ረሀብ ያሰጋቸው የናይጀሪያ ተፈናቃዮች | አፍሪቃ | DW | 25.06.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ረሀብ ያሰጋቸው የናይጀሪያ ተፈናቃዮች

በናይጀሪያ የቦርኖ ግዛት ከቦኮ ሀራም ሚሊሺያ ቡድን የሸሹ ቢያንስ 188 ስደተኞች ባለፈው ወር በረሀብ እና በጥም መሞታቸውን ድንበር የማይገድበው የሀኪሞች ድርጅት፣ «ሜድሰ ሶን ፍሮንትየር፣ ኤም እሴ ኤፍ» አስታወቀ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:16

ተፈናቃዮች በባማ መጠለያ ጣቢያ

24,000 ተፈናቃዮች የሚኖሩበትን የባማ መጠለያ ጣቢያ የጎበኘው «ኤም እሴ ኤፍ» በዚያ ያየው እጅግ አስደንጋጭ ሁኔታ ለጤና አስጊ መሆኑን አመልክቶዋል። ድርጅቱ ከጣቢያው ውጭ ከ1,000 የሚበልጡ ባለፈው አንድ ዓመት የተሰሩ መካነ መቃብሮችን፣ ከነዚህም 480ዎቹ የህፃናት መሆናቸውን እና በየቀኑም ሰዎች እንደሚሞቱ ገልጾዋል። የባማ መጠለያ ጣቢያ ነዋሪ የሆነው ሞኒማለም ብዙዎቹ ስደተኞች በዚሁ ሁኔታ ተደናግጠዋል።
« እውነት ነው፣ በረሀብ ምክንያት ብዙ ሰዎች ሞተዋል። ብዙዎቹም ሕፃናት ናቸው። ከሞቱት መካከል የጎረቤቴ ልጆችም ይገኙባቸዋል። በባማ እና ባንኪ አካባቢዎች አሳሳቢ የምግብ እጥረት አለ። ለኛ መጠለያ ጣቢያ የሚቀርበው ምግብ በፍፁም በቂ አይደለም፣ የጣቢያው ነዋሪዎች ቁጥር ደግሞ ሁሌ እየጨመረ ነው። »


የቦርኖ ግዛት አስቸኳይ ርዳታ አስተባባሪ መስሪያ ቤት ኃላፊ አህመድ ሳቶኒ ግን «ሜድሰ ሶን ፍሮንትየር፣ ኤም እሴ ኤፍ» ቢያንስ 188 ስደተኞች ሞቱ ያለበትን እና እጣቢያውን ሁኔታ በተመለከተ ያወጣውን ዘገባ አጠያይቀዋል።
« ይህ እውነት አይደለም። ይህን ቁጥር ከየት እንዳመጡት እኔ አላውቅም። ምክንያቱም የቦርኖ ግዛት አስቸኳይ ርዳታ አስተባባሪ መስሪያ ቤት ሰዎች ባማ መጠለያ ጣቢያ አብረዋቸው ነበሩ። እና ያኔ አንድም ሰው መሞቱን አላየንም። ከዚያ በተረፈ ደግሞ ከአንድ መቶ የሚበልጡ ሕሙማንን ማይዱግሪ ወደሚገኘው የጤና አገልግሎት መስጫ ማዕከል ወስደናል። በመሆኑም፣ እዚህ ቁጥር ላይ እንዴት እንደደረሱ ለማወቅ አልችልም። »
የመብት ተሟጋቾች መንግሥት የችግረኞቹን ሕይወት ለማትረፍ በቂ ስራ እንዳልሰራ ነው ያስታወቁት።
« ይህ አሳዛኝ ነው። መንግሥት ለችግረኞቹ እንደሚገባው እንክብካቤ ባለማድረጉ ሊነቀፍ ይገባል። በመሆኑም፣ ፌዴራዊው እና ያካባቢው መንግሥታት ሕይወታቸውን ያጡትን ተፈናቃዮች ቤተሰቦችን እና የናይጀሪያን ሕዝብ በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ እንፈልጋለን። »
የቦርኖ ግዛት መንግሥት እና ዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅቶች በሰሜን ምሥራቅ ናይጀሪያ እና በቻድ ሀይቅ አካባቢ የሚገኙት ተፈናቃዮች አሳሳቢ የምግብ እጥረት ሊግጥማቸው እንደሚችል አስቀድመው አስጠንቅቀው እንደነበር ገልጸዋል።

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic