ሥመ-ጥሩው ጠበቃ ተሾመ ገ/ማርያም አረፉ | ዓለም | DW | 21.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ሥመ-ጥሩው ጠበቃ ተሾመ ገ/ማርያም አረፉ

ባለፈዉ አርብ ያረፉት የመጀመሪያዉ የኢትዮጵያ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ተሾመ ገ/ማርያም ዛሬ አዲስ አበባ ዉስጥ ተቀበሩ።በአፄ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓተ-መንግስት በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ውስጥ ያገለገሉት አቶ ተሾመ፤ የውጭ ተቋማትን በጥብቅና በመወከል ይታወቁ ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:46
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:46 ደቂቃ

የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አረፉ

የዛሬው የአፍሪቃ ኅብረት የቀድሞው የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት የመመሥረቻ ቻርተርን ካረቀቁት አንዱ ነበሩ። አቶ ተሾመ ገብረማርያም ቦካን።ከዛሬዋ አዳማ ከተማ አቅራቢያ ሰቀቀሎ ከተሰኘች የገጠር መንደር በ1923 ዓ.ም. የተወለዱት አቶ ተሾመ በልጅነታቸው «አባ-ጠና» የሚል የፈረስ ስም ተሰጥቷቸው ነበር። በንጉሳዊው ስርዓተ-መንግሥት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ እና ሚንሥትር ደዔታ ሆነው ያገለገሉት አቶ ተሾመ የሕግ ትምህርታቸውን በካናዳው የማክ ጊል ዩኒቨርሲቲ ተከታትለዋል። ሥራቸውን የጀመሩት ግን በየኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥራ አስፈፃሚ የሕግ አማካሪ እና ልዩ ረዳት ሆነው ነበር። የቀድሞው የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማሕበር ፕሬዝዳንት አቶ ወንድማገኘሁ ገ/ስላሴ የአገሪቱን የማዕድን አዋጅ የተሟላ ለማድረግ አቶ ተሾ ላቅ ያለ ሚና ተጫውተዋል ሲሉ ይናገራሉ። «ከ1928 ዓ.ም. ጀምሮ የፕላቲኒየም፤ ወርቅ እና ማዕድናት ፍለጋን የተመለከቱ የተለያዩ የተቆራረጡ ህግጋት ነበሩ።» የሚሉትአቶ ወንድምአገኘሁ አቶ ተሾመ የማዕድን ሚኒስቴርን ከተቀላቀሉ በኋላ የተሟላ አዋጅ ገቢራዊ እንዲሆን አድርገዋል ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

የቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ የልጅ ልጅ የሆኑት ልዑል በዕደ ማርያም መኮንን የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት የመመሥረቻ ቻርተር ዝግጅት ላይ አቶ ተሾመ በጊዜው ውጭ ጉዳይ ሚኒሥትር ከነበሩት አቶ ከተማ ይፍሩ እና አቶ ክፍሌ ወዳጆን ከመሳሰሉ ባለሙያዎች ጋር ላቅ ያለ ሚና መጫወታቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ልዑል በዕደማርያም በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የደርግ የአስተዳደር ሥርዓት ላይ የሰላ ትችት የሚሰነዝሩት አቶ ተሾመ ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ ባለስልጣናት ጋር ለስምንት አመታት ያክል በእስር ላይ መቆየታቸውን ያስታውሳሉ። በንጉሳዊው ሥርዓተ-መንግሥት ውስጥ በባለሥልጣንነት በማገልገላቸው ምክንያት ለእስር የተዳረጉት አቶ ተሾመ በወታደራዊ ፍርድ ቤት ቀርበው በነፃ እንዲለቀቁ ቢወሰንላቸውም ሳይፈቱ መቅረታቸውን ልዑል በዕደ ማርያም መኮንን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።  

አቶ ተሾመ ገብረማርያም  በስማቸው ባቋቋሙት የጥብቅና ተቋም እስከ ሕይወታቸው ፍፃሜ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የማማከር አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል። ከእስር በተፈቱ ማግሥት በፖለቲካ እና ሕግ አማካሪነት የተሰጣቸውን ሥራ ጥለው በጥብቅና ሙያ የተሰማሩት አቶ ተሾመ የአፍሪቃ አገራት የማዕድን ዘርፍን አስመልክቶ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ያማክሩ ነበር። ልዑል በዕደ ማርያም፤ አቶ ተሾመን «ስኬታማ»ሲሉ ይገልጧቸዋል።

የቀድሞው የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማሕበር ፕሬዝዳንት አቶ ወንድምአገኘሁ ገ/ስላሴ አቶ ተሾመ በተደጋጋሚ ለተሻሻለው የኢትዮጵያ የማዕድን አዋጅ አስተዋፅዖ ሲያበረክቱ ቆይተዋል ሲሉ ይናገራሉ። የውጭ የማዕድን ኩባንያዎችን ወደ ኢትዮጵያ ይጋብዙ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ወንድማአገኘሁ ለኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማሕበር መጠናከር ድጋፍ ያደርጋሉ ይሏቸዋል።
ጠበቃ ተሾመ ገ/ማርያም ቦካን የቀብር ስነ-ስርዓት በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባው የቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተ-ክርስቲያን ተፈፅሟል። 
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ 

Audios and videos on the topic