ረሀብ እና ግጭት በደቡብ ሱዳን | አፍሪቃ | DW | 18.10.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ረሀብ እና ግጭት በደቡብ ሱዳን

አፍሪቃ ዉስጥ ርሃብ ካጠቃቸዉ ሀገራት አንዷ ደቡብ ሱዳን ከዜጎቿ ገሚሱ የእርዳታ እህል ፈላጊ ሆኗል። የዓለም የምግብ መርሃግብር በየመጠለያዉና መንደራቸዉ ለሚገኙ በርካታ ደቡብ ሱዳናዉያን በየጊዜዉ ምግብ ማደሉን ቀጥሏል። በሀገሪቱ ዉስጥ ለተከሰተዉ የርሀብ ቀዉስ የዝናብ እጥረት ብቻ ሳይሆን የሚካሄደዉ የእርስ በርስ ጦርነትም ዋናዉ ምክንያት ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:37
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:37 ደቂቃ

የዝናብ እጥረት ያመጣዉን ረሀብ ግጭቱ አባብሶታል፤

ዴልኪየ ኩንስ ኒኮቶልቦር የሚለዉ አገላለፅ የሞንጎሊያ ቋንቋ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን በደቡብ ሱዳን  የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ሕፃናት ሳይቀሩ የሚያዉቁት ስም ሆኗል። ትርጓሜዉ የዓለም የምግብ መርሃግብር ማለት ነዉ። መጠለያዉ ዉስጥ የሚኖሩት ሕፃናት ሁለት ነገሮች ያዉቃሉ። አንደኛዉ ከተመ የዓለም የምግብ መርሃግብር ምግብ እንደሚመጣ፤ ሁለተኛዉ ደግሞ የፀጥታ ጥበቃ በሞንጎሊያ እንደሚደርግላቸዉ። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የስደተኞቹ መጠለያ ከጋና ወታደሮች በተጨማሪ በዋናነት በሞንጎሊያ የተመድ የሰላም አስከባሪ ወታደሮች መጠበቁ ነዉ። ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2014ዓ,ም አንስቶ የስደተኞቹ መጠለያ በጦርነት መካከል ጥበቃ የሚደረግለት ራሱን የቻለ ዓለም ሆኗል። በሀገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ የተመድ ሲቪሎችን ከጥቃት ለመከላከል መጠለያዉን አቋቋመ። በዚህ ስፍራም የረዥም ጊዜ  ክብካቤ የሚደረግላቸዉ 200,000 የሚሆኑ ሰዎች ይገኛሉ። ባለፉት ዓመታትም ግጭቱ እያደገ የረሀብ ቀዉስን አስከትሎ መላ ሀገሪቱን በሚባል ደረጃ ተቆጣጥሯል። በአሁኑ ወቅትም ስድስት ሚሊየን ደቡብ ሱዳናዉያን ኑሯቸዉ በእርዳታ ምግብ ላይ የተመሠረተ ሆኗል። 
በቤንቱ የስደተኞች መጠለያ መጋዘን ዉስጥ የየዕለቱ ሥራ በወጉ ይከናወናል። በየወሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የተራቡ ሰዎች የሚከፋፈለዉን ምግብ ለመቀበል ይሰለፋሉ። አብዛኞቹም ሴቶች ናቸዉ። በደቡብ ሱዳን ባህል ለምግብ መሰለፍ የወንዶች ሥራ አይደለም። የሚሰለፉት ሰዎች ብዙ ቢሆኑም ግፊያ እና ትርምስ ግን አይታይም። ሃና ናያሩሬ ከሌሎቹ ሴቶች ጋር በመሆን በትዕግሥት ተራዋን እየጠበቀች ነዉ። የአራቶች እናት የሆነችዉ ሃና ካለ እርዳታ ለመኖር ብዙ ሞክራ ነበር። አስከፊዉ ግጭት ሳይበርድ ከጥቂት ወራት በፊት ከመጠለያዉ ወጥታ ወደቀድሞዉ መንደሯ ከነልጆቿ ለመመለስ ሞክራለች። 


«የፀጥታ ይዞታዉ ጥሩ ባይሆንም ቢያንስ በቤቴ አካባቢ የራሴን ሰብል እና አትክልቶች መትከልና ማብቀል እሞክራለሁ።»
እንዲያም ሆኖ በየወሩ ለአምስት ሰዓት ያህል እየተጓዘች የእርዳታ ምግብ ለመቀበል ወደመጠለያዉ ትመጣለች። ያለፈዉ የዝናብ ወቅት ባልተለመደ መልኩ አጭር መሆኑ ሰብል የማብቀል ሙከራዉን አዳጋች አድርጎታል። ለአካባቢዉ ነዋሪዎች ግን ከዝናብ ማጣቱ ይልቅ የቀጠለዉ ዉጊያ ነዉ ኑሯቸዉን የከፋ ያደረገባቸዉ። በዚህ ሁሉ መካከል በእርሻ ቦታቸዉ ላይ ጥቂት ማብቀል ቢችሉም እንኳን የተራቡ የመንግሥት ወታደሮች፤ አማፅያን ወይም ወሮበሎች ወደአካባቢዉ በመምጣት በጉልበት የፈለጉትን ይወስዱባቸዋል። ሃና ናያሩሬ ዝርፊያ እና ጥቃት ለረዥም ጊዜያት የዕለት ከዕለት ሕይወቷ አካል ሆነዉ መዝለቃቸዉን ትናገራለች። 
«የተሰጠኝን የምግብ ራሽን ተሸክሜ ወደመንደሬ በምጓዝበት ጊዜ በጣም አደገኛ አካባቢዎችን ማለፍ የግድ ይኖርብኛል። እርግጥ ነዉ ተዋጊዎቹ የያዝነዉን ራሽን ሁሉ አይወስዱም ጥቂት ለእኛ ይተዉልናል።»
ከታጣቂ ቡድኖቹ ጋር በመሰለፉ ባሏን ለወራት አላየችዉም። ሁኔታዉ በጣም አደናጋሪ ነዉ፤ የታጣቂዎቹ ጥምረት እና ግብ የተምታታ ነዉ፤ አንዳንዶቹ ቡድኖችም ቁጥር እንጂ ስም የላቸዉም። በፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር እና በቀድሞ ምክትላቸዉ ሪክ ማቻር መካከል የተነሳዉ አመግባባት ሰፍቶ በጎሳ እና በጎጥ ትግል ተበታትኗል። ቶማስ ሄርስ እንደ ሃና ያሉ ሴቶች የሚያጋጥማቸዉን አደገኛ ሁኔታ በቅርበት ያዉቃሉ። የጀርመኑ ግብረ ሠናይ ድርጅት ቬልት ሁንገር ሂልፈ ባልደረባ በቢንቱ መጠለያ ስፍራ የምግብ እደላዉ አስተባባሪ ናቸዉ። ቶማስ ሄርስ በየአካባቢዉ ተጨማሪ የምግብ ማደያ ማዕከሎች ቢኖሩ የተሻለ እንደሚሆን ያምናሉ። በመጠለያዉ ዉስጥ የማይኖሩት ሴቶች ለደህንነታቸዉ ሲባል ረዥም መንገድ መጓዝ የለባቸዉም ባይናቸዉ። 


«ተጨማሪ የማደያ ጣቢያዎችን መክፈት ብንችል ለሰዎቹ በተለይም ለሴቶቹ በጣም ጥሩ ይሆን ነበር። ሆኖም ለእኛም ሆነ ለሠራተኞቻችን ያለዉ አደጋ ከፍ ይላል። የሰፈራ ጣቢያዉ ባነሰ እና በተበታተነ ቁጥር የራሳችንን ሰዎች ደህንነት እንኳን ማረጋገጥ አስቸጋሪ ይሆናል።» 
ደቡብ ሱዳን ዉስጥ የእርስ በርስ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ቢያንስ 79 የሰብዓዊ ርዳታ ሠራተኞች ተገድለዋል። የሀገሪቱ ዜጋ የሆነዉ ፓትሪክ ማች እንደሚለዉ አብዛኛዉ ወንጀል  በታጠቁ ቡድኖች እንዲሁም በመንግሥት ወታደሮች የሚፈጸመዉ በመራባቸዉ ነዉ። 
«ደሞዝ የላቸዉም። ወደጦርነት ገብተዉ ያገኙትን ነዉ የሚወስዱት። እርግጥ መግደልም ሆነ አስገድዶ መድፈር ደሞዝ ካለመከፈል ጋር የሚያገናኘዉ ነገር የለም፤ ይልቁንም ማኅበራዊዉን ሥርዓት ከመስበር ጋር ይገናኛል። ለአብዛኞቹም በሰላማዊ ሲቪል እና በታጠቀ ተዋጊ መካከል ልዩነት የለም።» 
በግብረ ሠናይ ተግባር የተሰማሩት ቶማስ ሄርስ በዚህ ሁሉ መካከል ደቡብ ሱዳን አቅጣጫ እንደሳተች ያምናሉ። ወጣት የሀገሪቱ ዜጎች ከጦርነት ዉጭ ሌላ አማራጭ መመልከት ከጀመሩ በደቡብ ሱዳን ያለዉ ደም አፋሳሽ ግጭት ሰክኖ የረሃብ ቀዉሱም ሊያከትም እንደሚችልም ያመለክታሉ።

ሸዋዬ ለገሠ /አድሪያን ክሪሽ

ኂሩት መለሰ 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች