባል ።
የጀርመን ዓለም ዓቀፍ የልማት ተራድዖ መስሪያ ቤት በድረ-ገፁ እንዳሰፈረው ከዛሬ 15 ዓመት ወዲህ በዓለማችን ለውጭ ባለኃብቶች ከተሸጠው 56 ሚሊዮን ሄክታር መሬት 70 በመቶው የሚገኘው በአፍሪቃ ነው። ይሁንና እንደ መሥሪያ ቤቱ ከዚህ ሽያጭ የየአካባቢው ህዝብ ምንም ጥቅም አላገኘም።

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic