ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 16.02.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ባለፈው ሣምንት በዓለም ዙሪያ በርከት ያሉ የአትሌቲክስ ውድድሮች ሲካሄዱ ሣምንቱ ያለፈው እንደገና አንዳንድ አስደናቂ ውጤቶች በተመዘገቡበት ሁኔታ ነበር።

ቡንደስሊጋ፤ የበርሊን ጎል አግቢ ቮሮኒን

ቡንደስሊጋ፤ የበርሊን ጎል አግቢ ቮሮኒን

በአሜሪካ በፋየትቪል-አርካንሣስ ባለፈው አርብ ተካሂዶ በነበረ የአዳራሽ ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር ኢትዮጵያዊው በካና ዳባ አስደናቂ በሆነ ጊዜ የ 5 ሺህ ሜትር ሩጫ አሸናፊ ሆኗል። በካና ዳባ ባለፉት ሶሥት ዓመታት ውስጥ ከተመዘበቡት ጊዜያት ቀደምቱን ሰዓት ሲሮጥ በጠቅላላው በዚህ ርቀት ታሪክ ውስጥ ዘጠነኛው ፈጣን አትሌት መሆኑ ነው። የሃያ ዓመቱ ወጣት ሩጫውን በ 13 ደቂቃ ከ 17,89 ሤኮንድ ሲያሸንፍ አሁንም በቀደምትነት ጸንቶ የቀጠለው ቀነኒሣ በቀለ ከእምሥት ዓመታት በፊት ያስመዘገበው የዓለም ክብረ-ወሰን ነው።
የወጣቱ አትሌት ግሩም ድል የኢትዮጵያን የመካከለኛ ርቀት ሩጫ የወደፊት ተሥፋ ይበልጥ እንደሚያዳብር አንድና ሁለት የለውም። በዚሁ ሩጫ እስከ መጨረሻው ዙር ድረስ በጥቂት ዕርምጃዎች ሲመራ የነበረው አሜሪካዊው ጋለን ሩፕ ደግሞ እንዲሁ ግሩም በሆነ ጊዜ አዲስ ብሄራዊ ክብረ-ወሰን በማስመዝገብ ሁለተኛ ወጥቷል። ይህም በዓለም አምሥት ሺህ ሜትር ሩጫ ታሪክ ውስጥ አሥረኛው ፈጣን ሰዓት መሆኑ ነው። ሶሥተኛ፤ ሣም ቼላንጋ ከኬንያ! አሜሪካዊቱ ብላንካ ናይትም አስደናቂ በሆነ የ 22,88 ሤኮንድ ጊዜ የሁለት መቶ ሜትር አሸናፊ ሆናለች። በተረፈ በወንዶች የማይል ሩጫ የኒውዚላንዱ ኒክ ዊሊስ ሲያሸንፍ በሴቶች 3 ሺህ ሜትር ሩጫ ደግሞ ካናዳዊቱ አሌክስ ቤከር ለድል በቅታለች።

በኡክራኒያ-ዶኔትስክ በተካሄደ የአዳራሽ ውስጥ ውድድር ሩሢያዊቱ የምርኩዝ ዝላይ የአሎምፒክ ሻምፒዮን የለና ኢዚንባየቫ የራሷን 4 ሜትር ከ 97 ሤንቲሜትር የነበረ የዓለም ክብረ-ወሰን አሻሽላለች። ኢዚምባየቫ ልክ የዛሬ ዓመት በዚያው በዶኔትስክ አስመዝግባ የነበረውን ይህን ክብረ-ወሰን በሶሥት ሤንቲሜትር ስታሻሽል አምሥት ሜትር ከፍታን በመዝለል የመጀመሪያዋ ሴት አትሌት ለመሆንም በቅታለች። ለአስደናቂዋ የሩሢያ የአትሌቲክስ ንግሥት ይሄው 26ኛው ክብረ-ወሰንም መሆኑ ነው። በዚሁ ውድድር በወንዶች አውስትራሊያዊው ስቲቭ ሁከር 5 ሜትር ከ 92 በመዝለል አሸናፊ ሆኗል።

ስፓኝ-ቫሌንሢያ ላይ በተካሄደ የአዳራሽ ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር በ 1,500 ሜትር ሃሮን ካይታኒ የስፓኝ ተፎካካሪዎቹን አስከትሎ ሲያሸንፍ አብርሃም ጨርቆስ ደግሞ በ 3 ሺህ ሜትር ሁለት ኬንያውን ጥሎ በመግባት ለድል በቅቷል። በሴቶች 1,500 ሜትር ኑሪያ ዶሚንጌዝ ስፓኝ፤ እንዲሁም በ 3 ሺህ ሜትር ኬንያዊቱ ቪቪያን ቼሩዮት አሸናፊ ሆነዋል። በዚህ በጀርመን ካርልስሩኸ ላይ በተካሄደ የአዳራሽ ውስጥ ውድድር ደግሞ ኬንያውያን በ 800 ና በ 3 ሺህ ሜትር አሸናፊ ሲሆኑ ለአስተናጋጇ አገር ታላቁን ድል ያጎናጸፈችው የከፍታ ዝላይ የዓለም ሻምፒዮን የሆነችውን የክሮኤሺያ ኮከብ ብላንካ ቭላዚችን ያሸነፈችው አሪያነ ፍሪድሪሽ ነበረች። አሪያነ ያሽነፈችው 2 ሜትር ከ 5 ከፍታን በመዝለል ነው።

ከዚሁ ሌላ ጃማይካዊው የቤይጂንግ ኦሎምፒክ የሶሥት ወርቅ ሜዳይ ተሽላሚና የክብረ-ወሰን ባለቤት ኡሤይን ቦልት ኪንግስተን ላይ የያዝነውን ዓመት በ 400 ሜትር ድል ጀምሯል። በቤይጂንግ ኦሎምፒክ በመቶ፣ ሁለት መቶና በአራት ጊዜ መቶ ሜትር የዱላ ቅብብል አስደናቂ ውጤት ያስመዘገበው ቦልት ባለፈው አርብ ታላቁ የ 2008 ዓ.ም የጃማይካ የስፖርት ሰው በመባል ተሰይሞም ነበር። በፓሪስ የአዳራሽ ውስጥ ውድድር ደግሞ አውስትራሊያዊው ስቲቭ ሁከር በምርኩዝ ዝላይ ስድሥት ሜትር ከፍታን አቁዋርጧል። የኡክራኒያው ዝነኛ አትሌት የሤርጌይ ቡብካ 6,15 ክብረ-ወሰን አሁንም የማይደረስበት ሆኖ እንደቀጠለ ነው።

እግር ኳስ

ባለፈው ሣምንት አጋማሽ ላይ በዓለም ዙሪያ ከተካሄዱት በርካታ የወዳጅነት ግጥሚያዎች መካከል አንዳንዶቹ ተመልካች ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በ 2010 ዓ.ም. የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ምን እንደሚጠብቀው ያመላከቱ ነበሩ። ያለፈው ዓመት የአውሮፓ ሻምፒዮን የስፓኝ ቡድን እንግሊዝን ሤቪያ ላይ 2-0በመርታት ከሃያ ግጥሚያዎች በላይ በተከታታይ ሳይረታ ሲቀጥል ታላቅ ልዕልና ነው ያሳየው። ዴቪድ ቪያና ፌርናንዶ ሎሬንቴ ሁለቱን ጎሎች ሲያስቆጥሩ የእንግሊዝ ቡድን አንዴም ብቁ ተፎካካሪ ሆኖ አልታየም። ጥርስ የሌለው ነብር ነው የሆነው።

አርጄንቲናም በዲየጎ-አርማንዶ-ማራዶና አሰልጣኝነት ዘመን ካለፉት ጊዜያት ድክመቷ የተላላቀቀች መሆኗን ፈረንሣይን ማርሤይ ላይ 2-0 በማሽነፍ አስመስክራለች። ማራዶና ሃላፊነቱን ከተረከበ ካለፈው ሕዳር ወዲህ በሁለት ግጥሚያዎች ለሁለተኛ ድል ,መብቃቱ ነው። እንደ ፈረንሣይ ሁሉ ኢጣሊያም በብራዚል ስትረታ፤ በተለይ ጥገና የሚያስፈልገው መስሎ የታየው የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ነበር። ጥበብና ቅልጥፍና በጎደለው አጨዋወቱ በኖርዌይ 2-0 መረታቱ ግድ ሆኖበታል።
በተረፈ ከብዙ በጥቂቱ ለመጥቀስ የመጪው የዓለም ዋንጫ ውድድር አዘጋጅ ደቡብ አፍሪቃ በቺሌ 2-0 ስትሸነፍ ክሮኤሺያ ሩሜኒያን 2-1 ረትታለች። ሌሎች የአፍሪቃ አገሮች በተሳተፉባቸው ግጥሚያዎችም ኡሩጉዋይ ከሊቢያ 3-2፤ ሞዛምቢክ ከማላዊ 1-1፤ ማሊ ከአንጎላ 4-0፤ እንዲሁም ግብጽ ከጋና 2-2 ተለያይተዋል። በተጨማሪም አይቮሪ ኮስት ከቱርክ፤ ቱኒዚያ ከኔዘርላንድ፤ ሞሮኮ ከቼክ ሬፑብሊክ፤ ሁሉም እኩል ለእኩል በሆነ ውጤት ነር ግጥሚያቸውን የፈጸሙት። ወደ ሰንበቱ የአውሮፓ ሊጋ ግጥሚያዎች ሻገር እንበልና በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ሬያል ማድሪድ ጊዮንን 4-0 በመርታት ሊጋውን ከሚመራው ከባርሤሎና ጋር ያለውን ልዩነት ወደ አሥር ነጥብ ዝቅ ሊያደርግ በቅቷል። ለሬያል የሰንበቱ ድል በተከታታይ ስምንተኛው ሲሆን የጠቀመው ባርሤሎና ቤቲስን 2-0 ከመራ በኋላ በመጨረሻ እኩል ለእኩል መለያየቱ ነው።

በኢጣሊያ አንደኛ ዲቪዚዮን ዋነኛ ግጥሚያ ኢንተር የከተማ ተፎካካሪውን ኤ.ሢ. ሚላንን 2-1 በማሸነፍ አመራሩን ወደ ዘጠን ነጥብ ከፍ ሊያደርግ ችሏል። እንተር ያሸነፈው ብራዚላዊ አጥቂው አድሪያኖ እጁን ተጠቅሞ ባስቆጠራት የመጀመሪያ ግብ አከራካሪ በሆነ ሁኔታ ነው። ለማንኛውም ውጤቱ ለኢንተር ሲበጅ ለኤ.ሢ.ሚላን በ 11 ነጥብ ልዩነት ማቆልቆል ሆኗል። ሁለተኛው ጁቬንቱስም ቢሆን በገዛ ሜዳው ከሣምፕዶሪያ 1-1 ብቻ በመለያየት ወደፊት አልተራመደም።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየርን ሙንሺን ቀደምት ለመሆን በሰንበቱ ያገኘውን መልካም ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ባለፉት ወራት የአገሩን ኳስ ተመልካች ሲያስደንቅና ሲያስገርም የቆየው ከሁለተኛ ዲቪዚዮን ወጥቶ በአንዴ የነገሠ ቡድን ሆፈንሃይም በሌቨርኩዝን 4-1 ተቀጥቶ መንገዳገድ ሲጀምር ሳይታሰብ ቁንጮ ለመሆን የበቃው ባየርን ሙንሺንን በግሩም ጨዋታ 2-1 የረታው ሄርታ-በርሊን ነው። ሃምቡርግ ትናንት ቢለፌልድን 2-0 በማሽነፍ ወደ ሁለተኛው ከፍ ብሏል፤ ሶሥተኛው ባየርን ሙንሺን ነው። ግን በጀርመን ቡንደስሊጋ ውስጥ በቀደምቱ አራት ቡድኖች መካከል ያለው ልዩነት በሁለት ነጥብ ብቻ የተወሰነ በመሆኑ ፉክክሩ ከሣምንት-ሣምንት የጦፈ አንደሆነ ይቀጥላል። በተቀረ በፈረንሣይ፣ በኔዘርላንድና በፖርቱጋል፤ ሊዮን፣ አልክማርና ፖርቶ ከሰንበቱ ግጥሚያዎች በኋላም አመራራቸውን እንደያዙ ናቸው።

ቴኒስ

ትናንት ካሊፎርኒያ-ሣን-ሆሤ ላይ በተካሄደ የቴኒስ ፍጻሜ ግጥሚያ የቼክ ሬፑብሊኩ ራዴክ ስቴፓኔክ አሜሪካዊውን ማርዲይ ፊሽን በሶሥት ምድብ ጨዋታ 2-1 አሸንፏል። ሆኖም የሰንበቱ አስደናቂ የፍጻሜ ግጥሚያ ትናንት የተካሄደው ፓሪስ ላይ ነበር። በዚሁ ግጥሚያ ፈረንሣዊቱ አሜሊ ማውሬስሞ ሩሢያዊቱን የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ኤሌና ዴሜንትየቫን ሁለት ሰዓት ተኩል በፈጀ ድንቅ ጨዋታ ስታሽንፍ ድሏ በፓሪስ-ኦፕን ከ 2001 እና ከ 2006 ወዲህ ሶሥተኛው መሆኑ ነው። ብዙ ጊዜ በመቁሰል ተሰናክላ ከቆየች በኋላ እንደገና በጥንካሬ የተመለሰችው የአንዴዋ ቀደምት ተጫዋች ከደስታ ብዛት እንባ ሲተናቃት ታይታለች።

በሮተርዳም-ኦፕን ደግሞ በዓለም የማዕርግ ተዋረድ ላይ አንደኛ የሆነው የስፓኙ ራፋኤል ናዳል በእንግሊዛዊው በኤንዲይ መሪይ መሽነፉ ግድ ሆኖበታል። እርግጥ ናዳልን ከሽንፈቱ ይልቅ እንደገና የደረሰበት የጉልበት ጉዳት ይበልጥ ሳያሳስበው የቀረ አይመስልም። ናዳል ለሕክምና ዕርዳታ ጨዋታውን በተደጋጋሚ ማቁዋረጥ ነበረበት። በነገራችን ላይ ኤንዲይ መሪይ አንድ እንግሊዛዊ የሮተርዳሙን ውድድር ሲያሸንፍ የመጀመሪያው ይሆናል።

ቢስክሌት

ፈረንሣይ-ቱሎን ላይ በስድሥት ደረጃ ተከፋፍሎ የተካሄደው የሜዴትራኒያን አገር አቁዋራጭ ውድድር አሽናፊ በጠቅላላ ነጥብ የስፓኙ ሉዊስ-ሣንቼዝ ሆኗል። የትናንቱን የመጨረሻ እሽቅድድድም ያሸነፈው ፈረንሣዊው ዴቪድ ሞንኩቲዬ ነበር። በካሊፎርኒያ-ሣንታ-ሮዛም በተመሳሳይ ውድድር የስፓኙ ተወላጅ ፍራንሲስኮ ማንቼቦ የመጀመሪያውን ደረጃ እሽቅድድም በቀደምትነት ፈጽሟል። የቱር-ዴ-ፋራንስ የሰባት ጊዜ ሻምፒዮን ላንስ አርምስትሮንግ አሥረኛ ሲወጣ እርግጥ ፕሬሱን ከውጤቱ ይበልጥ የማረከው የቢስክሌቱ መሰረቅ ነበር።

ለማጠቃለል፤ በ 14ኛው የማሌይዚያ የላንግካዊ አገር አቁዋራጭ እሽቅድድም ደግሞ የኮሎምቢያው ሆሴ-ሮዶልፎ-ሤርፓ አሸናፊ ሆኗል። ከአንድ ሺህ ኪሎሜትር የሚበልጥ ርቀት ያለው የሰባት ቀናት እሽቅድድም ያበቃው ዋና ከተማይቱ ኩዋላ-ሉምፑር ላይ ነው።

MM