ሥነ-ቴክኒክና ኢንዱስትሪ፣ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 17.04.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ሥነ-ቴክኒክና ኢንዱስትሪ፣

ለልማት መሣካት ለኤኮኖሚና ሁለንተናዊ ዕድገት ፣ የሥነ ቴክኒክ ከፍተኛ እገዛ ወሳኝነት አለው። ለሥነ ቴክኒክ መሥፋፋትና ለአዳዲስ የፈጠራ ውጤት ደግሞ መሠረቱ ትምህርት ነው፦ ከትምህርትም ፣ ሳይንና ሂሳብ!በዚህ ረገድ ከደረጁት አገሮች ፤ ጀርመንንና

ጃፓንን ፤ እመርታ በማሳየት ላይ ከሚገኙት ድግሞ ደቡብ ኮሪያንና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል። በመሆኑም፤ ከምድራችን ክፍለ- ዓለማት አንዷ ፣ ማለትም በቆዳ ስፋት የ 6ኛነቱን ደረጃ የያዘችው (7,692,024 አጸፋ ኪሎሜር)እንዲሁም፣ ከ 23 ሚሊዮን ያነሰ ህዝብ ያላት አውስትሬሊያ ትምህርትን በጥራትና በስፋት ለማዛመት፣ ከሚመጣው 2014 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት አንስቶ ፣ 15,2 ቢሊዮን ያህል የአሜሪካ ዶላር ለመመደብ ማቀዷ ተነገረ። የአውስትሬሊያ መንግሥት፣ የአገሪቱ ት/ቤቶች፤ እ ጎ አ እስከ 2025 በጽሕፈትና ንባብ፤ በሂሳብ እንዲሁም በሳይንስ ፣ ደረጃቸው ፣ በዓለም ውስጥ ከከፍተኛዎቹ 5 አገሮች መካከል እንዲመደብ ነው የሚፈልገው። ጠ /ሚንስትር ወ/ሮ ጁሊያ ጊላርድ ፤ «በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የትምህርት ሥርዓት መቅረጽ ፣ ለወደፊቱ የአገሪቱ ጠንካራ ኤኮኖሚ ዋናው ቁልፍ ይሆናል ነው »ያሉት።

እያንዳንዱ አውስትሬሊያዊ ልጅ እጅግ በጣም ጥሩ ትምህርት ካገኘ ፤ የከፍተኛ ደመወዝ ዋስትና እንደሚኖረውም ነው ጠ/ሚንስትሯ ያስገነዘቡት። እናም የፊታችን ዓርብ፣ የአውስትሬሊያ የተለያዩ መስተዳድሮች ኀላፊዎች ካንቤራ ላይ በመሰብሰብ ከመከሩ በኋላ፣ እስከመጪው ሰኔ እቅዱን እንዲያጸድቁ ሳያስገነዘቡ አላለፉም። አገሪቱ ባለፉት 40 ዓመታት ለ ት/ቤቶች ታቀርብ የነበረው የድጎማ መጠን እንዲገመገም ያደረጉት ወ/ሮ ጁሊያ፣ በቂ አለመሆኑን ፣ እንዲያውም ብዙዎች እንዳይበልጧት የሚያሠጋ መሆኑን ከመጠቆማቸውም፤ ይህ ልዩ ፕሮጀክት፤ በመጪው መስከረም በሚካሄደው ምርጫ ከሌበር ፓርቲያቸው ጋር እንደገና ለመመረጥ ምናልባት መደላድል ሊሆንላቸው እንደሚችልም ሳያሰላስሉ አልቀሩም። ያም ሆነ ይህ ጥራት ያለው ትምህርት ፤ በተለይም ሳይንስና ሂሳብን የመሳሰሉ የትምህርት ዘርፎች እንዲስፋፉ ዕድል መስጠቱ በመጨረሻ ሀገርንና ህዝብን በሚገባ ሊክሱ እንደሚችሉ ይታመንበታል።

የሥነ ቴክኒክ ዕድገትም ሆነ ምጥቀት ጠቀሜታ ፤ እስከምን ድረስ ሊዘልቅ እንደሚችል በዚህ በጀርመን ሀገር በቅርቡ ከመጋቢት 30 -ሚያዝያ 4 ቀን 2005 ዓ ም የተካሄደው የሃኖፈር የአንድ ሳምንት የኢንዱስትሪ ዐውደ-ርእይ ዓይነተኛ ምሳሌ ነበረ ማለት ይቻላል።

«የተሣሠረ ኢንዱስትሪ» የሚለውን ርእስ ፣ መሪ ቃል ያደረገው ዐውደ ርእይ፣ በ 18ኛ ክፍለ ዘመን በእንፋሎት ኃይል ባቡር ማሽከርከር ከተጀመረበት የኢንዱስትሪው አብዮት አንስቶ የቀጠለው ሂደት ፣ አሁን 4ኛ እርከን ላይ መደረሱን ነው ያስገነዘበው። በ 20ኛው ክፍለ ዘመን አውቶማቲክ የፋብሪካዎች ምርት በ 1960ኛዎቹ ደግሞ የዓለምን ገጽ ኮምፒዩተር በእጅጉ ለውጦታል። ከጀርመን ታዋቂ የምርምር ተቋማት መካከል በአኸን ከተማ የ«ፍርውንሆፈር» የአምራች ሥነ ቴክኒክ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ Fritz Klocke በበኩላቸው 4ኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ተጀምሯል ባይ ናቸው። 4ኛው አብዮት የትኛው ነው?

1, «ሁሉም በኢንተርኔት ነው ተግባሩን የሚያከናው ነው። ከወጣት እስካዛውንት ሁሉም ትውልድ በኢንተርኔት የሚገለገል ሆኗል። አሁን የደረስንበት ደረጃ፣ ኢንተርኔትን ወደ ፋብሪካም ማስገባት ከሚቻልበት ላይ ነው።»

ለምሳሌ ያህል፤ የአውቶሞቢሉን ኢንዱስትሪ መጥቀስ ይቻላል። ተሽከርካሪዎች እጅግ ተሻሽለዋል፣ ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ በአውቶማቲክ የሚንቀሳቀሱ ሆነዋል። ከጊዜ ወደ ጊዜ ፣ በደኅንነት አስተማማኝነት ረገድ ይበልጥ ዋስትና የሚሰጡ ሆነው መገኘት ይኖርባቸዋል። ቢቻልም ረዘም ላለ ጊዜ የሚያገለግሉ ሊሆኑ ይገባል። በማንኛውም ጊዜ ሁሉም ትክክል የሚሠራ ስለመሆን -አለመሆኑ ለመቆጣጠር፣ ሠሪው ፋብሪካ ከሸጠም በኋላ ከአውቶሞቢሉ ጋር ግንኙነቱን ይቀጥላል።»

2, «ወደፊት አውቶሞቢል የኢንተርኔት አንድ አካል ሆኖ ተግባሩን ይቀጥላል። ሙሉ በሙሉ በዘመናዊው የሥነ ትክኒክ መረብ ተጠላልፏል። እንዲያውም አንዱ አውቶሞቢል ፣ ከሌላ ተሽከርካሪ ጋር መልእክት መለዋወጥ ይችላል። አንድ ተሽከርካሪ፣ እንዲያውም ቀደም ሲል ያልወጣ መርኀ ግብርን ወደ ጎን በመተው፤ የጥገና ወይም የቁጥጥር ጊዜ ያስፈልገኛል የሚል መልእክት ማስተላለፍም ይችላል።»

ተክሌ የኋላ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic