ረሃብ፤ ዕድገትን አንቆ የያዘ መዘዝ | ኤኮኖሚ | DW | 26.10.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ረሃብ፤ ዕድገትን አንቆ የያዘ መዘዝ

በታዳጊው የዓለም ክፍል ረሃብ የልማት ተሥፋን አንቆ የያዘ ብርቱ መዘዝ ነው። በያመቱ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ከረሃብ ጋር በተሳሰሩ ምክንያቶች ሳቢያ ይሞታል። ችግሩ በአብዛኛው በቂ ምግብ ጠፍቶ አይደለም። ዋናው የብዙሃኑ መራብና መራቆት ምክንያት የማሕበራዊ ፍትህ እጦት፣ ከፖለቲካ፣ ከኤኮኖሚና ከሕብረተሰብ መገለል ነው።

የአፍሪቃ የድህነት ገጽታ

የአፍሪቃ የድህነት ገጽታ

ይህን መሠረታዊ ነጥብ በማንሣት የሚከራከሩ ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ድርጅቶች በቅርቡ ታስቦ በዋለው የዓለም የምግብ ቀን በየቦታው የድሆችን ድምጽ ለማሰማት የቅስቀሣ ዘመቻ አካሂደው ነበር። ረሃብ፤ ድህነትና ከዚሁ የተያያዙ ችግሮች ዛሬ በልማት ኋላ ቀር ሆኖ የሚገኘው የደቡቡ ዓለም ገጽታ መለያዎች ናቸው። ከአንዲት ዶላር ባነሰች የቀን ገቢ ዕለታዊ ኑሮውን ለመግፋት መከራውን የሚያየው የዓለም ሕዝብ ከሚሊያርድ ይበልጣል። በረሃብና ከረሃብ ጋር በተሳሰሩ በሽታዎች በአጭሩ የሚቀጩት የታዳጊው ዓለም ሕጻናት ቁጥር ስፍር የላቸውም። እርግጥ ይህ ሁሉ የሚሆነው ምግቡም ሆነ ለኤኮኖሚ ዕድገት አስፈላጊ የሆነው ዘዴ ጠፍቶ አይደለም። ቅን ፍላጎቱ ጠፍቶ እንጂ!

ረሃብን በመታገሉ በኩል ብዙ መነገር በያዘበት በአሁኑ ወቅት እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ዘንድሮም የዓለም የምግብ ቀን ለ 27ኛ ዓመት ታስቦ ውሏል። ለእርሻ ልማትና ለምግብ ዋስትና አስፈላጊው ሁሉ ገቢር እንዲሆን ለመቀስቀስ ይህን መፈክር ያነሣውና ዕለቱ በተቋቋመበት ጥቅምት 16 ቀን እንዲታሰብ ያደረገው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንዳበቃ ዕውን የሆነው የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት ነበር። ዓለምአቀፉ ድርጅት ፋኦ ዘንድሮ ያነሣው መፈክር መዋዕለ-ነዋይ ለእርሻና ለምግብ ዋስትና የሚል ነው።

ይሁንና ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ድርጅቶች ለየት ያለ አመለካከት አላቸው። በነዚሁ አባባል ዛሬ በሚሊያርድ ለሚቆጠረው የታዳጊው ዓለም ሕዝብ መራቆት ችግሩ በማከፋፈሉና በአጠቃቀሙ ረገድ ፍትሃዊ ዘዴ መጥፋቱ እንጂ የምግብ ምርት እጥረት ኖሮ አይደለም። በዓለም ላይ ማንም እንዳይራብ ለማድረግና የሁሉንም ፍላጎት ለመሸፈን የሚበቃ ምግብ ይመረታል። ግን ይህ እንዳይሆን ሁለት መሠረታዊ ችግሮች ተደንቅረው ይገኛሉ። የመጀመሪያው ከጠቅላላው የእርሻ ምርትም ሆነ ከውቂያኖስና ከወንዞች የሚገኘው ምግብ አብዛኛው ሥጋቸውና የተያያዘ ምርታቸው በኢንዱስትሪ ልማት ለበለጸገው ዓለም ሕዝብ ፍጆት እንዲውል የሚደረግ ከብቶች መቀለቢያ መሆኑ ነው።

ይህ ደግሞ ሁለተኛውን ምክንያት የማሕበራዊ ፍትህ መጓደልን ማባባሱ አልቀረም። በርከት ባሉ ታዳጊ አገሮች በዚሁ በማሕበራዊው ፍትህ እጦት የተነሣ አብዛኛው ሕዝብ ደህናውን ቀርቶ በዝቅተኛ ጥራት ደረጃ የሚገኘውን ምግብ እንኳ፤ ለምሳሌ በቆሎን የመሳሰሉ መሠረታዊ ምርቶች ለመግዛት አይችልም። አስፈላጊው አቅም የለውም። Action Against Hunger የተሰኘው ረሃብን ለመቋቋም የሚጥር ከመንግሥት ነጻ የሆነ ድርጅት ሰሞኑን እንደዘገበው ዛሬ በዓለም ላይ ከረሃብ ጋር በተያያዘ በሽታ በየአራቷ ሤኮንድ አንድ ሰው ይሞታል። በረሃብ የሚሰቃየው የዓለም ሕዝብም አንድ ሚሊያርድ ገደማ የሚጠጋ ነው።

ይሄው ዓለምአቀፍ ድርጅት አያይዞ እንዳመለከተው በረሃብ ሳቢያ በያመቱ ስድሥት ሚሊዮን ሕጻናት ይሞታሉ። ከአምሥት ዓመት ዕድሜ እንኳ ሳይደርሱ በአጭሩ ከሚቀጩት ሕጻናት ግማሹ የሚሞቱት በዚሁ በረሃብ ምክንያት ነው። ይህን ቀውጢ ሰዓት ያለፉት ረሃብን የቀመሱ ሕጻናትም ቢሆን ሕይወታቸውን ሙሉ የምግብ ጉድለት ባስከተለው የአካል ጉዳት ይሰቃያሉ። ችግሩ የተሻለ የትግል ዘዴን የሚጠይቅ ነው። ይህንኑ በመገንዘብም በዘንድሮው የዓለም ምግብ ቀን የተለያዩ ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ድርጅቶች ስፓኝ ውስጥ “የምግብ መብት፤ በአስቸኳይ!” በሚል መፈክር ቅስቀሣ አካሂደው ነበር።
ድርጅቶቹ ባቀረቡት የፊልም መረጃ ለእርሻ ልማት መራመድ ድጋፍ ሳይኖር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደማይቻል አስገንዝበዋል። በእርግጥም የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት ሰንጠረዦች እንደሚያመለክቱት በምድራችን ላይ በረሃብ ከሚሰቃየው ሕዝብ ከሰባ በመቶ የሚበልጠው የሚኖረው አርሶ ራሱን መቀለብ ሊበቃ በሚችልባቸው በገጠር አካባቢዎች ነው። በመሆኑም የቅስቀሣ ዘመቻ ያካሄዱት ድርጅቶች መንግሥታት የምግብ ዋስትናን መረጋገጥ ሰብዓዊ መብት አድርገው እንዲቀበሉና በዚህ ረገድ ፖሊሲዎቻቸውን እንዲከልሱ፤ እንዲሁም የአካባቢ ተፈጥሮን ይዞታ የጠበቀ የእርሻ ልማት እንዲያራምዱ ጠይቀዋል።

ለረሃብና ድህነት መጠናከር አንዱ ምክንያት የሥራ አጦች መበራከት ነው። ደቡብ አፍሪቃን እንደምሳሌ ብንወስድ በተለይ የብዙሃኑ ጥቁሮች ሁኔታ ከአፓርታይዱ ዘመን ብዙም አልተሻሻለም። የአገሪቱ ሥራ አጥ ብዛት ወደ 30 በመቶ የሚጠጋ ሲሆን ሌላው ቀርቶ የዕለት ጉርሱን ለማግኘት እንኳ የሚቸገረው ብዙ ነው። ባለፉት ዓመታት ወደ መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ፈጣን ዕርምጃ ያደረጉ ጥቁሮች ባይታጡም ሃቁ ዛሬም የነዚህም ብዛት ከ 8 በመቶ አይበልጥም። ከደቡብ አፍሪቃ 47 ሚሊዮን ሕዝብ 78 በመቶው ጥቁሮች መሆናቸው ሲታሰብ ይህ ያን ያህል ዕድገት የሚሰኝ አይደለም። ሥራ አጥነት በአፍሪቃ በጠቅላላው የድሃውና የረሃብተኛው ቁጥር እንዲበራከት ያደርጋል። ማሕበራዊ ዋስትናና ድጎማ በማይታወቅበት በዚህ ክፍለ-ዓለም ደግሞ ለአብዛኛው የሚቀረው መራቡ ብቻ ነው። ችግሩን ለመወጣት ማሕበራዊ ፍትህና በጎ አስተዳደር መስፈኑ፤ እንዲያም ሲል ለልማት አስፈላጊው ሁኔታ መመቻቸቱ ግድ ይሆናል። ይህ ደግሞ የታዳጊውን ብቻ ሣይሆን የበለጸገውን ዓለም ተሳትፎ ጭምር የሚጠይቅ ጉዳይ ነው።

