1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሦስት የሲቪክ ድርጅቶች ታገዱ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 17 2017

ከተሰጣቸው ፈቃድ ውጪ ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ በሰብአዊ መብት ጥበቃ ዙሪያ ይሠሩ የነበሩ ሦስት የሲቪክ ድርጅቶች ከሥራቸው ታገዱ። በኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን እግድ የተጣለባቸው ድርጅቶች የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)፣ የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች እና ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ ናቸው።

https://p.dw.com/p/4nOvb
የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)
የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)

ሦስት የሲቪክ ድርጅቶች ታገዱ

ከተሰጣቸው ፈቃድ ውጪ ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ በሰብአዊ መብት ጥበቃ ዙሪያ ይሠሩ የነበሩ ሦስት የሲቪክ ድርጅቶች ከሥራቸው ታገዱ። በኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን እግድ የተጣለባቸው ድርጅቶች የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)፣ የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች እና ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ ናቸው። ድርጅቶቹ ለመታገዳቸው "ከፖለቲካ ገለልተኛ መሆን ሲገባቸው፣ ከዓላማቸው ውጭ በመንቀሳቀስ የአገርን ጥቅም የሚጎዱ ተግባራት ላይ ተሠማርተዋል" የሚል ምክንያት እንደቀረበባቸው ገልፀዋል።  የሲቪክ ድርጅቶቹ በተናጥል ባወጧቸው መግለጫዎች ግን ከፖለቲካ ነፃና ገለልተኛ ሆነው የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ጥረት ከማድረግ የዘለለ ሌላ ዓላማ እንደሌላቸው ገልፀዋል።የኢትዮጵያ የሲቪክ ድርጅቶች የሰላም ጥሪ

ከታገዱት አንዱ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)  "ከዓላማው ውጪ ምንም ዓይነት ተግባራት ላይ እንደማይሳተፍ እና በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ፍጹም ገለልተኛ ተቋም መሆኑ" በአጽንዖት ሊታወቅ ይገባል ሲል ከእገዳው በኋላ ባወጣው መግለጫ ገልጿል። ካርድ "ግልጽነት፣ ገለልተኝት እና ዴሞክራሲያዊነት" የድርጅቱ መርኾዎች መሆናቸውን አስታውሷል። ተጨማሪ ማብራሪያ የጠየቅናቸው የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሞገስ ደምሴ በጽሑፍ የወጣውን መግለጫ እንድንጠቀም ከመግለጽ ውጭ ተጨማሪ ማብራሪያ በድምፅ እንደማይሰጡ ገልፀውልናል። ኃላፊው ከሳምንታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የሲቪክ ምህዳር ከዶቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ግጭት መሠረት አድርጎ የሲቪክ ምኅዳሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበበ መጥቷል የሚል ግምገማ ነው ያለው"

እርምጃው በሕግ የተቀመጠውን ቅደም ተከተልና ቅድመ ሁኔታ የተከተለ ነውን? 

ሌላኛው መታገዱ የተነገረው የሲቪክ ድርጅት «የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች» የቀረበበትን የእግድ ምክንያት አልተቀበለውም። ይልቁንም ድርጅቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ "ከፖለቲካ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ" ሥራውን ማከናወኑን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ከማንኛውም የሥራ እንቅስቃሴ መታገዱን ያስታወቀው ይህ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ጋር በመወያየት ችግሩን ለመፍታት እንደሚጥር ገልጿል። ለተጨማሪ ማብራሪያ ኃላፊዎችን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ግን አልተሳካም።ሲቪክ ድርጅቶችና ምሁራን ለዘላቂ ሰላም መስፈን ምን ሠሩ?

ሌላኛው በኢትዮጵያ ሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የእግድ ደብዳቤ እንደደረሰው ያስታወቀው «ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ» የተባለው የሲቪክ ድርጅት ነው። ድርጅቱ ለመታገዱ ተመሳሳይ ምክንያት እንደቀረበለት ጠቅሶ ነገር ግን ባለፉት አራት ዓመታት የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታዎችን ለማሻሻል ጥልቅ የምርምር ሥራዎችን፣ የውትወታ ተግባራትን ከማከናወን በቀር ክሱ በቀረበበት ተግባር ውስጥ ያልተሳተፈ እና በፖለቲካም ሆነ በሌሎች መሰል ጉዳዮች ፍፁም ገለልተኛ መሆኑ ገልጿል።

የሲቪል ማኅበረስበ ድርጅቶች ባለስልጣን የወሰደው እርምጃ በሕጉ የተዘረዘረውን ቅደም ተከተልና ቅድመ ሁኔታ የሚጥስ መሆኑንም ይሄው ድርጅት ጠቅሶ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የሕግ የበላይነት እንዲፀና እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ባህል እንዲሰፍን ጥረት ማድረጉን እንደሚቀጥልበት አስታውቋል። የኢትዮጵያ ሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ከተመዘገቡ በኋላ የሚጠበቅባቸውን ያልተወጡ ያላቸውን 1500 ያህል ሲቪክ ድርጅቶች ባለፈው ዓመት ዘግቷል። አሁን ስለታገዱት ሦስቱ ድርጅቶች ለመጠየቅ ወደ ባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ደጋግመን ብንደውልላቸውም ምላሽ አይሰጡም። ኢትዮጵያ ውስጥ የሲቪክ ምህዳሩ እየተጠናከረ ወይስ እየተዳከመ ነው የሚለውን ከዚህ በፊት የጠየቅነቸው አንድ የሲቪክ ድርጅት መሪ "ጠንካራ የሲቪክ ማሕበር ቢኖረንማ የውትወታ ሥራ ይሠራ ነበር። ይህን መሥራት አልቻልንም። አስታራቂም መሆን ነበረብን። ይህ የሚያመለክትህ ጠንካራ ሲቪክ ማሕበር የለንም" ሲሉ መልሰው ነበር።

የሲቪክ ድርጅቶች ምክረ ሀሳብ - ለተመድ

የታገዱት የሲቪክ ድርጅቶች የሰላም ጥሪ እና ውትወታ በማድረግ የሚጠቀሱ ናቸው

 

እነዚህ የታገዱት የሲቪክ ድርጅቶች ከሌሎች ጋር በመሆን በየዓመቱ የሰላም ጥሪ በማድረግ ይታወቃሉ። ድርጅቶቹ በ2016 ዓ.ም ብቻ በመላው ኢትዮጵያ ከ1,792 በላይ ግጭት መመዝገባቸውን፣ በዚህም ምክንያት ከ6,164 በላይ ሰዎች መሞታቸውን በቅርቡ በጋራ ባወጡት የዳሰሳ ጥናት አመልክተው ነበር። ይህም ብቻ አይደለም በጋዜጠኞች፣ በሰብዓዊ መብት ተማጋቾች ላይ ይደርሳሉ ያሏቸውን ችግሮች ነቅሰው በማሳየት ያልተቋረጠ ውትወታ በማድረግ የሚታወቁ ጭምር ናቸው።

ሰሎሞን ሙጬ

ኂሩት መለሰ

ፀሐይ ጫኔ