ሠዓሊዉና ቡሩሹ | ባህል | DW | 05.11.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

ሠዓሊዉና ቡሩሹ

«ሥዕል ለኔ ሰላም የሚሰጠኝ፤ ሃሳብ ሲበዛብኝ፤ የሚያስጨንቁና የሚያሳዝኑ ሁኔታዎች ሲገጥሙኝ፤ ነፃ የምሆንበት መሳርያዬ ነው፤» ይሉናል

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:24
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
15:24 ደቂቃ

ሠዓሊዉና ቡሩሹ

ዛሬ በእንግድነት የምናቀርባቸዉ ሠዓሊ ዳንኤል ጌታሁን። ሠዓሊ ዳንኤል ጌታሁን የሚስሉዋቸዉ ሥዕሎች አብዛኞቹ የኢትዮጵያዉያንን ባህል አኗኗር የሚያንፀባርቁ በመሆናቸዉ በሚኖሩበት በቶሮንቶ ካናዳ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን «ሀገርን አስተዋቂ አንባሳደር» ነዉ የሚልዋቸዉ። ሠዓሊ ዳንኤል በብሩሽና በቀለም ብቻ ሳይሆን የሚስሉት በዲጂታልም እንደሆነ ይናገራሉ። የዲጂታል ሥዕል ስንል ምንድን ነዉ? በዚህ ዝግጅታችን ሠዓሊ ዳንኤል ጌታሁንና ሥዕሎቻቸዉን እንዲሁም ሥዕል በምሥል የሚታሰብ እይታዊ ቋንቋ ነዉ የሚሉንን የሥዕል መምህር በእንግድነት ይዘናል።


የሥነ-ጥበብ ምሁራን ሥዕል የራሱ ቋንቋ አለዉ ይላሉ። ከሦስት አስርተ ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት የተመረቁት ሠዓሊ ዳንኤል ጌታሁን ሥዕሎቻቸዉን በፊስ ቡክ ገፃቸዉ ላይ መለጠፍ ከጀመሩ ጊዜ አንስቶ ሥራዎቻቸዉ በርካታ አድናቂዎችን አትርፈዋል።

አቶ ዳንኤል ከሰላሳ ዓመታት በፊት አዲስ አበባ በሚገኘዉ የሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት መመረቃቸዉን ይናገራሉ።«ከአዲስ አበባ የሥነ-ጥበብ ት/ቤት የተመረኩት በጎርጎረሳዊ 1980 ዓ,ም ነዉ። ከዝያ በኋላ ካናዳ ነዉ የኖርኩት፤ አሁንም እዝያዉ ነዉ የምኖረዉ። ብዙ ጊዜ ሥራዎቼ የዘይት ቅብና፤ በዲጂታል በኮንፒዉተር የተሳሉ ናቸዉ። ሥራዎቼ በአጠቃላይ የሚያተኩሩት በኢትዮጵያ ባህላዊ ነክ ጉዳዮች ላይ ብቻ ነዉ።»ለምንድን ነዉ ባህላዊ ነክ ነገሮች ብቻ ላይ የሚንፀባርቁ ስዕሎችን ለእይታ የሚያቀርቡት?
« ብዙ ጊዜ መሥራት የምወደዉ ባህሌን ነዉ። ኢትዮጵያዊ መሆን አለበት ነዉ የኔ ፍልስፍና። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ እስከሆንኩ ያለዉን አካባቢዬንና ራሴን ነዉ መግለጽ የምችለዉ፤ ኢትዮጵያዊነቴንና የኢትዮጵያን ባህል ብቻ። ሁሉም ሠዓሊ እኮ የየሀገሩን የራሱን አካባቢ ነዉ በሥዕል የሚገልጸዉ። አሜሪካም፤ ቻይናም ጀርመንም ብንሄድ ሰዓሊዎች በአብዛኛዉ የሚሥሉት የራሳቸዉን ባህል ነዉ፤ ማስተዋወቅ የሚፈልጉትም የራሳቸዉን ነገር ነዉ። እኔም ልክ እንደዛ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያ ባህልን ነዉ የምሥለዉ፤ ያደኩት ከልጅነቴ ጀምሮ የማዉቀዉ የኖርኩበት በመሆኑ፤ ይህንን ባህሌን ነዉ መሣል የምወደዉ፤ ያስደስተኛልም። »

ሠዓሊ ዳንኤል አሁን በቶሮንቶ ካናዳ መተዳደርያዎ ሥዕል ነዉ ማለት ነዉ?


« አይ፤ አይደለም። ከኢትዮጵያ ከወጣሁ በኋላ ሥዕል መሣል አቁሜ ነበር። አሁን አሁን ነዉ ሥዕልን መሥራት የጀመርኩት። እጅግ የምታወቅ ሰዉ አይደለሁም፤ በአጋጣሚ አሁን በፊስ ቡክ ላይ የሳልኩዋቸዉን ሥዕሎች መለጠፍ ከጀመርኩ ወዲህ ቶሎ ቶሎ መሣል ጀምሪአለሁ ። ሰዎች እቤቴ ድረስ እየመጡ ይገዙኛልና ያንን እየሰራሁ ነዉ። በትርፍ ጊዜዬ።»

አዲስ አበባ ተወልደዉ ያደጉት ሠዓሊ ዳንኤል ጌታሁን ሥዕል የመሣል ፍላጎታቸዉ የጀመረዉ ገና በሕጻንነት እድሜአቸዉ እንደነበር ይናገራሉ። ስምንተኛ ክፍልም ሳሉ ከትምህርት ቤታቸዉ ሽልማት እደተቀበሉ ያስታዉሳሉ፤ ከዝያም ነዉ ተሰጥኦአቸዉን ለማሳደግ አዲስ አበባ የሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት የገቡት።« ከልጅነቴ ጀምሮ ነዉ 8 ዓመት ልጅ እያለሁ ደብተሪ በሙሉ በሥዕል ነበር የሚያልቀዉ። መሥራት፤ መሳል እወድ ነበር። ደብተሪ ላይ ክፍል ዉስጥም እንዲሁ። የኔ ደብተር በጣም ንጹሕና በጣም የሚያምር ነበር። ከዉስጥ በላስቲክ እሸፍነዋለሁ ፤ ተራራ ጎጆ ቤትቶች እየሠራሁ አሸበርቀዉ ነበር። ስምንተኛ ክፍል እያለሁ ሽልማት በዓመቱ መጨረሻ ላይ አግንቻለሁ። ከዝያ የሥዕል ስሜቱ አደረብኝና በኋላ ወደ ሥዕል ት/ቤት ገባሁ። ይህ በጎርጎረሳዊ 1976 ዓ,ም መሆኑ ነዉ። ትምህርቱን አጠናቅቄ ከተመረኩ በኋላ አስኮ አዲስ አበባ በሚገኘዉ ጫማ ፋብሪካ የጫማ ፋሽን ሥራ ዘርፍ ተቀጥሪ እሠራ ነበር። ከዝያ ነዉ ወደ ጣልያን ሀገር ለትምህርት የተላኩ። በደረግ ዘመነ መንግሥት ወደ ሀገር ቤት መመለስ ባለመፈለጌ ወደ እዚህ መጣሁ

ማለት ነዉ፤ ወደ ካናዳ። እዚህ ከመጣሁ በኋላ ሥዕል ሥዬ አላዉቅም፤ ምክንያቱም በሥዕል መተዳደር ከባድ ነዉ፤ ታዋቂ ሰዉ ካልሆኑ በቀር። ግን ቢሆንም ሥዕልን ስለምወድ አሁን በትርፍ ጊዜዬ መሥራት ጀምሪአለሁ። በተለይ እንዲህ በተደጋጋሚ እንድሠራ የገፋፋኝ በፊስ ቡክ ሳስቀምጥ ታዳሚዉ ሌላ ሥራዬን ማየት ይፈልጋል ብዬ ስላሰብኩ ፤ በቀጣይ በመሣል ላይ ነኝ»


የሥዕሎቻቸዉ በዘይት ቀለም ሸራ ላይ እንዲሁም አሁን ብቅ እያለ ባለዉ በአዲሱ ቴክኖሎጂ በዲጂታል መሆኑን ይናገራሉ። በዲጂታል ሥዕል መሣል ስንል ምን ማለት ይሆን? « በዲጂታል መሣል ስንል በኮንፒዉተር ተጠቅመን የምሰራዉ ማለት

ነዉ። ልክ ፎቶ ሾፕ እንደሚሰራዉ ማለት ነዉ። ለዚህ የሚሆን ሶፍት ዊር አለ። ልክ ሥዕል ለመሳያ እንደሚሆነዉ ቡሩሽ ቀለም ሁሉ ነገር በመቀላቀል መሳል ይቻላል። ልዩነቱ በቀለም መቆሸሽ የለም። እዝያዉ በኮንፒዉተሩ ላይ በመጠቀም የተለያዩ ቀለሞችን እየበጠበጡ መጠቀም ይቻላል። ይህ የቴክኖሎጂ ዉጤት ነዉ። በየጊዜዉ እየተሻሻለ አዳዲስ የመሳያ ሶፍት ዊር ብቅ እያለ ነዉ። እኔ የምጠቀምበት የዲጂታል መሣያ ሶፍትዊር «ፔንት» ይባላል። የተለያዩ የመሣያ ሶፍትዌሮች ማግኘት ይቻላል»


በዚያዉ በካናዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዘዉድነህ ዋለልኝ የሠዓሊ ዳንኤል ሥራዎችን ከሚያደንቁ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸዉ። ኢትዮጵያዉያን ተሰብስበዉ በዓላትን ሲያከብሩ የአቶ ዳንኤልን ሥዕሎች በመሸጥ ይተባበራሉ። እሳቸዉም ቢሆን የሠዓሊ

ዳንኤል ወደ ሰባት ስምንት ሥዕሎችን ገዝተዉ ገዝተዉ ቤታቸዉ ግድግዳ ላይ ሰቅለዋል። አቶ ዳንኤል ጌታሁን ቆየት ካለ ጊዜ ጀምሮ ጓደኛዬ ነዉ፤ በሥዕሎቹ ብዜ ባህልን ያስተዋዉቃል ሲሉ ተናግረዋል።


ሌላዋ የሠዓሊ ዳንኤልን ሥዕል ከሚያደንቁ የቶሮንቶ ነዋሪዎች መካከል ወ/ሮ ይርጋለም ክፍሌ ይገኙበታል። ወ/ሮ ይርጋለም በኔ አስተያየት እንደ ዳንኤል አይነት ጎበዝ ሠዓሊ አይቼ አላዉቅም። ሥዕሎቹን ሳይ የሀገሪ ትዝታ ይይዘኛል። ብዙ ባህሉን ወጉን አስባለዉ። እዉነት ለመናገር ዳንኤል በሥዕሎቹ ሀገርን አስተዋዋቂ አንባሳደር ነዉ።


ሥዕል ኃሳባችንን የምንገልጽበት ዕይታዊ ቋንቋ ነዉ የሚሉን ታዋቂዉ የሥዕል መምህርና የኢላይትመት አርት አካዳሚ በአማርና መጠርያዉ የደብረ አብራሔ ጥበብ አስተዳዳሪ አቶ እሸቱ ጥሩነህ፤ ሠዓሊ በቀለም ቡሩሹ ኃሳቡን ይገልፃል ሲሉ በሰፊዉ ማብራርያ ሰተዉናል። ለሥነ-ጥበብ እድገት ዋንኛዉ ለሠዓልያን ድጋፍ መሥጠት፤ የማኅበረሰቡን ንቃተ ህሊናንም ማስፋት በመሆኑ፤ ለሥነ-ጥበብና ባለሞያዎቹ ድጋፍ እንስጥ ያሉንን የሥነ-ጥበብ መምህር እሸቱ ጥሩነህን እንዲሁም ቃለ-ምልልስ የሰጡንን ሠዓሊ ዳንኤል ጌታሁንን በዶይቼ ቬለ ስም በማመሥገን ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ


ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic