ሣልሞኔላ-ካንሰር ተፋላሚው ባክቴሪያ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 08.07.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ሣልሞኔላ-ካንሰር ተፋላሚው ባክቴሪያ

ካንሰርን በባክቴሪያ ለመዋጋት ከተሳካም ለማስወገድ እዚህ ጀርመን ሀገር ቤተ-ሙከራ ውስጥ እንስሳት ላይ ምርምር እየተደረገ ነው። በካንሰር የተነሳ በዓለማችን በሚሊዮናት የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ካንሰር ኢትዮጵያን ጨምሮ በታዳጊ ሃገራት እጅግ እየተስፋፋ በመምጣት ላይ ይገኛል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:00
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:00 ደቂቃ

ሣልሞኔላ-ካንሰር ተፋላሚው ባክቴሪያ

ከ8,2 ሚሊዮን በላይ የዓለማችን ነዋሪዎች እንደ ጎርጎሪዮሣዊው አቆጣጠር በ2012 ዓ.ም. በካንሰር የተነሳ ሕይወታቸውን እንዳጡ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO)የቅርብ ዘገባ ይገልጣል። በሚቀጥሉት ኹለት ዐሥርተ ዓመት በካንሰር የተነሳ የሟቾች ቁጥር አሁን ካለው መጠን በ70 በመቶ እንደሚጨምር ድርጅቱ ገምቷል። ይኽን በዓለማችን የሰው ዘር ላይ ከባድ ጋሬጣ የፈጠረ ችግር ለመዋጋት ጀርመን ውስጥ የቤተ-ሙከራ ምርምር እየተደረገ ነው። እንደ ሳይንቲስቶቹ ገለጣ ከሆነ ሣልሞኔላ የተሰኘው በሽታ አማጪ ባክቴሪያን እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ በመርፌ ወደ አይጦች ገላ በማስረግ ከካንሰር ነፃ እንዲሆኑ ማስቻሉን ይፋ አድርገዋል። ምርምሩ ገና በሰዎች ላይ እንዳልተሞከረም ተጠቅሷል።

ሣልሞኔላ ባክቴሪያ ምርምር ሲደረግበት

ሣልሞኔላ ባክቴሪያ ምርምር ሲደረግበትካንሰር የሰው ልጆችን እጅግ አጣብቂኝ ውስጥ ከከተቱ የዘመናችን ፈተናዎች አንዱ ነው። በምድር ላይ ካንሰርን በአጠቃላይ ለመፈወስ የሚያስችል መድኃኒት እስካሁን አልተፈለሰመም። ይልቁንስ በካንሰር የተነሳ ለኅመም የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር ከዓመት ዓመት እያሻቀበ ነው። ካንሰር ለወትሮው ብዙ በማይታወቅባቸው ኢትዮጵያን ጨምሮ በታዳጊ ሃገራት ውስጥ እየተስፋፋ መሆኑ ይጠቀሳል። ዶ/ር ቦጋለ ሰለሞን ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ የግል የህክምና ተቋም የሚያገለግሉ የካንሰር ባለሙያ ናቸው።

በመላው ዓለም እጅግ በመስፋፋት ላይ የሚገኘውን አሳሳቢውን የካንሰር ችግር ለመዋጋት ሣይንቲስቶች ለዘመናት ያላሰለ ምርምር አከናውነዋል። በአዲስ መልኩ በካንሰር የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ መምጣትም ጠበብት አዲስ አይነት የምርምር ስልት ላይ እንዲያተኩሩ ምክንያት ኾኗል።

ሣልሞኔላ-ካንሰር ተፋላሚው ባክቴሪያ

ሣልሞኔላ ባክቴሪያ በማጉሊያ መነፅር ገዝፎ

ሣልሞኔላ ባክቴሪያ በማጉሊያ መነፅር ገዝፎ

በእርግጥ ሣልሞኔላ የሚታወቀው በበሽታ አማጭ ባክቴሪያነቱ ነው። እንዲያም ሆኖ ግን ከቅርብ ጊዜያት አንስቶ የካንሰር ምርምር ጠበብት የዚህን በሽታ አማጭ፥ አደገኛ ባካቴሪያ፥ የገዳይነት ጠባይ የካንሰር እባጭን መዋጋያ ለማድረግ በመሞከር ላይ ናቸው። ሐሳቡ በራሱ አዲስ አይደለም፤ ሆኖም የባክቴሪያውን አደገኛነት ለመጀመሪያ ጊዜ በቁጥጥር ስር ማዋል ግን ተችሏል። ዶ/ር ዚግፍሪድ ቫይስ፤ በሔልምሆልትስ የጀርመን የምርምር ማዕከላት የምርቀዛ ጥናት ውስጥ ያገለግላሉ።

«ካንሰርን በባክቴሪያ የመዋጋት ሐሳብ ቆየት ያለ ነው። ሣልሞኔላን የወሰድንበት ምክንያትም ረዘም ላለ ጊዜ ጥናት ስላደረግንበት ነው። የዚህ ባክቴሪያ አጥቂነት ካንሰርን በመዋጋቱ ዘርፍ በእርግጥም ውጤታማነቱን አስመስክሯል።»

ጀርመን ብራውንሽቫይግ ውስጥ በሔልምሆልትስ ማዕከል የሚገኙ ተመራማሪዎች ሣልሞኔላ የተሰኘው ባክቴሪያን ጠባይ በመቀየር፤ ካንሰርን እንዲያጠቃ ማድረግ ችለዋል። በውጤቱም የሰውነት በሽታ ተከላካይ ሴሎች እንዲያንሰራሩ ማስደረግ ተሳክቶላቸዋል።

ይኽ ሂደት ከአደጋ የጸዳ ነው ማለት አይደለም። ካንሰርን ኃይለኛ በሆነው የሣልሞኔላ ባክቴሪያ ለማከም መጣር እጅግ አደገኛ ነው። አደጋው ባስ ሲልም ባክቴሪያው የካንሰር በሽተኛውን ሊገድል ይችላል። ኃይለኛነቱ ለዘብ ካለ የሣልሞኔላ ባክቴሪያ ቤተ-ሙከራ ውስጥ ህክምና የተደረገላቸው አይጦች ጥሩ መሻሻል በማሳየት ሰውነታቸው ውስጥ የነበሩ የካንሰር ዕባጮች ሲከስሙ ተስተውለዋል።

ሣልሞኔላ ባክቴሪያ (ቀዩ)ሴልን ወሮ

ሣልሞኔላ ባክቴሪያ (ቀዩ)ሴልን ወሮ«ባክቴሪያውን እጅግ በምናዳክምበት ጊዜ ኅመም አማጭነቱ ያከትማል። እጅግ ጥንቃቄ በተመላበት ሒደትም በአንድ መልኩ የባክቴሪያው ኃይለኝነት ሳይጠፋ፥ በሌላ መልኩ ለሰውነት አደገኛ መሆኑ እንዲያከትም እናደርጋለን።»

ተመራማሪዎች ዋነኛ የደረሱበት ግኝት ባክቴሪያውን ከርቀት እንደፈለጉ መቆጣጠር መቻላቸው ነው። ያም ማለት የባክቴሪያው መቆጣጠሪያ «ማብሪያ» ላይ የሚያሳይ ከሆነ ባክቴሪያው ኃይለኛነቱ አለ ማለት ነው። መቆጣጠሪያው «ማጥፊያ» ላይ ካመለከተ ደግሞ በሰውነት የበሽታ መከላከያዎች ሊሸነፍ ይችላል ማለት ነው። ይኽ መቆጣጠሪያ የተፈለገበት ዋነኛ ምክንያት ባክቴሪያው ካንሰሩን በሚዋጋበት ወቅት ኃይለኛነቱ እንደተጠበቀ ቆይቶ ግዳጁን ከተወጣ በኋላ በሰውነት የበሽታ መከላከያ ሴሎች መወገድ እንዲችል ነው። ዶ/ር ቦጋለ ሰለሞን ይኽን መሰል እጅግ የረቀቀ ምርምር ከእንስሳት ወደ ሰው ለማሸጋገር ረዥም ጊዜ እንደሚፈጅ ጠቅሰዋል።

የቤተ-ሙከራ አይጥ

የቤተ-ሙከራ አይጥ

በርቀት መቆጣጠሪያው የተዳከመው ሣልሞኔላ የተሰኘው ባክቴሪያ በተለየ የስኳር ንጥር ብቻ ወደ ገዳይነት መሸጋገር እንዲችል ይደረጋል። ባክቴሪያው በመርፌ ወደ ሰውነት እንዲሠራጭ እና ልዩው የስኳር ንጥር እንዲወገድ በተደረገ በጥቂት ሠዓታት ውስጥ ግን ጎጂነቱ በመጥፋት ወደ ደካማ ባክቴሪያነት ይቀየራል። በሔልምሆልትስ ማዕከል ተማራማሪ የሆኑት ዶ/ር ዲኖ ኮቺያንቺች ባክቴሪያው እንዴት ለህክምና አገልግሎት እንደሚውል በዚህ መልኩ ያብራራሉ።

«አይጧን ስንወጋት እና ባክቴሪያውን ወደ ሰውነቷ ስናስገባ ልዩ የስኳር ንጥሩን በማደባለቅ በመሆኑ የባክቴሪያው ተፋላሚነት እና አደገኛነት እንዳለ ይኾናል። ልዩው የስኳር ንጥር በተወገደ ቅጽበት ግን ባክቴሪያው እጅግ ይዳከማል። ባክቴሪያው ላለበት አካልም ጎጂነቱ እጅግ አናሳ ይኾናል። ይኽንን ነው በህክምና ወቅት ተግባራዊ ለማድረግ የምንሞክረው።»

በካንሰር ላይ የሚደርግ ረቂቅ ምርምር በኢትዮጵያ እንደሌለ የተናገሩት ዶ/ር ቦጋለ ለካንሰር አጋላጭ ይኾናሉ ተብለው የሚገመቱ ነገሮች ላይ ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ግን አሳስበዋል።

በቤተ-ሙከራ ምርምር

ቤተ-ሙከራ ምርምር

ቤተ-ሙከራ ምርምር

ሔልምሆልትስ የምርምር ማዕከል ውስጥ የሚገኙ ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ሣልሞኔላ የተሰኘውን ባክቴሪያ አይጥ ውስጥ በመሞከር እመርታ አሳይተዋል። ካንሰር ያለባት አይጥን በጭራዋ በኩል ሣልሞኔላ የተሰኘውን ባክቴሪያ በመርፌ በመውጋት ባክቴሪያው ካንሰሩ ወዳለበት ስፍራ እንዲያቀና ማድረግ የህክምናው ቀዳሚ ተግባር መሆኑን ገልጠዋል። ከዚያም ኃይለኞቹ ባክቴሪያዎች የካንሰር ዕባጭ የፈጠሩትን የተዛቡ ሴሎች በመግደል ይመገቧቸዋል። በካንሰሩ አጠገብ የሚገኙ ሌሎች የሰውነት በሽታ ተከላካዮች ደግሞ የባክቴሪያውን እንቅስቃሴ በማጤን ፈጣን አጸፌታ ያደርጋሉ፤ በዚህም የተጎዳው ሰውነት ከካንሰር ነጻ ይኾናል ማለት ነው።

እንግዲህ በዚህ ስልት ካንሰርን ማከሙ አስተማማኝ ስለመሆኑ ጀርመናውያን ሳይንቲስቶቹ በእርግጠኝነት ተናግረዋል። በእርግጥ ሣልሞኔላ የተሰኘውን እጅግ አደገኛ ባክቴሪያ በመጠቀም ካንሰርን ለማከም በሰዎች ላይ እስካሁን ሙከራ አልተደረገም። ሆኖም ሣልሞኔላ በተሰኘው ባክቴሪያ እና በሰውነት የበሽታ ተከላካይ ሴሎች መካከል የጠባይ ለውጦች እንዲከሰቱ በማድረግ ካንሰርን አዲስ በሆነ መልኩ የመዋጋት እመርታ ግን ታይቷል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic