ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 09.03.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

እግር ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ ቴኒስ

የበርሊን የጎል ዋስትና ቮሮኒን

የበርሊን የጎል ዋስትና ቮሮኒን

እግር ኳስ

አውሮፓ ውስጥ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ጠንካራው እንደሆነ በሚነገርለት በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ያለፈው ሰንበት የፌደሬሺኑ ዋንጫ ውድድር ሩብ ፍጻሜ የተጠናቀቀበት ነበር። በዚሁ ውድድር ማንቼስተር ዩናይትድ፣ ቼልሢይ፣ ኤቨርተንና አርሰናል የመጨረሻዎቹ አራት ቡድኖች በመሆን ለግማሽ ፍጻሜው ዙር አልፈዋል። የ 11 ጊዜው የፌደሬሺን ዋንጫ አሸናፊና የክብረ-ወሰን ባለቤት ማኒዩ ወደ ግማሽ ፍጻሜው የተሻገረው በተጋጣሚው በፉልሃም ላይ ፍጹም ልዕልና በማሣየት ነው። ማንቼስተር ዩናይትድ 4-0 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ ሁለቱን የመጀመሪያ አጋማሽ ጎሎች ያስቆጠረው ድንቅ አጥቂው ካርሎስ ቴቬዝ ነበር።
25 ሺህ ተመልካች በተገኘበት ስታዲዮም ከእረፍት በኋላ የተቀሩትን ጎሎች ያስገቡት ደግሞ ዌይን ሩኒይና ፓርክ-ጂ-ሱንግ ነበሩ። ማንቼስተር ዩናይትድ ዘንድሮ ከፌደሬሺኑ ዋንጫ ባሻገር በፕሬሚየር ሊጉና በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የዋንጫ ባለቤት የመሆን ዕድሉን ጠብቆ መራመዱን ቀጥሏል። ቼልሢይ ደግሞ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ያለፈው ኮቬንትሪይ ሢቲይን 2-0 በመሸኘት ነው። በ 34 ሺህ ተመልካች ፊት ጎሎቹን ያስቆጠሩት ዲዲየር ድሮግባና አሌክስ ነበሩ። ሌሎቹ በፌደሬሺኑ ዋንጫ ውድድር ለመቀጠል የበቁት ሁለት ክለቦች ኤቨርተንና አርሰናል ናቸው። ኤቨርተን ሚድልስቦርህን 2-1 ሲያሸንፍ አርሰናል ደግሞ የሁለተኛ ዲቪዚዮኑን ክለብ በርንሊይን 3-0 ረትቷል።

በዚህ በጀርመንም ባለፈው ሣምንት አጋማሽ ላይ የፌደሬሺኑ ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ ግጥሚያዎች ሲካሄዱ በተለይ ከአራት ሁለቱ ግጥሚያዎች የደመቁና የጎል ፌስታ የታየባቸው ነበሩ። ባየርን ሌቨርኩዝን ቀደምቱን ክለብ ባየርን ሙንሺንን 4-2 ቀጥቶ ከውድድሩ ሲያሰናብት በዩኤፋ ዋንጫ ኤ-ሢ.ሚላንን በሩብ ፍጻሜ ያስወጣው ቬር’ደር ብሬመን ደግሞ ቮልፍስቡርግን 5-2 ለማሽነፍ በቅቷል። ባየርን ሙንሺን የቀድሞ ጥንካሬው ከድቶት ሲታይ አሠልጣኙ ዩርገን ክሊንስማን እንዳለው ቡድኑ ከእንቅልፉ የነቃው ሲበዛ ቆይቶ ነበር።
“በደምብ መንቀሳቀስ የጀመርነው ሶሥት ጎሎች ከገቡብን በኋላ ነበር። ከዚያም ሁለት ጎሎች እናስቆጥራለን። ሌላው ቀርቶ ሶሥት ለሶሥት የማድረግ ዕድልም ነበረን። ግን ሌቨርኩዝን በሚገባ ነው ያሸነፈው። ዛሬ የተሻለው ቡድን ነበር። እናም የፌደሬሺኑን ዋናጫ መርሣት አለብን”

በሁለቱ ግጥሚያዎች በጠቅላላው 13 ጎሎች መቆጠራቸው ጨዋታዎቹ ለተመልካች ማራኪና አርኪ እንደነበሩ የሚያመለክት ነው። በተቀረ ሃምቡርግ ዝቅተኛ ተጋጣሚውን ቬኸንን አሽንፎ ሲያልፍ ሻልከ ደግሞ በሁለተኛው ዲቪዚዮን ክለብ ተሰናክሎ ቀርቷል። በሚቀጥለው ወር በሚካሄዱት የግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያዎች ሃምቡርግ ከብሬመን፤ ሌቨርኩዝን ከማይንስ ይገናኛሉ። ከዚያም የፌደሬሺኑ ዋንጫ የፍጻሜ ግጥሚያ በመጪው ግንቦት ወር በርሊን ላይ ይካሄዳል።

በሰንበቱ የአንደኛ ዲቪዚዮን ግጥሚያዎች ላይ እናተኩርና በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ተፎካካሪዎቹን በ 12 ነጥቦች ልዩነት ማስከተል ከያዘ በኋላ ባለፉት ሣምንታት እያቆለቆለ የመጣው ባርሤሎና እንደገና አመራሩን ሊያሰፋ በቅቷል። ባርሣ አትሌቲክ ቢልባዎን 2-0 ሲረታ አመራሩን ከአራት ወደ ስድሥት ነጥቦች ከፍ ሊያደርግ የቻለው በቅርብ የሚከተለው ሬያል ማድሪድ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋር 1-1 በሆነ ውጤት በመወሰኑ ነው። ሤቪያ አልሜይራን 2-1 በመርታት በሶሥተኛው ቦታ ሲቆናጠጥ ኤስፓኞልን 1-0 ያሸነፈው ቪላርሬያል አራተኛ ነው። ቫሌንሢያ በአንጻሩ በኑማንሢያ 2-1 በመሸነፉ ወደ አምሥተኛው ቦታ ለመጠጋት የነበረውን ዕድል ሳይቀምበት ቀርቷል፤ ስምንተኛ ነው።

በኢጣሊያው ቀደምት ሊጋ ሤሪያ-አ ኢንተር ሚላን ዘንድሮም ሻምፒዮንነቱን ለመድገም በሚያደርገው ግፊት በስኬት እየተራመደ ነው። ኢንተር የስዊድኑ ኮከብ ዝላታን ኢብራሂሞቪችና ማሪዮ ባሎቴሊ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ጌኖዋን 2-0 ሲያሸንፍ በሰባት ነጥቦች ልዩነት መምራቱን ቀጥሏል። ቶሪኖን 1-0 የረታው ጁቬንቱስ ሁለተኛ ሲሆን ኤሢ.ሚላን ደግሞ አታላንታን 3-0 በማሸነፍ ሶሥተኛ ነው። ለሚላን ሶሥቱንም ጎሎች ያስቆጠረው የኢጣሊያው ብሄራዊ ቡድን አጥቂ ፊሊፒ ኢንዛጊ ነበር። ኢንተርና ጁቬንቱስ ነገና ከነገ በስቲያ ለሚካሄዱት የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ግጥሚያዎች የሚቀርቡት ጠቃሚ ተጫዋቾች ቆስለውባቸው ነው።

ፉክክሩ በተለየ ሁኔታ በጦፈበት በጀርመን ቡንደስሊጋ ሄርታ በርሊን ባለፈው ሣምንት ከሃምቡርግ የነጠቀውን አመራር በአራት ነጥቦች ሊያሰፋ ችሏል። በርሊን ኮትቡስን 3-1 ሲያሽንፍ ሶሥቱንም ጎሎች ያስቆጠረው አንድሬይ ቮሮኒን ነበር። ባየርን ሙንሺን ሃኖቨርን 5-1 በመሸኘት መልሶ ወደ ሁለተኝነቱ ቦታ ሲያሻቅብ ከብሬመን ጋር ባዶ-ለባዶ የተለያየው ሆፈንሃይም በሶሥተኝነት ተወስኗል። ቮልፍስቡርግ ድምጹን አጥፍቶ ድንገት አራተኛው ቦታ ላይ ብቅ ሲል የሣምንቱ ደካማ ቡድን ከሁለት ወደ አምሥተኛ ቦታ የተንሸራተተው ሃምቡርግ ነው። ሃምቡርግ በመጨረሻው ቡድን በመንሸን ግላድባህ ተቀጥቶ ከሜዳ ይወጣል ብሎ የጠበቀ ማንም አልነበረም።

ለማንኛውም ከሁለት እስከ አምሥት ያሉት ቡድኖች በሙሉ በነጥብ እኩል ሲሆኑ ፉክክሩ የጠነከረ ሆኖ ይቀጥላል። በሌላ በኩል በሣምንቱ አጋማሽ የፌደሬሺን ዋንጫ ግጥሚያ ገኖ የታየው ሌቨርኩዝን ትናንት በሜዳው ከቦሁም ጋር ባካሄደው ግጥሚያ 1-1 በሆነ ውጤት ሲወሰን ከቀደምቶቹ ቡድኖች ጋር የነበረውን ንኪኪ ማጣቱ ግድ ነው የሆነበት። አሠልጣኙ ብሩኖ ላባዲያ ቡድኑ ያገኛቸውን የጎል ዕድሎች ሁሉ ሊጠቀም ባለመቻሉ በጣም ነው ያዘነው። በአንጻሩ የተጋጣሚውን ወገን የትግል መንፈስም ሳያደንቅ አላለፈም።

“የቦሁም ቡድን ግሩም የትግል ባህርይ ያለውና ላንዳፍታ እንኳ ጋብታ ያልታየበት ነበር። ሆኖም የጨዋታውን ሂደትና እኛ ያገኝናቸውን የጎል ዕድሎች ለተመለከተ ዛሬ ሳንጠቀምባቸው መቅረታችን የሚያሳዝን ነው። ምንኛ ባረካን ነበር”

ግን አልሆነም፤ ሌቨርኩዝን አሁን ሻምፒዮንነቱ ቀርቶ ለመጪው የዩኤፋ ዋንጫ ውድድር ለማለፍ የሚያበቃውን ቦታ እንኳ እንዳያጣ ብርቱ ትግል ነው የሚጠብቀው።

በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮንም የቀደምቱ ቡድኖች ፉክክር እንደ ጀርመን ቡንደስሊጋ ሁሉ እየጠበበ በመሄድ ላይ ነው። ቀደምቱ ኦላምፒክ ሊዮን ዘንድሮም ለስምንተኛ ተከታታይ ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን በያዘው ውጥን የሰንበቱ ግጥሚያ አልሰመረለትም። ሊዮን በሊል 2-0 ሲረታ አመራሩ በአንዲት ነጥብ የመነመነች ሆናለች። በአንጻሩ በሁለተኝነት የሚከተለው ፓሪስ-ሣን-ዣርሜይን ሎሪየንትን 1-0 በማሸነፍ አንደኝነቱን በቅርብ ማሽተት ይዟል። ኦላምፒክ ማርሤይና ቱሉዝ ደግሞ ሶሥተኛና አራተኛ ሆነው ይከተላሉ። በቱሉዝ 3-0 የተረታው ቦርዶ ወደ አምሥተኛው ቦታ ሲያቆለቁል ከአንድ እስከ አራት ያሉትን ቡድኖች የሚለዩዋቸው አራት ነጥቦች ብቻ ናቸው።

በኔዘርላንድ ሻምፒዮና አልክማር ከሰንበቱ ግጥሚያዎች በኋላ የብቻ አመራሩን ወደተደላደለ የ 11 ነጥብ ልዩነት ለማስፋት በቅቷል። አልክማር ኒሜገንን 1-0 ሲያሸንፍ ራቅ ብለው የሚከተሉት ኤንሼዴና አያክስ አምስተርዳም በየበኩላቸው ግጥሚያ ከእኩል ለእኩል ውጤት ሊያልፉ አልቻሉም። ሄረንፌን አራተኛ፤ አይንድሆፈን አምሥተኛ! በፖርቱጋል ሻምፒዮና ቀደምቱ ቡድኖች ፖርቶ፣ ቤንፊካና ስፖርቲንግ ሁሉም በማሸነፋቸው የአመራር ለውጥ የለም። ፖርቶ በሁለት ነጥብ ልዩነት ቁንጮ ሆኖ ቀጥሏል። ከሰንበቱ ግጥሚያዎች በኋላ የአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ይዞታ ከሞላ-ጎደል ይህን የመሰለ ሲሆን የያዝነው ሣምንት ደግሞ ታላላቅ የሻምፒዮና ሊጋ ግጥሚያዎች የሚካሄዱበት ነው።

በአውሮፓ ክለቦች የሻምፒዮና ሊጋ በመጨረሻዎቹ 16 ቡድኖች መካከል በሚካሄደው ውድድር በነገው ምሽት የሚደረጉት የመልስ ግጥሚያዎች የሚከተሉት ናቸው። ባየርን ሙንሺን ስፖርቲንግ ለዝበን፤ ጁቬንቱስ ቸልሢይ፤ ሊቨርፑል ሬያል ማድሪድ፤ ፓናቴናኢኮስ ቪላርሬያል! ባየርን ሙንሺን በመጀመሪያው ግጥሚያ ሊዝበንን 5-0 በማሸነፉ ተዓምር ካልተፈጠረ በስተቀር ወደ ተከታዩ ዙር ማለፉ ያለቀለት ነገር ነው። በሌላ በኩል ጁቬንቱስና ሬያል ማድሪድ በእንግሊዙ ክለቦች በቼልሢይና በሊቨርፑል የደረሰባቸውን የ 1-0 ሽንፈት መልሶ የማረቅ ዕድል አላቸው።

በፊታችን’ ረቡዕ ከሚደረጉት ቀሪ ግጥሚያዎች ዋነኛው በማንቼስተር ዩናይትድና በኢንተር ሚላን መካከል የሚካሄደው ነው። ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ግጥሚያ ባዶ-ለባዶ ሲለያዩ እንደ አዲስ ነው የሚጀምሩት ለማለት ይቻላል። በሌላ በኩል አርሰናል ከሮማ የሚጋጠም ሲሆን የመጀመሪያው 1-0 ድሉ የሚያበረታታው ነው። በተረፈ ባርሤሎና ከኦላምፒክ ሊዮን፤ እንዲሁም ፖርቶ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ካለፉት እኩል ለእኩል ውጤቶች በኋላ የግድ መሽናነፍ ይኖርባቸዋል። ቢበዛ ጨዋታዎቹ በውጭ ሜዳ በተቆጠሩ ጎሎች ብልጫ ቢለይላቸው ነው። በማግሥቱ ሕሙስ ደግሞ ምሽቱ የዩኤፋ ግጥሚያዎች ይሆናል።

አትሌቲክስ

ኢጣሊያ-ቶሪኖ ላይ በተካሄደ የአውሮፓ የአዳራሽ ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድር አጎልባች መድሃኒት በመውሰድ ሁለት ዓመት ተቀጥቶ የነበረውና ከቤይጂንግ ኦሎምፒክም ታግዶ የቀረው የብሪታኒያ ሯጭ ድዌይን ቼምበርስ የ 60 ሜትር አሸናፊ ሆኗል። ቼምበርስ ባለፈው ቅዳሜ ግማሽ ማጣሪያ በ 6,42 ሤኮንድ አዲስ የአውሮፓ ክብረ-ወሰን ሲያስመዘግብ ይሄው በውድድሩ ታሪክ ሶሥተኛው ፈጣን ጊዜ ነው። በአራት ጊዜ አራት መቶ ሜትር የዱላ ቅብብል የሩሢያ ሴቶች ሲያሸንፉ በወንዶች ምርኩዝ ዝላይ ፈረንሣዊው ሬናውድ ላቪሌን በ 5 ሜትር ከ 81 አንደኛ ሆኗል። በርዝመት ዝላይ ደግሞ ጀርመናዊው ሤባስቲያን ባየር ሲያሸንፍ በከፍታ ዝላይም የአገሩ ልጅ አሪያነ ፍሪድሪሽ ለድል በቅታለች።

ትናንት ጃፓን-ናጎያ ላይ በተካሄደ የሴቶች ማራቶን ሩጫ የአገሪቱ ተወዳዳሪዎች በተለየ ልዕልና አሸናፊ ሆነዋል። አንዲት ኬንያዊት በዘጠነኝነት መሃል ከመግባቷ በስተቀር ርቀቱን ከአንድ እስከ አሥር በመከታተል የፈጸሙት በሙሉ ጃፓናውያን ነበሩ። ዮሺኮ ፉጂናጋ በ 2 ሰዓት ከ 28 ከ 13 ሤኮንድ አንደኛ ሆናለች። በተረፈ የዓለም የማራቶን ክብረ-ወሰን ባለቤት የብሪታኒያዋ ሯጭ ፓውላ ሬድክሊፍ የእግር ጣቷ ላይ በገጠማት ጉዳት የተነሣ ከሚቀጥለው ወር የለንደን ማራቶን ወደ ኋላ ማለቱ ግድ ሆኖባታል።

ሬድክሊፍ የለንደንን ማራቶን ሶሥት ጊዜ ማሸነፏ ይታወሣል። ፓውላ ከእንግዲህ የምታተኩረው በፊታችን ነሕሴ ወር በርሊን ላይ ለሚካሄደው የዓለም ,አትሌቲክስ ሻምፒዮና በመዘጋጀቱ ላይ ነው። በለንደኑ ማራቶን ያለፈው ዓመት አሸናፊ ጀርመናዊቱ ኢሪና ሚቲቼንኮ፣ ሩሜኒያዊቱ የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ኮንስታንቲና ዲታ፣ ኬንያዊቱ የኦሎምፒክ የብር ሜዳይ ተሸላሚ ካቴሪን እንዴሬባ፤ እንዲሁም ብርሃኔ አደሬንና ጌጤ ዋሚን የመሳሰሉት ቀደምት አትሌቶች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

በተረፈ በዓለም የቴኒስ ዴቪስ-ካፕ የመጀመሪያ ግጥሚያዎች ከብዙ በጥቂቱ አርጄንቲና ከኔዘርላንድ 5-0፤ ቼክ ሬፑብሊክ ከፈረንሣይ 3-2፤ ክሮኤሺያ ከቺለ 5-0፤ አሜሪካ ከስዊዝ 4-1፣ ሩሢያ ከሩሜኒያም እንዲሁ 4-1 ተለያይተዋል።

Mesfin Mekonnen