ሞዛምቢክና ፀረ- ፈንጂ ትግሏ | አፍሪቃ | DW | 28.06.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ሞዛምቢክና ፀረ- ፈንጂ ትግሏ

የተቀበሩ ፈንጂዎችን ምርት እና ዝውውርን የሚከለክለው የኦታዋ ውል የሚፈተሽበት ሦስተኛው ዓለማቀፍ ጉባዔ ትናንት በሞዛምቢክ ተጠናቀቀ። ውሉን የተፈራረሙት ሀገራት የመጀመሪያውን ጉባዔ ያካሄዱት ከ15 ዓመታት በፊት ነበር ። ደቡባዊትዋ አፍሪቃ ሀገር ሞዛምቢክ ያኔ በዓለም እጅግ ብዙ ፈንጂዎች ከተቀበሩባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ነበረች።

ዛሬ ግን ሁኔታው ተቀያይሮ ሞዛምቢክ አዎንታዊ ውጤት ማስመዝገቧ ተሰምቶዋል። በዓለም እጅግ ብዙ ፈንጂዎች ተቀብሮባቸዋል ከሚባሉት አምሥት ሀገራት መካከል ሞዛምቢክ በጠቅላላ ከፈንጂ ነፃ የምትሆን የመጀመሪያዋ ሀገር ልትሆን የምትችልበት ዕድል ከፍ ያለ ነው። የሞዛምቢክ መንግሥት እስከ ተያዘው አውሮጳዊ ዓመት 2014 ማብቂያ ድረስ በሀገሩ አሁንም ፈንጂ በብዛት ተቀብሮ የሚገኝባቸውን 303 አካባቢዎች የማፅዳት ዕቅድ ይዞዋል። ይኸው አካባቢ አራት ሚልዮን ካሬ ሜትር ወይም የመዲናይቱን ማፑቶ ያህል ስፋት እንዳለው ይነገራል።


እአአ ከ2007 ዓም ወዲህ በተለያዩት የሞዛምቢክ ክፍላተ ሀገር ከ100,000 የሚበልጡ ፈንጂዎች ተወግደዋል፤ እንደ ሞዛምቢክ ተጠባባቂ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኤንሪኬ ባንዝ እምነትም፣ የቀሩት ፈንጂዎች እአአ እስከ ታህሳስ 31፣ 2014 ዓም ከተቀበሩበት ይወጣሉ።
« ሞዛምቢክ በሀገርዋ አሁንም ተቀብረው የሚገኙትን ፈንጂዎች በተቻለ ፍጥነት ለማስወገድ ቃል ገብታለች። የዚሁ ስራ ሂደት የሚንከታተልበት መሳሪያ እንደሚያሳየው፣ ፈንጂ አለባቸው ተብለው እስካሁን የሚታሰቡትን አካባቢዎች ከፈንጂ ነፃ ማድረግ እንችላለን። በዚሁ ሥራችን ላይ የተለያዩ ተጓዳኞች እና በተለይም ያካባቢው ሕዝብ ረድተውናል። »
የተቀበሩ ፈንጂዎች ምርት እና ዝውውር የሚከለክለው ውል እአአ በ1980 ዓም በኦታዋ ካናዳ በተፈረመበት ጊዜ ፣ እአአ በ1974 ዓም ከፖርቱጋል ነፃነቷን ያገኘችው ሞዛምቢክ በዓለም ፈንጂ በብዛት ከተቀበረባቸው ሀገራት መደዳ ትቆጠር ነበር። እንደሚታወሰው፣ በዚያን ግዜ ማርክሳዊ የፍሬሊሞ ፓርቲ የመራው የሞዛምቢክ መንግሥት ቀድሞ ሮዴዥያ በመባል ትታወቅ በነበረችው የአሁኗ ዚምባብዌ እና በደቡብ አፍሪቃ በነበሩት የዉሁዳን ነጮች አገዛዝ አንፃር ትግል ያካሄዱ የነበሩ የታጠቁ ቡድኖችን መርዳት በቀጠለበት ጊዜ የነዚሁ ሁለት ሀገራት መንግሥታት በሞዛምቢክ በገዥዉ በፍሬሊሞ አንፃር ይንቀሳቀስ ለነበረው ያማፅያኑ የሬናሞ ቡድን ርዳታ ማቅረብ ጀመሩ። በፍሬሊሞና ሬናሞ መካከል እአአ ከ1977 እስከ 1992 ዓ,ም እና በተካሄደው የርስ በርስ ጦርነት ወቅት፤ በሀገሪቱ ቁጥሩ በውል ያልታወቀ እጅግ ብዙ ፈንጂዎች ተቀብረዉ ነበር። ተቀናቃኞቹ ወገኖች የ16 ዓመቱን የርስ በርስ ጦርነት ያበቃውን ውል በሮም፣ ኢጣልያ ከተፈራረሙ በኋላ እነዚሁ ፈንጂዎች ለብዙ ዓመታት ለሀገሪቱ ልማት ትልቅ እንቅፋት ደቅነው ነበር። ይህ ሲታሰብ ታድያ፣ እስከ እአአ 2014 ማብቂያ ድረስ ሀገሪቱን ከፈንጂ ነፃ ማድረግ ይቻላል ብሎ የጠበቀ አልነበረም። ይሁን እንጂ፣ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ፣

ለጋሽ ሀገራት እና የሞዛምቢክ መንግሥት ባንድነት ባደረጉት ጥረት ይኸው ፀረ ፈንጂው ትግሉ የተሳካ ውጤት አስገኝቶዋል። እና በአሁኑ ጊዜብዙው የሞዛምቢክ ከፊል ከፈንጂ የፀዳ ሲሆን ፣ የሀገሪቱ ነዋሪም ካላንዳች ገደብ በፈለገበት አካባቢ ሊንቀሳቀስ ችሎዋል።
የሞዛምቢክ ፕሬዚደንት አርማንዶ ገቡዛ በርስ በርሱ ጦርነት ጊዜ የተቀበሩ ፈንጂዎችን በማውጣቱ ስራው ላይ የሀገራቸው መንግሥት ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ላገኘው ድጋፍ ምሥጋናቸውን በማቅረብ ድጋፉን እንዲቀጥል ተማፀነዋል።
« ሞዛምቢክን ከፈንጂ ነፃ የሆነችበትን ዕለት አብረን ማክበር እንችል ዘንድ በዚሁ ረገድ በጀመርነው እና አሁን በመጨረሻ ደረጃ ላይ በምንገኝበት ጥረታችን ላይ አብራችሁን እንድትጓዙ በዚህ አጋጣሚ ለመጠየቅ እፈልጋለሁ። የኦታዋ ውል በተግባር የተተረጎመበት ድርጊት አበረታች ውጤት አሳይቶዋል። አሁን መሥቀለኛ መንገድ ላይ ነው የምንገኘው፤ ምክንያቱም የቀሩ ፈንጂዎች እንዲወድሙ እና ፈንጂ የተቀበረባቸው ማሳዎችም እንዲፀዱ ለማድረግ ይህን ያስመዘገብነውን ውጤት ለመላ ዓለም ማስተላለፍ ይጠበቅብናልና። »
ይሁን እንጂ፣ በሞዛንቢክ የተቃዋሚው ፓርቲ ሬናሞ እና ገዢው ፍሬሊሞ ካለፈው ዓመት ወዲህ እንደገና መዋጋት ጀምረዋል። በተለይ፣ በማዕከላይ ሞዛምቢክ ሬናሞ በፖሊስ፣ በጦር ኃይሉ እና ሲቭሉን በሚያመላልሱ አውቶቡሶች ላይ ጥቃት እየጣለ መሆኑ ተሰምቶዋል። በአማፅያኑ ጥቃት የተነሳ መንገዶችን አዘውትረው መዝጋት ግድ ሆኖዋል። ይህም ቢሆን ግን፣ የሞዛንቢክ መንግሥት ጦር ኃይላትም ሆኑ የሬናሞ ተዋጊዎች እስካሁን አዳዲስ ፈንጂዎችን አለመቅበራቸው እፎይ የሚያሰኝ መሆኑን ፈንጂዎች እንዲከለከል የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ ዘመቻ የሚያስተባብሩት እና የኖቤል ሰላም ተሸላሚ ጆዲ ዊልያምስ ገልጸዋል።
« ወደ ሞዛምቢክ የምንመጣው ደስ እያለን ነው። ራሷን ከፈንጂ ነፃ ለማድረግ ቆርጣ የተነሳች ለሌሎች አርአያ የምትሆን ሀገር ናት። »
በሞዛምቢክ መዲና፣ ማፑቶ ባለፉት አምሥት ቀናት በተካሄደው ፀረ ፈንጂ ውል ፈታሽ ጉባዔ የተሳተፉት ከ150 በላይ ከሆኑ ሀገራት የተውጣጡት ከ800 የሚበልጡ ልዑካን ሞዛምቢክ የተቀበሩ ፈንጂዎችን በማፅዳቱ ተግባር ያስመዘገበችው ዓይነቱ አዎንታዊ ውጤት እንዴት በሌሎች ሀገራት ሊደገም እንደሚችል በሰፊው መክረዋል።


ኬንያ ፤ የጎሳ ግጭት ሥጋት
በምዕራባዊ ኬንያ ካለፉት በርካታ ቀናት ወዲህ በተለያዩት የሀገሪቱ ጎሣዎች መካከል ጥላቻ የሚያስፋፉ ማን እንደጻፋቸው የማይታወቁ ወረቀቶች መበተን ይዘዋል። ለምሳሌ ባንድ አካባቢ ለተቃዋሚው ቡድን መሪ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ራይላ ኦዲንጋ እና ለሉዎ ጎሣቸው « ጦርነት ከፈለጋችሁ፣ ታገኙታላችሁ።

» የሚል ማስጠንቀቂያ የሚነበብበት ጽሑፍ ይገኝበታል። ሌላ ከአሥር ቀናት በፊት የተበተነ ደግሞ በስምጥ ሸለቆ የሚኖሩት የሉዎ ጎሣ አባላት ግዛቱን በሰባት ቀናት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ ያስጠነቅቅ እና ይህን ካላደረጉ በየቤቱ ገብተው እንደሚያባርሩዋቸው ይዝታል። በማህበራዊ መረቦችም በወቅቱ አንዱን ጎሣ ከሌላው የሚያጣላ መልዕክት እየቀረበ ነው። ይኸው ማስጠንቀቂያ በተለይ የሉዎ ጎሣን ያነጣጠረበት ድርጊት በኬንያ የባህር ጠረፍ በምትገኘዋ የምፔኬቶኒ ከተማ አፋዊው የተጣሉት ጥቃቶች ተጠያቂ ነው። ከ13 ቀናት በፊት በምፔኬቶኒው ጥቃት ቢያንስ 65 ሰዎች ተገድሎዋል። ምንም እንኳን አሸባብ ጥቃቱን እንደጣለ ቢያስታውቅም፣ የኬንያ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ ይህን አስተባብለው፣ የተቃውሞው ቡድን በኪኩዩ ጎሣቸው ላይ የጣለው ጥቃት መሆኑን ያስታወቁት። ይህ የመብት ተሟጋቹ ጆን ጊቶንጎ እንዳሉት መንግሥቱ ጉዳዩን በሚገባ እንዳልያዘው አሳይቶዋል።
« የሚያሳዝነው፣ የሀገሪቱ መንግሥት ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ የተከተለዉ አሰራር የሚገኘበትን ግራ የመጋባት እና አቅም አልባ የሆነበትን ሁኔታ በግልጽ ያአየ ይመስለኛል። ባንድ በኩል፣ ፕሬዚደንቱ የተቃዋሚው ቡድን ከጥቃቱ በስተጀርባ እንዳለበት ሲናገሩ፣ በሌላ ወገን፣ ብሔራዊው የስለላ ድርጅት አሸባብን ጠርጥሮዋል። ይህ ግራ መጋባትን ከመፍጠሩ ጎን፣ በኬንያ ውጥረቱን እና አለመተማመኑን አባብሶታል። »


በዚህም የተነሳ የኬንያ ሕዝብ በአሁኑ ጊዜ በተጠንቀቅ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ያሁኑ ሁኔታ በብዙዎች ዘንድ እአአ ከታህሳስ ፣ 2007 ዓም ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በኋላ የተካሄደውን የጎሣ ግጭት ትዝታ ቀስቅሶዋል። እንደሚታወሰው፣ አወዛጋቢውን የምርጫ ውጤት በተከተሉት ወራት በቀድሞው ፕሬዚንት ምዋይ ኪባኪ እና በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ራይላ ኦዲንጋ ደጋፊዎች መካከል በተፈጠረው የጎሣ ግጭት ቢያንስ 1,200 ሰዎች ሲገደሉ፣ በመቶ ሺህ የሚገመቱ ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። ተቀናቃኞቹ ወገኖች ከረጅም ድርድር በኋላ ሥልጣኑን ለመጋራት በተስማሙበት ጊዜ ነበር ውዝግቡ ሊያበቃ የቻለው።
እአአ በ2013 በኬንያ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በተካሄደበትም ጊዜ ተመሳሳይ ውዝግብ እንዳይደገም ሕዝቡ በጣም ቢፈራም፣ በሰላማዊ ሁኔታ ነበር የተጠናቀቀው። ለዚህም፣ በበርሊን የሚገኘው « ሽቲፍቱንግ ቪስንሻፍት ኡንድ ፖሊቲክ » የተሰኘው የፖለቲካ ጥናት ተቋም ባልደረባ እንደ ማርጊት ሄልቪክ በተ አስተያየት፣ አሁን ኬንያን በፕሬዚደንትነት እና በምክትል ፕሬዚደንትነት የሚመሩት ኡሁሩ ኬንያታ እና ዊልያም ሩቶ ሁለቱን ተቀናቃኝ ጎሣዎች ወክለው በዕጩነት መወዳደራቸው እና ማሸነፋቸው ድርሻ አበርክቶዋል።
« ይህ ግን በሰፊው ሕዝብ መካከል ሀቀኛው እርቀ ሰላም ወርዶዋል ማለት አይደለም። የኪኩዩ እና የሉዎ ጎሳዎች መካከል ተቀናቃኝነቱ ሁሌም የኖረ ነው። »በተለይ ኬንያታ ተቃዋሚውን ለሰሞኑ ጥቃት ተጠያቂው የተቃዋሚው ቡድን ባሉበት ድርጊት በሁለቱ ጎሣዎች አክራሪ አባላት መካከል እየተባባሰ የሄደውን ውጥረት ይበልጡን ማካረራቸውን ሄልቪግ በተ አስረድተዋል፣ ይሁንና፣ ይላሉ ሄልቪግ በተ ፣ የተቃዋሚው ወገንም ፀብ ከመጫር ወደኋላ አላለም። ኦዲንጋ በዚህ በያዝነው ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ በተለያዩት የሀገሪቱ ችግሮች ላይ የሚመክር አንድ ብሔራዊ ውይይት እንዲደረግ ጥያቄ ባቀረቡበት ጊዜ ነበር፤ ውዝግቡ እንዳዲስ የተቀሰቀሰው። የኬንያ መንግሥት ሕዝቡን ከአሸባብ ጥቃት አልተከላከለም በሚል ኦዲንጋ ወቀሳ በመሰንዘር፣ ኬንያ በሶማልያ ያሠማራችውን ጦሯን እንድታስወጣ እና የሀገሯን የፀጥታ ሁኔታም እንድታሻሽል ጠይቀዋል። ይህን ተከትሎ የመንግስቱ እና የተቃዋሚ ቡድን ተወካዮች የጋለ ክርክር አካሂደዋል።

አንዳንዶችም ይህንን ክርክር የጎሣውን ልዩነት ለማነሳሳቱ ተግባር ተጠቅመውበታል። በዚህም የተነሳ የኬንያ ዓቃብያነ ሕግ ጽሕፈት ቤት ጥላቻን ነዝተዋል ብሎ የጠረጠራቸውን ፖለቲካኞች ለጥያቄ ጠርቶዋል። የተቃዋሚው የሴቶች ተወካይ ሚሺ ምቦኮ ለምሳሌ አብዮት እንዲካሄድ ጥሪ አቅርበዋል፤ የገዢው ፓርቲ የምክር ቤት እንደራሴ ሞዘስ ኩሪያ የሉዎ ጎሣ አለመረጋጋት ለመፍጠር እና የኃይል ተግባር ለመውሰድ ዝግጁ ነው ሲሉ በፌስቡካቸው ወቅሰዋል። ይኸው ገጻቸው አሁን ታግዶዋል። ጥላቻን የማስፋፋቱ ሁኔታ አመቺ መሆኑን የቀድሞዋ የውህደት ሚንስትር ሚሊ ልዋንጋ አስታውቀው፣ ጥምሩ መንግሥት የራሱን ጎሣዎች ጥቅም ለማስከበር የቆመ ነው በሚል ብዙዎች መውቀሳቸውን አመልክተዋል።
« ኬንያ ብዙ ችግሮች አሉዋት። እና ሰዎች አዳጋች ሁኔታ ሲገጥማቸው እና ለችግራቸውም መፍትሔ ማግኘት ሲያቅታቸው ያለመረጋጋት ለመፍጠር የሚፈልጉ ሰዎች የሚያሰራጩትን ፕሮፓጋንዳ በቀላሉ ይቀበላሉ። »

አርያም ተክሌ
ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic