ሦስቱ የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት መሪ እጩዎች | ጤና እና አካባቢ | DW | 27.01.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

ሦስቱ የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት መሪ እጩዎች

ሦስቱ የመጨረሻ እጩዎች በመጭዉ ግንቦት በ194 የድርጅቱ አባል ሀገራት የሚመረጡ ሲሆን ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ከተመረጡ የዓለም አቀፉን የጤና ድርጅት የሚመሩ የመጀመሪያዉ አፍሪቃዊ ይሆናሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:13

ሦስቱ የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት መሪ እጩዎች

 

ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት በምህጻሩ «WHO» የድርጅቱን  መሪ ለመምረጥ  እጩዎችን  በማወዳደር ላይ ይገኛል። የድርጅቱ የስራ አስፈጻሚ ቦርድ ባለፈዉ ረቡዕ በጄኔቫ  የመጨረሻወቹን ሦስት እጩወች ይፋ አድርጓል። ከነዚህም መካከል የኢትዮጵያ የቀድሞ የጤናና የዉጭ ጉዳይ ሚንስትር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖምን ጨምሮ የፓኪስታን የቀድሞ የጤና ጥበቃ ሚንስትር ሳኒያ ኒሽታር እና የቀድሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ አማካሪ  የብሪታኒያዉ ዴቪድ ናባሮ  ይገኙበታል። በጎርጎሮሳዊዉ የዘመን ቀመር ከ2006  ዓ.ም ጀምሮ ድርጅቱን እየመሩ ያሉትን የሆንግ ኮንግ ተወላጅዋ ማርጋሬት ቻንን ለመተካት እየተካሄደ  ያለዉ የእጩወች  የምርጫ ዘመቻ በመጭዉ ግንቦት ፍጻሜዉን ያገኛል። ድርጅቱን ላለፉት አስር ዓመታት የመሩት የሆንግ ኮንግ ተወላጅዋ ማርጋሬት ቻን በድርጅቱ  በቂ ግልጽነትና ተጠያቂነት አላሰፈኑም በሚል በአንዳንዶች ዘንድ ሲወቀሱ ቆይተዋል። የሃርቫርድ ዩንቨርሲቲ  የአለም የጤና ተቋም ዳይሬክተር  ፕሮፌሰር አሽሽ ጃሃ የማርጋሬት ቻንን አስተዳደር  ከሚወቅሱት አንዷ ናቸዉ።አሽሻ ጃሃ ምርጫዉን በተመለከተ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በሰጡት አስተያየት  በ2014 በምዕራብ አፍሪቃ  ሀገሮች ተከስቶ በነበረዉ የኢቮላ ወረርሽኝ ድርጅቱ ባሳየዉ ቸልተኝነት  የ11 ሺህ ሰወች ህይወት መቅጠፉን አስታዉሰዋል። ይሁን እንጅ  የደረሰዉን ችግር በተመለከተ ጀኔቫ ከሚገኙ የተቋሙ ሰራተኞች አንድም በሃላፊነት የተጠየቀና የተቀጣ  አለመኖር በድርጅቱ የተጠያቂነት ችግር መኖሩን ያሳያል ሲሉ ተችተዋል። ደይቼ ቨለ ያነጋገራቸዉ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የህክምና ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር  መስፍን አርአያ መሰል የአፍሪቃ የጤና ችግሮችን ለመፍታት አፍሪካዊ የጤና ባለሙያ ወደ ዓለም አቀፉ የጤና ተቋም በመሪነት መምጣት አስፈላጊ  ነዉ ይላሉ። የኦክስፎርድ ዩንቨርሲቲ ዶክተር የሆኑት ብርታኒያዊዉ  የ67 ዓመቱ ዴቪድ ናባሮ በኢቮላ ወረርሽኝ ባደረጉት አስተዋጽኦ ጥሩ ስም ያላቸዉና ቢመረጡ ለወረርሽኝና ለአጣዳፊ  በሽታወች ትኩረት እንደሚሰጡ ተናግረዋል። ከእጩወቹ መካከል ብቸኛዋ ሴት ተወዳዳሪ የሆኑት የፓኪስታኗ ዶክተር  ሳኒያ ኒሽታር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስራ ልምድ ያላቸዉና ሀገራቸዉ  ፓኪስታን ዉስጥ ለትርፍ ያልተቋቋመ የጤና ማዕከል መስራች ናቸዉ ተብለዋል።የ 53 ዓመቷ ሳኒያ ኒሽታር ቢመረጡ የድርጅቱን አሰራር ለማሻሻል እንደሚፈልጉ ጠቅሰዋል።

ሦስተኛዉና  ብቸናዉ አፍሪቃዊ እጩ ተወዳዳሪ ፤ኢትዮጵያ የቀድሞ የጤናና የዉጭ ጉዳይ ሚንስትር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በወባ ወረርሽኝ ምርምር በማድረግና የጤናን ተደራሽነት ለማስፋፋት ተግተዉ የሰሩ በሚል ስራቸዉ  በድርጅቱ ዘንድ አጽንኦት ተሰጥቶታል። ቢመረጡም የታዳጊ ሀገሮችን የጤና ችግር ለመፍታትና የምዕተዓመቱን የጤና ግብ ለማሳካት እንደሚሰሩ ገልጸዋል። በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የህክምና ትምህርት ክፍል መምህሩ ዶክተር  መስፍን አርአያ፤ ኢትዮጵያዊዉን ዕጩ በተመለከተ በሰጡት አስተያት የአፍሪቃን የጤና  ችግር በቅርብ የሚያዉቁ በመሆናቸዉ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ቢመረጡ ለአፍሪቃ ብሎም በተመሳሳይ ችግር ዉስጥ ላሉ ታዳጊ ሀገሮች ጠቃሚ ነዉ ብለዋል። ሦስቱ የመጨረሻ እጩወች በመጭዉ ግንቦት በ194 የድርጅቱ አባል ሀገራት  የሚመረጡ ሲሆን ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ከተመረጡ የዓለም አቀፉን የጤና ድርጅት የሚመሩ የመጀመሪያዉ አፍሪቃዊ ይሆናሉ።

 

ፀሐይ ጫኔ

አዜብ ታደሰ

 

 

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች