ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 24.11.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በአውሮፓ ቀደምት አንደኛ ዲቪዚዮን ክለቦች ውስጥ በርካታ ማራኪ ግጥሚያዎች ተካሂደው ነበር። በአትሌቲክሱ ዓለም የዓመቱ ድንቅ አትሌቶች በመባል የተመረጡት ስፖርተኞች ሲሽለሙ በአዲስ አባባም ታላቁ ሩጫ ብዙም ባልታወቀ ወጣት አትሌት አሸናፊነት ተፈጽሟል።

የባየርን አጥቂ ሉካ ቶኒ

የባየርን አጥቂ ሉካ ቶኒ

በአውሮፓ አንደኛ ዲቪዚዮን ክለቦች ውድድር እንጀምርና በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ኢንተር ሚላን ጁቬንቱስን 1-0 በመርታት የሊጋ አመራሩን በሶሥት ነጥብ ልዩነት ለማስፋት በቅቷል። ይህ የሆነው የቅርብ ተፎካካሪው ኤ.ሢ.ሚላን ከቶሪኖ ጋር እኩል ለእኩል ብቻ በመለያየቱ ነው። ለኢንተር ብችኛዋን ጥቃሚ ጎል ያስቆጠረው የጋናው የመሃል ሜዳ ተጫዋች ሣሊይ ሙንታሪ ነበር። ኤ.ሢ.ሚላን በ 27 ነጥቦች ሁለተኛ ሲሆን ጁቬንቱስና ናፖሊ እኩል 24 ነጥብ ይዘው ይከተላሉ። በዘንድሮው ውድድር በደታች ያቆለቆለው ሮማ ደግሞ ሌቼን በማሽነፍ ወደ 15ኛው ቦታ ከፍ ለማለት ችሏል።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን የቪላርሬያል የመጀመሪያ ሽንፈት ላለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን ለሬያል ማድሪድ በጣሙን ነው የበጀው። ቪላርሬያል በሬያል ቫላዶሊድ 3-0 ሲረታ ሬያል ማድሪድ ሁዌልቫን 1-0 ማሽነፉ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለተኛውን ቦታ እንዲይዝ አብቅቶታል። የሬያል ድል የመባረር አደጋ ለተደቀነበት ጀርመናዊ አሠልጣኙ ለበርንድ ሹስተርም ለጊዜውም ቢሆን ዕፎይታ ነው የሆነው። በሌላ በኩል ኤፍ.ሢ.ባርሤሎና ምንም እንኳ ከጌታፌ 1-1 ቢለያይም በሶሥት ነጥብ ልዩነት፤ ማለትም በ 29 ነጥቦች መምራቱን እንደቀጠለ ነው። ሁለተኛው ሬያል ማድሪድ 26 ነጥቦች ሲኖሩት ወደታች የተንሸራተተው ቪላርሬያል አንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ሶሥተኛ ነው። በሰንበቱ ግጥሚያ ባዶ-ለባዶ የተለያዩት ቫሌንሢያና ሤቪያ ደግሞ በእኩል 24 ነጥብ ይከተላሉ።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሰንበቱ ከቀደምቱ አራት ክለቦች አንዱም ያሽነፈበት አልነበረም። ቼልሢይ-ኒውካስል ዩናይትድ፤ ሊቨርፑል-ፉልሃም፤ ማንቼስተር ዩናይትድ ኤስተን ቪላ፤ በሙሉ ተመካክረው ሜዳ የገቡ ይመስል ባዶ-ለባዶ ነው የተለያዩት። በዚሁ ውጤት የተነሣም ያለፈው ሣምንት አሰላለፍ ሳይለወጥ ባለበት ቀጥሏል። ቼልሢይና ሊቨርፑል እኩል 33 ነጥቦች ይዘው በሰፊ ልዩነት ይመራሉ፤ ማንቼስተር ዩናይትድ ስምንት ነጥቦች ወረድ ብሎ በ 25 ነጥቦች ሶሥተኛ ሲሆን ኤስተን ቪላ በ 24 ነጥብ አራተኛ ነው። የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በአጭር ጊዜ ስሌት የሁለት ክለቦች የበላይነት የሰፈነበት ሆኖ የሚቀጥል ነው የሚመስለው።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ሳይታሰብ ቁንጮ የሆነው የመንደር ክለብ ሆፈንሃይም ከቅዳሜ-ቅዳሜ እያየለ መሄዱን ቀጥሏል። ቡድኑ ኮሎኝን 3-1 በመርታት የሊጋውን አመራር ለብቻው ሲይዝ ጥንካሬው በአጨዋወት ስክነት እንጂ በአጋጣሚ እንዳልሆነ ለተፎካካሪዎቹ ይበልጥ ግልጽ እየሆነ ነው። በተለይ የቦስና አጥቂው ቬዳድ ኢቢዜቪች በ 14ኛ ጨዋታው 16ኛ ጎሉን በማስቆጠር ሊጋውን በአስተማማኝ ሁኔታ እየመራ ሲሆን በቀላሉ የሚያቆመው ተከላካይ አልተገኝም። እንደ አሠልጣኙ እንደ ራልፍ ራንግኒክ ዕምነት ለቡድኑ ስኬት ሚስጥሩ ከልብ የመነጨ አጨዋወቱ ነው።

“ዛሬ ዘጠናውን ደቂቃ ሙሉ ከልብ በመነጨ ስሜት ነው የተጫወትነው። ወሣኝ በሆኑ የጨዋታው ሂደቶች ላይ አስፈላጊው የአዕምሮ ብቃትም ነበረን። በዚሀ የክረምቱ የሜዳ ሁኔታ ተጫዋቾቹ ያሳዩት ቅልጥፍና ሊደነቅ የሚገባው ነው። ከዚህ የበለጠ ጨዋታ ለዚያውም በውጭ ሜዳ ለማሳየት አይቻልም”
በዚሁ ስኬትም ሆፈንሃይም እስካለፈው ሣምንት ይመራ የነበረው ሌቨርኩስን በቢለፌልድ በመሽነፉ አመራሩን በ 31 ነጥቦች ለብቻው ለመያዝ በቅቷል። የሰንበቱ ተጠቃሚ በጥቂት ሣምንታት ውስጥ ወደ ሶሥተኛው ቦታ ያሻቀበው ሻምፒዮን ባየርን ሙንሺንም ነበር። ኮትቡስን 4-1 በመሸኘት ከሁለተኛው ከሌቭርኩዝን ጋር እኩል ነጥቦች በመያዝ አመራሩን እየተቃረበ ነው። አሠልጣኙ ዩርገን ክሊንስማን እንደሚያስበው ከሆነ ባየርን አመራሩን የሚጨብጥበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።

“ቀስ በቀስ ከገናው በዓል በፊት ልንደርስበት ካቀድነው ግብ እየተቃረብን ነው። የበልጉ፤ ማለትም የመጀመሪያው ዙር ሻምፒዮን ለመሆን እንፈልጋለን። ለዚህም አስፈላጊውን ጥረት እያደረግን ነው። ከሆፈንሃይም ጋር በሜዳችን የምንጋጠም ሲሆን ከዚያ በኋላ በታሕሣስ አጋማሽ ላይ የሚሆነውን በጉጉት ነው የምጠብቀው”

በዕውነትም ባየርን ሙንሺን በበልግ ሻምፒዮንነቱ አቅጣጫ የሚያመራ የሚሄድ ነው የሚመስለው። በተረፈ ቬርደር ብሬመን በሃምቡርግ 2-1 ሲሸነፍ ሽቱትጋርት ደግሞ በቮልፍስቡርግ 4-1 ተረትቶ ወደ 11ኛ ቦታ ከተንሸራተተ በኋላ አሠልጣኙን አሰናብቷል።

በተረፈ በፈረንሣይ ሊጋ ኦላምፒክ ሊዮን በዘንድሮው የውድድር ወቅት ለሁለተኛ ጊዜ ቢሽነፍም በአመራሩ እንደቀጠለ ነው። ሆኖም በፓሪስ ሣን ዣርማን በደረሰበት 1-0 ሽንፈት የሰባት ነጥብ ልዩነቱ ወደ አምሥት ጠበብ ብሏል። ሁለተኛው ሣንት ኤቲየንን የረታው ኒስ ነው። ከሊል 2-2 የተለያየው ኦላምፒክ ማርሤይ ደግሞ በሶሥተኝነት ይከተላል። በኔዘርላንድ ሻምፒዮና አልክማር አያክስ አምስተርዳምን 2-0 በማሸነፍ አመራሩን ሲነጥቅ በፖርቱጋል ሊጋ ሌክሶስ ከቤንፊካ ሊዝበን አንድ ነጥብ ላቅ ብሎ መምራቱን እንደቀጠለ ነው። የቀደምቱ የአውሮፓ ሊጋዎች ሻምፒዮና ሁኔታ በወቅቱ ከሞላ-ጎደል ይህን ይመስላል።

አትሌቲክስ

የዓለም አትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር የቤይጂንጉን ኦሎምፒክ የሶሥት ወርቅ ሜዳሊያ ተሽላሚ ጃማይካዊ ኡሤይን ቦልትንና ሩሢያዊቱን የምርኩዝ ዝላይ ሻምፒዮን የለና ኢዚንባየቫን ትናንት ሞናኮ ላይ የዓመቱ ድንቅ አትሌቶች ብሎ ሰይሟል። ኡሤይን ቦልት በመቶ፣ ሁለት መቶና በአራት ጊዜ አንድ መቶ ሜትር የዶላ ቅብብል ማሽነፍ ብቻ ሣይሆን በሁሉም አዲስ የዓለም ክብረ-ወሰን ማስመዝገቡም የሚታወስ ነው። የማሕበሩ ፕሬዚደንት ላሚን ዲያክ በአድናቆት “የማይረታ” ብለውታል። ከዚሁ ሌላ የኩባው የ 110 ሜትር መሰናክል የዓለም ክብረ-ወሰን ባለቤት ዳይሮን ሮብልስ፣ ጥሩነሽ ዲባባና የቼኳ ባርባራ ስፖታኮቫ ደግሞ በዓመቱ ላሣዩት ድንቅ ውድድር ተሽላሚ ሆነዋል።

ኡሤይን ቦልትና ጥሩነሽ ዲባባ ልዩ የኦሎምፒክ ሽልማት ከተቀበሉት ስድሥት አትሌቶች መካከልም ይገኙበት ነበር። በተረፈ ዓለምአቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ከ 2010 ዓ.ም. ጀምሮ የአትሌቲክሱን ጎልደን-ሊግ ውድድር ከስድሥት ወደ አሥራ ሁለት በእጥፍ ለማስፋት ወስኗል። ሌላው የትናንቱ ዓቢይ የአትሌቲክስ ትዕይንት አዲስ አባባ ላይ የተካሄደው ዓመታዊው ታላቁ ሩጫ ነበር። በውድድሩ 32 ሺህ ሰዎች ሲሳተፉ በወንዶች ሩጫውን ያሸነፈው እስከ ትናንት ብዙም ያልታወቀው ወጣት አትሌት ጫላ ደቻሣ ነው።
የ 22 ዓመቱ ወጣት አትሌት አሥሩን ኪሎሜትር በ 28 ደቂቃ ከ 55 ሤኮንድ ሲያቁዋርጥ ለድል የበቃው ያሸንፋል ተብሎ የተጠበቀውን የ 2006 ክብረ-ወሰን ባለቤት ደሪባ መርጋን ከኋላው በማስቀረት ነው። ሃይሌ ገ/ሥላሴ ለወጣቱ አትሌት አድናቆቱን በመግለጽ የወደፊት ዕድሉ የቀና እንደሚሆን ተንብዮለታል። በሴቶች አንደኛ የወጣችው ደግሞ የሃያ ዓመቷ ወጣት ውዴ አያሌው ነበረች። በሌላ በኩል የሽብርተኞች ጥቃት ይደርሳል ሲል ተናፍሶ የነበረው ወሬ ይመስገነው ወሬ ብቻ ሆኖ ቀርቷል።

በተረፈ ኢጣሊያ ውስጥ በተካሄደ የሚላን ማራቶን ኬንያውያን ከአንድ እስከ ሶሥት ተከታትሎ በመግባት የተሟላ ድል ለመጎናጸፍ በቅተዋል። ሩጫውን በ 2 ሰዓት ከ 7ደቂቃ ከ 53 ሤኮንድ በመፈጸም ያሸነፈው ኪቤት ኪሮንግ ነው። የቅርብ ተፎካካሪዎቹ ኤሊያስ ቺሞ ሁለተኛ ሲወጣ በሶሥተኝነት ተከትሎት የገባው ደግሞ ሊዮናርድ ማይና ነበር።

ቴኒስ

የስፓኝ የቴኒስ ኮከቦች ትናንት የማይቻል መስሎ የታየውን የዴቪስ ካፕ ፍጻሜ ውድድር በማሸነፍ ከአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫና ከቢስክሌት ሻምፒዮንነት በተጨማሪ ለአገሪቱ ታሪካዊ የሆነውን ዓመት በስኬት አጠቃለዋል። ከአርጄንቲና ጋር የተካሄደው ፍጻሜ ግጥሚያ የለየለት ፌርናንዶ ቫርዳስኮ የአርጄንቲና ተጋጣሚውን አምሥት ምድብ ድረስ በሄደው የመጨረሻ ጨዋታ በአስደናቂ ሁኔታ ካሸነፈ በኋላ ነበር። ስፓኝ የዴቪስ ካፕ አሸናፊ ስትሆን ለሶሥተኛ ጊዜ ሲሆን አርጄንቲና በአንጻሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን የነበራት ዕድል ከንቱ ሆኖ ቀርቷል። በውድድሩ ያልተሳተፈው ቀደምት የስፓኝ ኮከብ ራፋዔል ናዳል ድሉን “የማይረሣ” ነው ያለው።

ዘገባችንን በእግር ኳስ ለማጠቃለል የብራዚል ሻምፒዮና ሊጠናቀቅ ሁለት ግጥሚያዎች ብቻ ቀርተው ሳለ ዘንድሮ ሣኦ ፓውሎ ለድል የተቃረበ እየመሰለ ነው። ክለቡ ትናንት በቫስኮ-ዳ-ጋማ ስታዲዮም ጥሩ አቀባበል ባይደረግለትም በጨዋታው 2-1በመርታት አመራሩን በአምሥት ነጥቦች ልዩነት አስፍቷል። ቡድኑን ለዚህ ያበቃው የሁለተኛው ክለብ የግሬሚዮ መሽነፍ ነው። ሣኦ ፓውሎ በተከታታይ ለሶሥተኛ ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን አንዴ ማሽነፍና አንዴ እኩል ለእኩል መውጣት ሊበቃውም ይ’ችላል። ሶሥተኛ ክሩዜሮ፤ አራተኛ ፓልሜይራስ ሲሆን የሚያሳዝን ሆኖ የአንዴው ዝነኛ የፔሌ ክለብ ሣንቶስ 14ኛ ነው።

በተረፈ በዚህ በአውሮፓ ነገና ከነገ ወዲያ በስምንት ምድቦች ተከፍሎ የሚደረገው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ቀጣይ ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። ብዙዎቹ ግጥሚያዎች 16 ክለቦች ብቻ ወደሚቀሩበት ወደ ተከታዩ ዙር ለማለፍ ወሣኝነት አላቸው። ተመልካቾችን ይበልጥ ከሚማርኩት ታላላቅ ግጥሚያዎች መካከል ቪላርሬያል-ማንቼስተር ዩናይትድ፤ ዢሮንዲን ቦርዶ-ኤፍ.ሢ.ቼልሢይ፤ አትሌቲኮ ማድሪድ-አይንድሆፈን፤ እንዲሁም አርሰናል ለንደን-ዲናሞ ኪየቭ፤ ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው።