ሠንደቅ ዓላማው፣የጠቅላይ ሚንስትሩ ድጋፍና ግጭቶች | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 06.07.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ሠንደቅ ዓላማው፣የጠቅላይ ሚንስትሩ ድጋፍና ግጭቶች

በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ሰሞኑን በሚደረጉ የድጋፍ ሰልፎች አደባባይ የሚታዩ ባንዲራዎች ድጋፍ እና ውዝግብ አስነስተዋል። «ይኼ ነው ሠንደቅ ዓላማው» እና «እኔን አይወክለኝም» የሚል ክርክርም አጭሯል። በተለያዩ ስፍራዎች ዜጎች ከቀዬያቸው መፈናቀላቸው፣ በተደራጀ መልኩ በሚመስል ኹኔታ ተጠናክሯል። የእምነት አባቶችን የማስታረቅ ሒደቱም ተጀምሯል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:34

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ፋታ ያጡበት ሳምንት

በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ሰሞኑን በሚደረጉ የድጋፍ ሰልፎች አደባባይ የሚታዩ ባንዲራዎች ድጋፍ እና ውዝግብ አስነስተዋል። አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሠንደቅ ዓላማ በድጋፍ ሰልፎች ላይ በድምቀት ሲውለበለብ መታየቱ፦ «ይኼ ነው ሠንደቅ ዓላማው» እና «እኔን አይወክለኝም» የሚል ክርክር አጭሯል። የድጋፍ ሰልፉ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ስፍራዎች ዜጎች ከቀዬያቸው መፈናቀላቸው፣ በተደራጀ መልኩ በሚመስል ኹኔታ ተጠናክሯል። የሃይማኖት አባቶችን የማስታረቅ ሒደቱም ቀጥሏል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች መጠነ ሰፊ የድጋፍ ሰልፎች እየተከናወኑ ነው። የድጋፍ ሰልፎቹ ዋነኛ ማጠንጠኛ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የጀመሩት የለውጥ ሒደት እንዲጠናከር ማበረታታት ነው። በሰልፎቹ ላይ የተለያዩ ባንዲራዎች ሲውለበለቡ ተስተውለዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ እና በተለይ በባህር ዳር ከተማ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ መውለብለቡ እጅግ ያስደሰታቸው በርካቶች የመኾናቸውን ያኽል የተከፉም ነበሩ። ደስታቸውን የገለጡ ሰዎች እላዩ ላይ ምንም ምልክት የሌለበት ባለሦስት ቀለሙ ሠንደቅ ዓላማ ኢትዮጵያውያንን በአንድነት ያሰባስባል «የአባቶቻችን ባንዲራ ነው» ሲሉ ተደምጠዋል። የዚህ ሰንደቅ ዓላማ መውለብለብ ያልተዋጠላቸው ደግሞ፦ በሀገሪቱ ያለውን ብኅኃነት እና ልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ባንዲራ ነው ሲሉ ተቃውሞዋቸውን አስተጋብተዋል።

አዲስ ቸኮል፦ «የሰሞኑን ሰልፎች ተከትሎም ጫጫታዎች ነበሩ» ሲል ጽሑፉን ያንደረድራል። አሁን ሰዎች በሃገራቸው ላይ የፈለጉትን የመያዝ መብታቸው ይከበርላቸው፤ በአሜሪካ ያልተከለከለ ኢትዮጵያዊ አርማና ባንዲራ በኢትዮጵያ ሊከለከል አይገባም፡፡ ይሄ ለዜጎች ልንፈቅድ ከሚገቡ መብቶች እጅግ ኢምንቷ ነች፡፡ ወደፊት መቀየር ካለብን እንቀይረዋለን፤ አሁን ሰዓቱ ስላልሆነ ነው» ሲል ዘለግ ባለው ጽሑፉ አትቷል።  

ጸሐፊ አፈንዲ ሙተቂ «ባንዲራው!» ሲል ርእስ በሰጠው ጽሑፉ፦ «ይህንን ባንዲራ የምጠላው የአጼዎቹ ስርዓት መለያ ስለሆነ ነው» የሚል አስተያየት የሚያቀርቡ ወንድሞች ተከስተዋል። አሁን ገባኝ! ለዚህ ነበር በልሙጡ ባንዲራ ላይ ክርክር የተከፈተው? አጀንዳው ይህ ከሆነ መልሱ ቀላል ነው። የአጼዎቹ ባንዲራ ይህ አይደለም። የአጼዎቹ ባንዲራ ከመሃሉ ባለ ዘውድ አንበሳ ነበረው» ሲል መሀሉ ላይ አርማ የሌለው ባለሦስት ቀለሙ ሠንደቅ ዓላምን የሚነቅፉ ሰዎች ትክክል እንዳልኾኑ ገልጧል።

ከደራሲያን አለም ፔጅ በሚል የፌስቡክ ገጽ ባህርዳር ከተማ ውስጥ አደባባይ ስለወጣው ግማሽ ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሠንደቅ ዓላም  ቀጣዩ ተጽፏል። «በባህር ዳር የአማራ ክልል ባንዲራ ሳይውለበለብ ዋለመደመር ማለት ይህ ነውይህን ለመግለፅ አቃተኝ ቃላቶች ከየት ላምጣ ?! በሕይወት ዘመኔ ይህን በማየቴ እጅግ ደስተኛ ነኝ። ፈጣሪ የሁለቱም ኃይማኖቶች አምላክ የተመሰገ ይሁንዘረኝነት በሽታ ነው ከእንግዲህ እንዳይመለስ አደራ!! እርዝመቱ 500 ሜትር የሆነ ባንዲራ ተውለበለበ» ብሏል። 

አወል አሎ ትዊተር ላይ ባቀረበው የእንግሊዝኛ ጽሑፉ የባህርዳር የድጋፍ ሰልፈኞች ይዘውት የወጡትን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ በማያያዝ  ቀጣዩን ጽፏል። «የጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ ለውጥን በመደገፍ የተደረገው በዛሬው የባህር ዳር ሰልፍ ከምንም በላይ ብዝኃነትን እና ልዩነትን እጅግ የሚያጣጥል ነው»  ብሏል። አያይዞም፦ «በእውነቱ የሰዎች የመደመር ሐሳብ ይኽ ከኾነ ትልቅ ችግር አለብን ማለት ነው» ብሏል። የወደፊቱን አዲስ ነገር ማለም እንደሚገባም ጠቅሷል።

ለአወል ከተሰጡ በርካታ አስተያየቶች መካከል የዞን ጠዘኝ ጦማሪያን አባል ሶሊያና ሽመልስ ቀጣዩን በእንግሊዝኛ ብላለች። «ጭንቀቱ ይገባኛል፤ ወደፊት መመልከትም ያስፈልጋል።  ኾኖም ባህርዳር ስብጥር እንዲኖራት አይጠበቅም። ባህርዳሮች እንደ አማራ ነው ሰልፍ የወጡት፤ ያ ደግሞ እጅግ ደህና ነው» ብላለች።

ጋዜጠኛ ፍስሃ ተገኝ፦ «እነሱ ማለት አብዛኛዎቹ እንደ ኢትዮጵያዊ ለድጋፍ ወጥተዋል ያ ደግሞ እጅግ ደህና ነው» ሲል ከሶሊያና ተቃራኒ የኾነ ሐሳብ ሰንዝሯል። ቀጠል አድርጎም «ለመኾኑ ከመቼ ጀምሮ ነው አንድነት እና ፍቅር መስበክ አደገኛ ነገር ማድረግ የኾነው?» ሲል አጠይቋል። 

ወንድወሰን ተክሉ በበኩሉ‏፦ «ከፋ ከባህር ዳር በለጠች??» ሲል ትዊተር ላይ ጽፏል። «ተዓምር ነው መቼም» ሲል ይንደረደራል የወንድወሰን ጽሑፍ። «በደቡብ ክልል አርባምንጭ የታየው የኢትዮጵያ ባንዲራ ርዝመት ከባለ 500ሜ የባህር ዳሩ በልጦ ባለ 600ሜትር ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ተዓምር ነው ደቡብ!!» ያለው ወንድወሰን ይኽ የአማራ ክልል ሳይኾን አርባ ምንጭ ነው ሲል በእንግሊዝኛ ጽሑፉ መደነቁን ገልጧል።   

«ሲፈልጉ መሀሉ ላይ ንቧን ያርጉበት አረንጓዴ ቢጫ ቀዩአን ግን አይንኩብኝ። ምክንያቱም በልጅነቴ ትምርት ቤት ሰቅያታለው!" እና እቺ ባንዲራ የማንም ብሄር አደለችም የኢትዮጵያውያን እንጂ!» ስትል የጻፈችው ሐዊ ናት ትዊተር ላይ።

በኢትዮጵያ የተለያዩ ስፍራዎች የድጋፍ ሰልፎች የመኪያሄዳቸው ዜና በሚሰማበት በአሁኑ ወቅት ዜጎች ከተለያዩ አካባቢዎች እየተፈናቀሉ መኾኑም አስተጋብቷል። በጌዲዮ ግጭት ብቻ ስምንት መቶ ሺህ ሰው መፈናቀሉ በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎችን አስቆጥቷል።

ገጣሚና ደራሲ ዮሐንስ ሞላ ፌስቡክ ላይ በከተበው ጽሑፉ፥ «ስምንት መቶ ሺህ ሰው ሲፈናቀል ዝም ለማለት የሚያስደፍር ኢትዮጵያዊነት የለም፣ ለጌድኦ ድምጻችንን እናሰማ!» ብሏል።

አሚጎ አሚጎ በሚል የፌስቡክ ስም የቀረበ ጽሑፍ አካባቢን እና ጎጥን እየለዩ ለመብት የሚቆረቆሩ ግለሰቦችን አጥብቆ ተችቷል። «ጥሩ ናቸው የምንላቸው የኦሮሞ አክቲቪስቶች እንኳን አብዲ ኢሌይ 600,000 ህዝባችንን አፈናቅሏል እያሉ ሲጮሁ ከርመው ከጉጂ ዞን የተፈናቀለው 800,000 ጌዲዮ አያሳስባቸውም! ይህ የዘውጌ-ብሔርተኝነት የሚሉት ነገር እንዴት አርጎ ነው ህዝቤን ሰብዓዊነቱን የሚቀማው?» ሲል መደነቁን ገልጧል።  «ከልጅነትህ ጀምሮ አብረህ የኖርከውን ጎረቤትህን ሳትወድ የማታውቀውንና ጠረፍ ላይ የሚኖረውን "የብሔርህን አባል" እንዴት ልትወደው ቻልክ? ይህ ነገር ጤነኛ ነው?» ሲልም ጠይቋል።

ግጭቶቹ ከጌዲዮ ባሻገር፦ በምሥራቅ ሀረርጌ እንዲሁም በሱዳን ጠረፎችም ተስተውለዋል። የቀድሞ የሰማያዊ ፓርት የሕዝብ ግኑኝነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ረጋሳ በፌስቡክ ገጹ፦ «ሀረርጌ በሰውና በንብረት አልፎም በእንስሳት ላይ እልቂቱ እንደቀጠለ ነው። ይሄንን አረመኔያዊ ተግባር የሚያስቆም አካል በቦታው የለም። የሚደርስላቸው የለም። ኸረ የመሪ ያለህ! መተማና ሀረርጌ ኢትዮጵያዊ አይደሉም እንዴ? ምንድን ነው የሚጠበቀው?»  ሲል ጥሪ አስተላልፏል።

በመተማ የእርሻ ሥፍራዎች የሱዳን ጦር ጥቃት ሰነዘረ መባሉም በስፋት ተነግሯል። የሱዳን ጦር ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ገፍቶ ጥቃት ማድረስን ያኽል ይቅርና እያንዳንዷ ጥቃቅን ነገር ለጠቅላይ ሚንስትሩ ትደርሳለች ያለው ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ጠንከር ያለ ትችቱን ሰንዝሯል። «ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተጠያቂ ነው!» በሚለው የፌስቡክ ጽሑፉ ርእስ ስር ዝርዝር ጉዳዮችንም ጽፏል። «የቀን ጅብና ፀጉረ ልውጥ አብረን እንከላከል ማለት አንድ ነገር ነው። ዜጎች ድረሱልን ሲሉ አለመድረስ ደግሞ ተጠየቂነትን ያመጣል» ያለው ጌታቸው፥ «በተለይ የዜጎችን ደህንነትና ሉአላዊነት የማስጠበቅ የመጨረሻው ሥልጣን የተሰጠው ሰው ይህን ያህል ቸልተኝነት ማሳየቱ ከቆዩት የሚለየው ነገር አይኖርም!» ብሏል።

ከሰሞኑ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎችን ቀልብ ከሳቡ ጉዳዮች መካከል በክርስትና እና እስልምና ኃይማኖቶች አባቶች መካከል የነበረውን ቅሬታ እና ልዩነት ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ይገኝበታል። ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እና የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን አነጋግረው ከስምምነት ላይ እንዲደርሱ መደረጉን በርካቶች አወድሰዋል።

«በይቅርታ መንፈስ የተናደው የጥላቻ ተራራ በሚል ርእስ ጽሑፉን ያቀረበው ጋዜጠኛ ነቢዩ ሲራክ እርቀ ሰላም በመውረዱ በዝርዝር ጽሑፉ ደስታውን ገልጧል። «ግፉ እንዳይጥል በሙስሊም ልሂቃን መካከል ላለው አለመግባባት ሰላማዊ መፍትሄ ለማምጣት አዲስ የጋራ ኮሚቴ ተመስርቶ እርቅ በመውረዱ ደስታየ ከመጠን አልፏል ሁላችሁንም እንኳን ደስ ያላችሁ!» ብሏል።

ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ ሀገር ቤት እና በውጭ ሀገር የሚገኙ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተከርስቲያን አባቶችን ለማስታረቅ ሒደቱን መጀመራቸውንም ብዙዎች አወድሰዋል። በሀገር ውስጥ እና በውጭ በሚገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶስክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶሶች መካከል ዕርቀ ሰላም ለማውረድ በመጪው ሐምሌ 12 በአሜሪካ ድርድር ማድረግ እንደሚጀመር መገለጡን በተመለከተ በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።  

የተወሰኑትን ለማቅረብ ያኽል፥ መንበረ-ማርያም በሚል የፌስቡክ ስም የቀረበ ጽሑፍ፦ «እንኳን ተስማማችሁ፤ ሠላም ለኹሉም ጥሩ ነው፤ የሰላም ጠላት ዲያብሎስ ይፈር» የሚል መልእክት ይነበብበታል።  አብዱ መኪ፦ «እጅግ መልከም ዜና ነው» ሲል «አላህ ያግዛችሁ» ያለው ደግሞ ኬዊ ሲቲ ነው።  «ተመስገን»  የሚለው አጭር የፌስቡክ መልእክት ደግሞ የመሰረት ምሳሌው ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic