ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 26.01.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ያለፈው ሣምንትም በዓለም ዙሪያ የተለያዩ የስፖርት ውድድሮች የተካሄዱበት ነበር።

የጀርመን የዕጅ ካስ ቡድን ቁጣና ዳኛው

የጀርመን የዕጅ ካስ ቡድን ቁጣና ዳኛው

ክሮኤሺያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው የዓለም የዕጅ ኳስ ሻምፒዮና ወደ ግማሽ ፍጻሜው እየተቃረበ ነው። በሁለት ምድብ ተከፍሎ በሚካሄደው የሩብ ፍጻሜ ዙር ማጣሪያ ትናንት በምድብ አንድ አስተናጋጇ ክሮኤሺያ ስሎቫኪያን 31-25 ስትረታ ሁንጋሪያ ስዊድንን ጠባብ በሆነ ውጤት 31-30፤ እንዲሁም ፈረንሣይ ደቡብ ኮሪያን 30-21 አሸንፈዋል። በምድብ ሁለት ውስጥ ፖላንድ ከሰርቢያ 35-23፤ ዴንማርክ ከማቄዶኒያ 32-24 ሲለያዩ ያለፈው ሻምፒዮና ባለድል ጀርመን ትግል በተመላበት አከራካሪ ጨዋታ 25-24 በኖርዌይ ተረትታ በውድድሩ የመጀመሪያ ሽንፈቷን በመቀበል ከወዲሁ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ለማለፍ የነበራትን ዕድል ሳትጠቀምበት ቀርታለች።

ጀርመን የመጨረሻዎቹ አራት ጠንካራ ቡድኖች ለሻምፒዮንነት ወደሚታገሉበት ግማሽ ፍጻሜ ለመድረስ ነገ የአውሮፓ ሻምፒዮን ከሆነችው ከዴንማርክ ጋር ትጋጠማለች። ጨዋታው በጣሙን ወኝ ሲሆን እርግጥ ሁለቱም ቡድኖች እኩል ለእኩል ውጤት ይበቃቸዋል። ቢሆንም ግጥሚያው ለሁለቱም ቀላል አይሆንም። በመጨረሻዎቹ ሤኮንዶች ላይ ውዥምብር በታየበት የጀርመንና የኖርዌይ ግጥሚያ ሁለቱ የስሎቬኒያ ዳኞች አንድ የጀርመን ተጫዋች የዕጅ ውርወራውን ከአንዴም ብዙ ጊዜ እንዲደግም ያደረጉት ውሣኔ በጀርመኖች በኩል ብርቱ ቁጣን ነበር ያስከተለው። ኖርዌይ በዚህ ወቅት ሁለት ተጫዋቾች ተቀጥተውባት በጎዶሎ ስለነበረች ጀርመን ውጤቱን ለማስተካከል ጥሩ ዕድል ነበራት። ግን አልሆነም። ለማንኛውም በረኛው ሢልቪዮ ሃይነቬተር የዳኞቹን ውሣኔ መረዳቱ ቢያስቸግረውም ሽንፈቱ የራስ ድክመት ጭምር አላጣውም ባይ ነው።

“ጉድለቱን ሁልጊዜ በዳኞች ላይ መላከክ አይቻልም። እኛ ራሳችንም ፊት የነበሩንን ብዙ ብዙ ዕድሎች ሳንጠቀምባቸው ቀርተናል። ግን እንዴት ዳኞቹ ሶሥት ወይም አራት ጊዜ የዕጅ ውርወራው እንዲደገም ሊያደርጉ እንደቻሉ አልገባኝም። ይህ ለአኔ ጊዜ መፍጀት ያልነበረበት አጉል ቀልድ ነው”

ያም ሆነ ይህ ከትናንቱ ውጤት ወዲህ ምድብ አንድን ፈረንሣይና ክሮኤሺያ በአኩል ስምንት ነጥብ ይመራሉ፤ በምድብ ሁለት ውስጥ ደግሞ ዴንማርክ በስድሥት ነጥብ አንደኛ ስትሆን ጀርመን አንዲት ነጥብ ዝቅ ብላ ሁለተኛ ናት። የግማሽ ፍጻሜው ዙር ሁለት ግጥሚያዎች በፊታችን አርብ ይካሄዳሉ፤ የፍጻሜው ጨዋታ የሚደረገው ደግሞ በመጪው ዕሑድ ዛግሬብ ላይ ነው።

አትሌቲክስ

ትናንት ኦሣካ ላይ ተካሂዶ በነበረ ዓለምአቀፍ የሴቶች ማራቶን ሩጫ ጃፓናዊቱ ዮኮ ሺቡኢ ከግቧ ለመድረስ አሥር ኪሎሜትር ሲቀራት ተፎካካሪዎቿን ጥላ በመሄድ ግሩም በሆነ የ 2 ሰዓት ከ 23 ደቂቃ፤ 42 ሤኮንድ ጊዜ አሸናፊ ሆናለች። ሺቡኢ በዚሁ ድሏ በፊታችን ነሐሴ ወር በርሊን ላይ በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመሳተፍ በብሄራዊ ቡድኗ ውስጥ ቦታዋን ስታረጋግጥ የኦሣካን ማራቶን ስታሸንፍ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። ሁለተኛና ሶሥተኛ የወጡትም ጃፓናውያን ናቸው። ዩኪኮ አካባ ሁለተኛ ስትሆን የ 2007 ሻምፒዮን የነበረችው ዩሚኮ ሃራ ሩጫውን በሶሥተኝነት ፈጽማለች። የሢድኒይ ኦሎምፒክ የብር ሜዳይ ተሸላሚ የነበረችው ሩሜኒያዊት ሊዲያ ሢሞን ደግሞ አራተኛ ሆናለች። ከኢትዮጵያ ወርቅነሽ ቶላ 12ኛ!

በዚህ በጀርመን የአገሪቱ የ 800 ሜትር ሩጫ ሻምፒዮን የሬኔ ሄርምስ ድንገተኛ አሟሟት የተፈጥሮ እንጂ አንዳንዶች እነጠረጠሩት በአጎልባች መድሃኒት መውሰድ የተነሣ እንዳልሆነ በጉዳዩ በተካሄደ ምርመራ ለማረጋገጥ ተችሏል። ሄርምስ በቤቱ ሞቶ የተገኘው ከሁለት ሣምንት በፊት ነበር። አንድ የምሥራቃዊቱ ከተማ የድሬስደን ፍርድቤት በሣምንቱ መጨረሻ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው የ 26 ዓመቱ አትሌት የሞተው በተህዋስ መለከፍ ባስከተለው የልብ ድካም ነው። ሬኔ ሄርምስ በአጭር የስፖርት ዕድሜው ከሃያና ከ 23 ዓመት በታች ወጣቶች የ 800 ሜትር የአውሮፓ ሻምፒዮን ለመሆን በቅቷል። በ 2004 የአቴን ኦሎምፒክም አገሩን ወክሎ በመወዳደር እስከ ግማሽ ፍጻሜ ሲደርስ ጀርመን ለወደፊት ብዙ ተሥፋ የጣለችበት የመሃከለኛ ርቀት ሯጭ ነበር።

ከአሳዛኙ ወደ በጎው የአትሌቲክስ ዜና ሻገር እንበልና ሕዝባዊት ቻይና ያለፈውን የቤይጂንግ ኦሎምፒክ ዓመት 2008 ድንቅ አትሌቶቿን መርጣ ሸልማለች። ምንም እንኳ በእግር ሕመም ችግር ምክንያት በቤይጂንጉ ኦሎምፒክ ባይሳተፍም የአገሪቱ የ 110 ሜትር መሰናክል ሩጫ ኮከብ ሊዩ ሺያንግ ለዚህ ክብር ከበቁት 157 ቀደምት አትሌቶች መካከል አንዱ ነው። የተወዳጁ አትሌት አሰልጣኝ ሱን ሃይፒንግም ከሌሎች መሰሎቻቸው ጋር ለሥራቸው ዕውቅና በማግኘት ተሸልመዋል። የአቴኑ ኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሊዩ ይሁንና አሠልጣኑ እንደጠቀሱት በፊታችን ነሕሴ በርሊን ላይ በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና መሳተፍ መቻሉ አጠያያቂ ነው።

እግር ኳስ

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በመጪው 2010 ዓ.ም. የሚካሄደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ከዛሬ ጀምሮ 500 ቀናት ይቀሩታል። ይህም በተለይ ዝግጅቱ ምን ደረሰ? ጥያቄን መልሶ የሚያስነሣ ነው። የደቡብ አፍሪቃ የዝግጅት ብቃት በዓለም እግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር በፊፋ ፕሬዚደንት በዮዜፍ ብላተር ታላቅ ዓመኔታን ማግኘቱ ጥርጣሬ ያላቸውን ሁሉ ዝም እያሰኝ መሄዱ አልቀረም። ብላተር ትናንት በፊፋ ድህረ-ገጽ ላይ በወጣ ቃለ-ምልልስ “በ 500 ቀናት ውስጥ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የዓለም ዋንጫ ውድድር የሚጀምር በመሆኑ እጅግ ደስ ይለኛል፤ ታሪካዊ እንደሚሆንም አልጠራጠርም” ብለዋል።

ደቡብ አፍሪቃ በወቅቱ ቢቀር በስታዲዮም ግንቢያው ረገድ ከሞላ-ጎደል የተጣለውን ጊዜ ተከትላ እየተራመደች ነው። አምሥት አዳዲስ ስታዲዮሞች በመገንባቱና ሌሎች ያሉ አምሥት ስታዲዮሞችን በማሻሻሉ ረገድ ዕርምጃው ከ 2007 የሠራተኞች ዓድማና ሌሎች መሰናክሎች ወዲህ ተሥፋ ሰጭ እየሆነ ተራምዷል። አሁንም አከራካሪ ሆኖ የቀጠለው የትራንስፖርቱ ዘርፍ ግንቢያና ወንጀልን የመቆጣጠሩ ዝግጅት ሂደት ነው። ግን ይህ ፊፋን ብዙ ያወከ አይመስልም። “በአፍሪቃውያን የዝግጅት ብቃት ላይ ዕምነት ሊኖረን ይገባል። ዓመኔታው በራስ መተማመንን የሚያዳብር ነው”ብለዋል የፊፋው ፕሬዚደንት!

የፊፋው ፕሬዚደንት ዮዜፍ ብላተር ለአፍሪቃ ያላቸው ውዳሤ ዝግጅቱን ጠልፎ ለመውሰድ በተጠንቀቅ ለመቆም የቃጣቸውን አንዳንድ አገሮች ዕርም ሳያሰኝ የቀረ አይመስልም። “አፍሪቃ ለእግር ኳሱ ዓለም የሰጠችው ብዙ ነው። በርካታ ተሰጥኦ ያላቸው ተጫዋቾችን፣ አሰልጣኞችን፤ ክለቦችንና ብሄራዊ ቡድኖችን ለግሳለች። በመሆኑም አንድ ቀን የዓለም ዋንጫን ማዘጋጀት መቻሏ ፍትሃዊ ነው። አሁን ጊዜው የደቡብ አፍሪቃ ነው” በማለት ቁርጥ ያለ ቃል ተናግረዋል። በሌላ በኩል የዓለም እግር ኳስ ማሕበር የወቅቱ የፊናንስ ቀውስ ተጨምሮ ምናልባት በውድድሩ ብዙ ትርፍ አያገኝ እንደሆን እንጂ ታላቁን ውድድር ወደ አፍሪቃ ክፍለ-ዓለም በማሻገሩ ብቻ ከወዲሁ ታሪክ እንደሠራ አንድና ሁለት የለውም። ደቡብ አፍሪቃም የርሷንና የክፍለ-ዓለሚቱን የዝግጅት ብቃት አጠያያቂ ያደረጉትን ሁሉ ውድድሩ ከ 500 ቀናት በኋላ ሲከፈት ኩም እንደምታደርግ ቢቀር የብዙ አፍሪቃውያን ተሥፋ ነው።

በአፍሪቃ የሣምንቱ አሳዛኝ ዜና ናይጄሪያ ውስጥ የአንድ እግር ኳስ ክለብ 15ተጫዋቾች በተሽከርካሪ አደጋ ሕይወታቸውን ማጣታቸው ነው። የሰሜን-ምሥራቃዊቱ አዳማዋ ክፍለ-ሐገር ቡድን ለግጥሚያ ወደ ዋና ከተማይቱ ወደ አቡጃ በማምራት ላይ ነበር። ባለፈው ወር በዚሁ ኮረብታማ መንገድ ላይ የአንድ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ዘጠኝ ተጫዋቾች ከነሁለት አሰልጣኞቻቸው በተመሳሳይ ሁኔታ ሕይወታቸውን አጥተው ነበር። የተሽከርካሪዎች በአግባብ አለመጠገንና የሾፌሮች የብቃት ጉድለትም ለአደጋው አስተዋጽኦ ሳይኖራቸው አልቀረም። ያሳዝናል፤ የናይጄሪያ እግር ኳስ ፌደሬሺን ሁኔታውን በማጤን ለተሻለ ዘዴ መጣሩ ግድ ነው የሚሆነው።

በዚህ በአውሮፓ የጀርመን ቡንደስሊጋ ከክረምት እረፍቱ ሊመለስ በዋዜማው ላይ ሲሆን በተቀሩት ቀደምት ሊጋዎች ውስጥ በዚህ ሰንበትም ግሩም ግጥሚያዎች ተካሂደዋል። በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ባርሤሎና በዚህ ሣምንትም በኑማንሢያ ላይ አስተማማኝ 4-1 ድል ሲጎናጸፍ የ 12 ነጥብ አመራሩን እንዳስከበረ ነው። ከአራት ሁለቱን ጎሎች ያስቆጠረው የአርጄንቲናው ኮከብ ሊዮኔል ሜሢ ነበር። ሬያል ማድሪድ ሁለተኛ፤ ሤቪያ ሶሥተኛ በመሆን ይከተላሉ።

በኢጣሊያ ሤሪያ.አ. ሰንበቱ የአንዴው የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን አምበል ዴቪድ ቤክሃም ለኤ.ሢ.ሚላን የመጀመሪያ የሊጋ ጎሉን ያስቆጠረበት ሆኖ አልፏል። ሚላን ቦሎኛን 4-1 ሲረታ ሁለቱን ጎሎች ያስገባው ደግሞ ብራዚላዊው ካካ ነው። ሻምፒዮኑ ኢንተር ሚላን ሣምፕዶሪያን 1-0 በመርታት በሶሥት ነጥብ ይመራል። ጁቬን’ቱስ ሁለተኛ፤ ኤ.ሢ.ሚላን ሶሥተኛ!

በእንግሊዝና በፈረንሣይ ደግሞ ሣምንቱ የፌደሬሺን ዋንጫ ጥሎ-ማለፍ ግጥሚያዎች የተካሄዱበት ነበር። ያለፈው ዓመት ሻምፖዮን ፖርትማውዝ በሁለተኛው ዲቪዚዮን ቡድን በስዋንሢ 2-0 ተሸንፎ ሲሰናበት የፕሬሚየር ሊጉ ቀደምት ክለቦች ቼልሢይ ኢፕስዊችን 3-1፤ እ’ንዲሁም ማንቼስተር ዩናይትድ ቶተንሃምን 2-1 በማሽነፍ ወደ ተከታዩ ዙር አልፈዋል። በተረፈ አርሰናል ከካርዲፍ ባዶ-ለባዶ፤ ሊቨርፑል ከኤቨርተን 1-1፤ ኤስተን ቪላም ከሮቨርስ 0-0 ተለያይተዋል።

በፈረንሣይ የፌደሬሺን ዋንጫ ውድድር ከአንድ በስተቀር የሁለተኛ ዲቪዚዮን ቡድን ታላላቆቹን የደፈረበት ሁኔታ አልነበረም። ሞናኮ ወደ ተከታዩ ዙር ማለፉን ሲያረጋግጥ ያለፈው ሻምፒዮን ኦላምፒክ ሊዮን፤ ፓሪስ-ሣን-ዠርሜን፤ ማርሤይና ሌሎች ቀደምት ቡድኖችም ሰንበቱን በድል አሳልፈዋል። በመጨረሻዎቹ 16 ክለቦች መካከል የሚካሄደው ተከታዩ ውድድር ምናልባት አስደናቂ ውጤቶች የሚታዩበት ይሆናል።

በኔዘርላንድ ሻምፒዮና አልክማር በቅርብ ተፎካካሪው በአያክስ አምስተርዳም መሽነፍ አመራሩን ወደ ስድሥት ነጥቦች ከፍ ለማድረግ ሲበቃ በፓርቱጋል ሻምፒዮናም ፖርቶ ሁለቱ የሊዝበን ቡድኖች ቤንፊካና ስፖርቲንግ በእኩል ለእኩል ውጤት በመወሰናቸው አልፏቸው አመራሩን በአንዲት ነጥብ ብልጫ ለመያዝ ችሏል። የጀርመን ቡንደስሊጋ ነገና ከነገ በስቲያ የፌደሺን ዋንጫ ግጥሚያዎች ከተካሄዱ በኋላ ከእረፍት መልስ ሁለተኛ ዙር የሊጋ ውድድሩን አርብ ይጀምራል።

ሜልበርን ላይ በሚካሄደው አውስትራሊያን-ኦፕን የቴኒስ ውድድር የስፓኙ ከኮብ ራፋኤል ናዳል፣ የስዊሱ ሮጀር ፌደረር፣ አሜሪካዊቱ ሤሬና ዊሊያምስና ሩሢያዊቱን ስቬትላና ኩዝኔትሶቫን የመሳሰሉት ቀደምት ተጫዋቾች ግጥሚያቸውን በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍጻሜው ሲያልፉ ጉዞው ለአንዳንድ ጠንካራ ተጫዋቾች አጭር መሆኑም አልቀረም። በውድድሩ ዋዜማ ታላቅ ተሥፋ ከተጣለባቸው መካከል በዓለም የቴኒስ ማዕረግ ተዋረድ ላይ አራተኛው ኤንዲይ መሪይ በስፓኙ ተወላጅ በፌርናንዶ ቫርዳስኮ ተሸንፎ ከወዲሁ መሰናበቱ ግድ ሆኖበታል።

ተዛማጅ ዘገባዎች