በአሕጽሮት SADC በመባል የሚታወቀው የደቡባዊው አፍሪቃ የኤኮኖሚ ተራድኦ ማሕበር ዓባል መንግሥታት መሪዎች የአውሮፓውን መሰል ሕብረት ለመፍጠር በያዙት የረጅም ጊዜ ጥረት ሰሞኑን ጆሃንስበርግ ላይ ልዩ ስብሰባ አካሂደዋል። 14 መንግሥታትን የጠቀለለው ማሕበር ከሁለት መቶ ሚሊዮን የሚበልጥ የአካባቢውን ሕዝብ የሚወክል ነው። ከ 25 ዓመታት በፊት ሲቋቋም በዕድገቱ የጣለው ተሥፋ ታላቅ ነበር። የአፓርታይዱ አገዛዝ ዘመን እንዳበቃም በአካባቢው በኤኮኖሚዋ ጠንከር ያለችው ደቡብ አፍሪቃ ማሕበሩን በዓባልነት በመቀላቀል በድርጅቱ ውስጥ አዲስ የተሥፋ ጮራ እንዲፈነጥቅ ታደርጋለች።
ግን ሁሉም ነገር እንደታሰበው አልሆነም። በመሠረቱ ለ 1991 ዓ.ም. ታስቦ የነበረው የነጻ ንግድ ክልል ዕውን ለመሆን ከተጣለው የጊዜ ገደብ በላይ ተጨማሪ አሥር ዓመታት ሳይወእድ የሚቀር አይመስልም። ሌሎች በአውሮፓው ሕብረት ፈለግ የተጸነሱ የማሕበሩ ፕሮዤዎችም ቢሆን ገና ገቢር የሚሆኑበትን ጊዜ እየጠበቁ ነው። ባለፈው ሰኞ ምሽት ጆሃንስበርግ ላይ የተጠናቀቀው ልዩ የመሪዎች ጉባዔ እንግዲህ ብዙ መነጋገሪያ ነጥቦች ነበሩት። ሆኖም የአፍሪቃ እንድነት ድርጅት ከሶሥት ዓመታት በፊት ወደ አፍሪቃ ሕብረት እንደተለወጠው ሁሉ የአካባቢውን የልማት ተራድኦ ማሕበረሰብ ወደ ተመሳሳይ ግብ ማሻገሩ ገና ጊዜው እንዳልሆነ ነው የሚነገረው።

የዚምባብዌው ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ ሕብረት በመፍጠር ባለመው ሃሣብ ቁጥብነት እንዲኖር አስገንዝበዋል። በመሆኑም 14ቱ የደቡባዊው አፍሪቃ የልማት ተራድኦ መንግሥታት በመጀመሪያ ደረጃ የራሳቸውን አካባቢ ማሳደግ ይፈልጋሉ። ለዚሁ ያስቀመጧቸው ግቦች ደግሞ ከፍተኛ ናቸው። እ.ጎ.አ. እስከ 2008 ዓ.ም. ዓባል ሃገራቱ ነጻ የንግድ ክልል መፍጠር አለባቸው። በ 2010 ደግሞ የቀረጥ ሕብረት፤ በ 2015 የጋራ ገበያ፤ በ 2016 የምንዛሪ ሕብረት፤ በ 2018 ም አንድ ወጥ ምንዛሪ ለማስፈን ነው የሚታሰበው። ከ 14 አሥሩ ዓባል መንግሥታት ይህን የሚመለከተውን ፕሮቶኮል ሰነድ በፊርማ አጽድቀዋል። የደቡባዊው አፍሪቃ የኤኮኖሚ ተራድኦ ማሕበር ቢሮ ሃላፊ ቶማዝ-አውጉስቶ-ሣላማኦ በሂደቱ እርካታ እንደሚሰማቸው ነው የሚናገሩት። በዚህ ተግባር ሂደት ጥሩ ዕርምጃ እያደረግን ነው ይላሉ።

በሌላ በኩል በዚምባብዌ ችግርና ቀውስ አኳያ አንድም ጭብጥ ዕርምጃ አይታይም። ጉዳዩ በሰሞኑም ልዩ የመሪዎች የኤኮኖሚ ስብሰባ ከሁለት ወራት በፊት ተካሂዶ እንደነበረው ዓመታዊ ጉባዔ ሁሉ የአካባቢው ከባድ ችግር እንዳልሆነ ነገር ወደጎን ነው የተተወው። ለነገሩ የአንዴዋ የክፍለ-ዓለሚቱ የዕሕል ጎተራና የተሥፋ መለያ ዚምባብዌ ከባድ የኤኮኖሚ ቀውስ ላይ መውደቋ፣ ነጭ ገበሬዎች ከአገሪቱ መባረራቸውና ፕሬዚደንት ሙጋቤም አልመከር ማለታቸው አካባቢውን ብርቱ ችግር ላይ መጣሉ አልቀረም። ዓለምአቀፉ ዓመኔታ እየመነመነ ሄዷል።

ግን በደቡባዊው አፍሪቃ ተራድኦ ማሕበር ውስጥ የሚታየው የኤኮኖሚ ዕድገት ለሥፋ ምንጭ የሚሆን ነው። የአካባቢው አጠቃላይ ማህበራዊ ምርት 230 ሚሊያርድ ዶላር በመድረስ ከምዕራባዊው አፍሪቃ ሲነጻጸር እጥፍ የሚጠጋ ነው። ከሰባት ዓመታት በፊት አንድ ከመቶ ብቻ የነበረው አማካይ የዕድገት መጠንም ዛሬ በአምሥት ዕጅ ከፍ ብሏል። በሚቀጥለው ዓመት የአካባቢው የኤኮኖሚ ዕድገት በአማካይ 6 በመቶ እንደሚደርስ ነው የሚጠበቀው። ይህ ደግሞ ደቡባዊው አፍሪቃ በአውሮፓ አርአያ ሕብረት ለመፍጠር በያዘው ራዕይ ተሥፋን የሚያዳብር ነው።