ሞኖሮቪያ፤ በላይቤሪያ የኤቦላ ወረርሽኝ ስጋት አከተመ | ዓለም | DW | 14.01.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ሞኖሮቪያ፤ በላይቤሪያ የኤቦላ ወረርሽኝ ስጋት አከተመ

የዓለም የጤና ድርጅት በምዕራብ አፍሪቃ በተለይ በሶስት ሃገራት የበርካቶችን ህይወት የቀጠፈዉ የኢቦላ ወረርሽን መገታቱን ዛሬ ይፋ አደረገ። ኤቦላ ላለፉት ሁለት ዓመታት በተጠቀሰዉ አካባቢ ከ11 ሺህ የሚበልጡ ሰዎችን ፈጅቷል።

በወቅቱ የወረርሽኙ መስፋፋት ከመድኃኒት አለመገኘት ጋር ተደራርቦ ያሰጋዉ የዓለም የጤና ድርጅት በመላዉ ዓለም የጤና ስጋት መከሰቱን አዉጆ ነበር። በበሽታዉ ከተጠቁት ሃገራት ቀደም ሲል ጊኒ እና ሴራሊዮን ከኤቦላ ተሐዋሲ ስጋት ነፃ መሆናቸዉን ድርጅቱ ባለፈዉ ወር አመልክቷል። ከኤቦላ ነፃ የመሆኛዋን ቀን ስትጠብቅ የቆየችዉ ላይቤሪያ ዛሬ የጠበቀችዉን ይህን የምስራች በዋና ከተማዋ ተቀብላለች። በዓለም የጤና ድርጅት የአስቸኳይና አደጋ ሰብዓዊ አስተዳደር ዳይሬክተር ዶክተር ሪክ ብረኒን የወረርሽኙ ስርጭት በላይቤሪያ ብቻ ሳይሆን በመላዉ ምዕራብ አፍሪቃ ማክተሙን እንዲህ አብስረዋል።

«ክቡራት እና ክቡራን ዛሬ ጥሩና ወሳኝ ቀን ነዉ። የዓለም የጤና ድርጅት በቅርቡ ላይቤሪያ ዉስጥ የተቀሰቀሰዉ ገዳይ የኤቦላ ተሐዋሲ ወረርሽኝ ማክተሙን ይፋ ያደርጋል። ወረርሽኙ ካለፈዉ ኅዳር አጋማሽ ጀምሮ የመቆሙ ክትትል ሲደረግ ቆይቷል። በዚህም ላይ ሶስቱም የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ጊኒ፤ ሴራሊዮን እና ላይቤሪያ ይህን ፈታኝ ወረርሽኝ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ለመጀመሪያ ጊዜ በጋራ ስርጭቱ እንዲቆም ማድረግ ችለዋል።»

Karte Ebola Neue Fälle 1. Juli 2015

በኤቦላ የተጎዳዉ የምዕራብ አፍሪቃ ክፍል

አያይዘዉም ምንም እንኳን ወረርሽኙ አብቅቷል ቢባልም በበሽታዉ ተይዘዉ ከሞት የተረፉትን የመከታተል የማማከርና ተገቢዉን የህክምና ርዳታ የመስጠቱ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመልክተዋል። ላይቤሪያ ከኦቦላ ነፃ የመሆኗ ማረጋገጫ የተሰማዉ የመጨረሻዉ የኤቦላ ታማሚ ተሐዋሲዉ በዉስጡ እንደሌላ ከተረጋገጠ ከ42ቀናት በኋላ መሆኑ ነዉ። ላይቤሪያ ቀደም ሲል ባለፈዉ ግንቦት ወር ከኤቦላ ነፃ መሆኗን ይፋ አድርጋ ነበር። ሆኖም በተሐዋሲዉ የተያዙ አዳዲስ በሽተኞች ሲገኙ ዳግም ከኤቦላ ለመላቀቅ ያለፉትን ወራት ስትታገል ሰንብታለች። በኤቦላ የሞቱትን ጨምሮ ባጠቃላይ በተሐዋሲዉ 28,600 ሰዎች መያዛቸዉን የዓለም የጤና ድርጅት መዝግቧል።