ረሀብና የተዛባው የመንግሥታት የፖለቲካ መርኅ፣ | ዓለም | DW | 18.01.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ረሀብና የተዛባው የመንግሥታት የፖለቲካ መርኅ፣

ባለፈው 2010 ጎርጎሪዮሳው ዓመት በዓለም ዙሪያ የረሃብተኛው ቁጥር ወደ 100 ሚሊዮን መናሩ ታውቋል። የእርዳታ ድርጅቶች፤ በተለይ በድሆች አገሮችአዲስ የረሃብ መቅሠፍት ያሠጋል በማለት በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው።

default

ድሀነት ከሚያጠቃቸው አገሮች መካከል አንዷ በሆነችው በሄይቲም፣ ልጆች ይራባሉ።

የሰሜኑም ሆነ የደቡቡ ንፍቀ-ክበብ የፖለተካ መርኅ፤ እስካሁን ድህነትን መታገል አልቻለም። የዶቸ ቨለ ባልደረባ፣ ዑተ ሼፈር በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ሐተታ ጽፋለች ፤ ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው አቅርቦታል።

በድህነት በማቀቁት አገሮች፣ በቂ ምግብ ባለማግኘት በየ 6 ቱ ደቂቃ አንድ ህጻን ይሞታል። በኢንዱስትሪ በበለጸጉት አገሮች፤ ህዝቡ ኑሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከባድ እየሆነበት ነው። በዓለም ዙሪያ፣ 30 አገሮች፣ አብዛኞቹ አፍሪቃ ውስጥ የሚገኑ ናቸው፣ በምግብ እጥረት በመማቀቅ ላይ ናቸው። በአውሮፓና በዩናይትድ እስቴትስ፣ መንግሥታቱ፣ ለግብርና ድጎማ በማቅረብ ፣ ምርቱ እንዲትረፈርፍ ከማድረጋቸውም፤ በርካሽ ዋጋ ወደ አዳጊ አገሮች በመላክ፤ ገበያውን ያሰናካክሉታል። በረሃብና ተመጣጣኝ ምግብ ባለማግኘት ሰዎች በሚሞቱባቸው አገሮች፣ የዐረብ ባህረ-ሰላጤ አገሮችና የቻይና ታላላቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ፣ አህል ለማምረትና ወደ አገራቸው ለማጋዝ በብዙ ሺ ሄክታር የሚለካ መሬት ይገዛሉ። ዑተ ሼፈር እንደምትለው፤ የተዘበራረቀ ዓለም! የከሠረ ፖለቲካ!

አንዳንዶቹ፣ ከመጠን በላይ፣ ሌሎቹ ደግሞ እጅግ ጥቂት የሚላስ የሚቀመስ ነው ያላቸው። ታላላቅ የግብርና ኢንዱስትሪዎች፤ በገፍ ለማምረት ሲሆን የሚሯሯጡት፣ በታዳጊ አገሮች ፣ አብዛኛው አርሶ-አደር፣ የዘመናት የአሠራር ልምዱን በመቀጠል ከእጅ ወደ አፍ የሚሆን ነው የሚያመርተው።

የምግብ ውድነት፤ በሌጎስ፤ ካይሮም ሆነ አልጀርስ ከተሜዎችን በአጅጉ ጎንጧል። በዓለም ገበያ የመሠረታዊ መባልዕት ዋጋ ትንሽ እንኳ ከጨመረ፣ የሸማቾችን ኪስ ቆንጠጥ ማድረጉ፤ የማይቀር ነው። አቅም የሌላቸው በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ድሆች ደግሞ ይበልጥ ነው የሚሰማቸው።

የዓለም ህዝብ ቁጥር እየጨመረ ስለሚሄድ፤ ችግሩ ይበልጥ እየተባባሰ መሄዱ አይቀሬ ነው። እ ጎ አ እስከ 2050 አሁን 7 ቢሊዮን የሚገመተው የዓለም ህዝብ ቁጥር፣ ወደ 9 ቢሊዮን ገደማ ከፍ ይላል። በሚመጡት ዓመታትም ከሚመረተው ይልቅ የፈላጊው መጠን ይበልጥ ከፍ ማለቱ የማይቀር ነው። በአሁኑ ጊዜም ቢሆን ፣ በዓለም ዙሪያ አንድ ቢሊዮን ያህል ህዝብ በረሃብ ይማቅቃል። ይህ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ የፖለቲካ ቦንብ ሊባል የሚችል ነው። በ 2007 እና 2008 በደቡብ አሜሪካ፤ አፍሪቃ እና እስያ፣ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ረሃብተኞች አደባባይ በመውጣት፣ ጎዳናዎችን አስጨንቀው እንደነበረ አይዘነጋም። ከ 30 በላይ በሚሆኑ አገሮች በተፈጠረ ሁከት፣ በደርዘኖች ሊቆጠሩ የሚችሉ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

የፖለቲካ መፍትኄ ግን አልተፈለገም፣ አልተገኘምም ። የአየር ንብረት ለውጥና የተፈጥሮ አካባቢ ከሚያደርሱት ተጽእኖ ባሻገር የፋይናንሱ ትንበያም ለመሠረታዊ መባልዕት ዋጋ መዋዠቅ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረጉ አልቀረም። እጅግ አጠያያቂ የሆነውን በድሆች አገሮች የእርሻ መሬቶችን በመቀራመት፣ ገንዘባቸውን ሥራ ላይ ለማዋል የተነሳሱትንም የፖለቲካ መሪዎች፤ መረን ነው የለቀቋቸው። ባለፉት 2 ዓመታት የውጭ ኩባንያዎች፣ 47 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ፣ 2/3ኛው አፍሪቃ ውስጥ ሱዳን፤ ሞዛምቢክ ፣ኮንጎ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እንዲሁም ሴራ ሊዮንን በመሳሰሉ አገሮች ተከራይተዋል። በስልጣን የባለጉ ፈላጭ ቆራጭ የአፍሪቃ መሪዎች፣ ለህዝባቸው ኅልውና የሚበጀውን እጅግ ውድ የሆነ ለም መሬት ለባዕዳን እያሳለፉ ይሰጣሉ። የቡድን 8 አገሮች፤ ኩባንያዎቻቸው፣ በነጻ ፍላጎታቸው በሚቀምሩት ደንብ እንዲመሩ ይሻል፤ ይህ ደግሞ ዑተ ሸፈር እንደምትለው የማያጽናና ህልም ነው።

በአዳጊ አገሮች፣ የገጠር ልማትና መለስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች፣ ዐቢይ ድርሻ ሊኖራቸው ይገባል። ጠበብት እንደሚሉት ፣ በዓለም ዙሪያ ምርትን ከፍ ማድረግ የሚቻለው በዚህ በኩል ነው። አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች፤ ይበልጥ ለታላላቅ ኩባንያዎች አቅራቢዎች እንዲሆኑ ማደፋፋር ፣ መርዳት ያሻል። የገጠር ልማት ፣በግብርና በሚመኩ ሞዛምቢክን በመሳሰሉ አገሮች ዐቢይ የፖለቲካ ርእስ አይደለም። ግን በሌሎቹ ም አዳጊ አገሮች ሁሉ፣ በአንደኛ ደረጃ የሚታይ የፖለቲካ ጉዳይ መሆን ነበረበት። 80% የዓለም ረሃብተኞች የሚኖሩት በገጠር ነው። እርግጥ ማሳቸው ምናልባት ለም ላይሆን ይችላል ወይም መጠኑ በቂ አይደለም። አንዳች ድጋፍ ወይም ምክር አይሰጣቸውምና። መንግሥቶቻቸውም የገጠርን ልማት አናንቀው ነው የሚያዩት። በስልጣን ላይ ያሉት ልሂቃን፤ የገጠርን ልማት ኋላ-ቀር ነው ብለው ያስባሉ።

መታየት ያለበት እንዲሁ ከምርት መጨመር አኳያ መሆን የለበትም። በኢንዱስትሪ ኩባንያዎችና ደጋፊዎቻቸው ግፊት የፖለቲካው አመራር የተዛባ አመለካከት ነው ያለው። ልማት፤ የግብርናና የኤኮኖሚ ፖለቲካ፣ በበለጸጉት አገሮች፤በመልማት ላይ ባሉት አገሮችም በጥሞና ሊታሰብበትና፣ ሊያዝም ይገባል። እህል ፣ በቀጥታ ተጠቃሚው እጅ ሊገባ ይገባል። በቀጥታ በሚመረትበት ቦታ ምግብ መዘጋጀት ይኖርበታል። የማምረቻው መሣሪያ፣ የተለያየ የአየር ንብረትንና የተፈጥሮ አካባቢን ግምት ውስጥ ማስገባት ይጠበቅበታል። ይህም ሲሆን ፣ የእኛውን በመሰለ ዓለም አቀፍ ኤኮኖሚ ፤ ምግብ የማግኘት መብት ፣ ተከብሮ እንዲገኝ ማድረግና፣ ረሃብን መታገል ይቻላል።

ተክሌ የኋላ

ሒሩት መለሰ

ተዛማጅ ዘገባዎች