ሠማያዊ ፓርቲ ምርጫውን አወገዘ | ኢትዮጵያ | DW | 30.05.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ሠማያዊ ፓርቲ ምርጫውን አወገዘ

ሠማያዊ ፓርቲ ባለፈው ሣምንት በኢትዮጵያ የተኪያሄደው አጠቃላይ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ አለመሆኑን በመግለጥ ማውገዙን የፈረንሣይ ዜና አገልግሎት ዘገበ። አጠቃላይ ውጤት ከመገለጡ በፊት ይፋ የሆነው ቅድመ ውጤት እንደሚያመላክተው ከሆነ ከ547 የምክር ቤት መቀመጫዎች ገዢው ኢሕአዴግ እስካሁን 442ቱን መቀመጫዎች ለራሱ አድርጓል ሲል የዜና አውታሩ ጠቅሷል።

ከአፍሪቃ በሕዝብ ብዛቷ ኹለተኛ በሆነችው ኢትዮጵያ ከኹለት ዐሥርት ዓመታት በላይ ሥልጣኑን ተቆጣጥሮ የቆየው ኢሕአዴግ የምክር ቤት መቀመጫዎችን ይጠቀልላል ተብሎ እንደሚጠበቅም የዜና ምንጩ ገልጧል።

ሠማያዊ ፓርቲ ትናንት በሠጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፥ «ሠማያዊ ፓርቲ የምርጫ ሒደቱን ነፃ እና ፍትኃዊ ነው ብሎ አይቀበልም፤ ጤናማ እና ዲሞክራሲያዊ ያልሆነ የምርጫ ውጤትንም አይቀበልም» ብሏል። «ይኽ መቶ በመቶ የገዢው ፓርቲ ማሸነፍ ክብር ያለመስጠት መልእክት ነው። መድብለ-ፓርቲ በኢትዮጵያ እንዳከተመለትም ያሳያል» ሲል ፓርቲው አክሏል። እሁድ ምርጫው ከመከናወኑ በፊት መንግሥት ድሉን አስተማማኝ ለማድረግ የማስፈራራት፣ ዕጩዎችን ያለመመዝገብ አለያም ደጋፊዎችን የማሰር አምባገነናዊ ዘዴዎችን ተጠቅሟል ሲል ሠማያዊ ፓርቲ መግለጡም ተዘግቧል።

የሠማያዊ ፓርቲ ቃል-አቀባይ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ቁጥራቸው 200 የሚደርስ የፓርቲያቸው ዕጩዎች ለምክር ቤት ምርጫ የመወዳደር መብታቸው እንደተነፈጋቸው ብሎም 52 የፓርቲ አባላት ከምርጫው ቀደም ብሎ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ለዜና አውታሮች ተናግረዋል። ቃል አቀባዩ አያይዘው ሲናገሩ፥ «ቅሬታችንን የሚያስተናግድ ገለልተኛ የፍትኅ ሥርዓት አለ ብለን አናስብም። ሠላማዊ ትግላችንን እንገፋበታለን» በማለት ለጋዜጠኞች ገልጠዋል።

ከኢትዮጵያ ጋር በአካባቢያዊ የፀጥታ ጥበቃዎች ትብብር የምታደርገው ዩናይትድ ስቴትስ ከምርጫው በኋላ በሠጠችው መግለጫ «የሲቪል ማኅበራት፣ መገናኛ አውታሮች፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲሁም ገለልተኛ ድምጾች እና ዕይታዎች ላይ የቀጠለው ማዕቀብ እጅግ ያሳስበናል» ማለቷም ተዘግቧል።

የአውሮጳ ኅብረት በበኩሉ እውነተኛ ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ ገና ስር አልያዘም ማለቱ ተጠቅሷል። «በጋዜጠኞች እና ተቃዋሚዎች ላይ የሚደረገው የእስራት ተግባር፣ የተለያዩ የመገናኛ አውታሮች መዘጋት፣ ተቃዋሚዎች በምርጫ ዘመቻ ወቅት ያጋጠማቸው መሰናክል» አሳሰበን ሲል የአውሮጳ ኅብረት ጠቅሷል በማለት የፈረንሣይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

ይሁንና የአፍሪቃ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ምርጫው «ተዓማኒ» እና«አፍሪቃ ውስጥ ምርጫ ለማከናወን የአፍሪቃ ኅብረት ካስቀመጠው መመሪያ ጋር በአጠቃላይ ስምም ነው» ሲል ጠቅሷል።

ረቡዕ ዕለት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች /ቤት ሚንሥትር ዲኤታ አቶ ሽመልስ ከማል አሸናፊነቱ የመጣው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሻሻል በማሳየቱ ነው ማለታቸውን በመጥቀስ «በሀገሪቱ ለተዋወቀው የኢኮኖሚ መሻሻል መራጮች ለገዢው ፓርቲ የሚገባውን አድርገዋል» ማለታቸውን የዜና አውታሩ አክሎ ዘግቧል።

ቶት ስለሺ

ልደት አበበ