ሞቃዲሾና የውጊያው መዘዝ | የሶማልያ ውዝግብ | DW | 18.04.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የሶማልያ ውዝግብ

ሞቃዲሾና የውጊያው መዘዝ

የሶማልያ መዲና ሞቃዲሾ ውስጥ ትናንት ሌሊት በአዳፍኔና በመድፍ ብርቱ ውጊያ ተካሄደ። በውጊያው ቢያንስ አስራ አንድ ሰዎች ተገድለዋል። በርካቶችም ቆስለዋል። አራት ሰዓት ገደማ ያህል የተካሄደው ውጊያ ስላስከተለው ጉዳት በመዲናይቱ የሚገኘውን ሶማልያዊው ጋዜጠኛ አዌስ ኡስማን ዩሱፍን አርያም ተክሌ በስልክ አነጋግራዋለች።

የኢትዮጵያ ወታደር በሞቃዲሾ

የኢትዮጵያ ወታደር በሞቃዲሾ

« በሞቃዲሾ ፕሬዚደንታዊ ጽሕፈት ቤት በተመደቡት የኢትዮጵያ ወታደሮች በሠርጎ ገቦች በሚረዱት የጎሣ ሚሊሲያዎች መካከል በተለያዩ የመዲናይቱ ሠፈሮች ትናንት ሌሊት በተካሄደው ውጊያ ቢያንስ አስራ አንድ ሰዎች መገደላቸውና የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ሀያ ሰዎችም ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑ ተዘግቦዋል። »
በሞቃዲሾ የሚገኙት የተለያዩት ጎሣዎች ሽማግሌዎች እንዳስታወቁት፡ ባለፉት ጥቂት ሣምንታት በመዲናይቱ በተካሄደ ውጊያ ከአንድ ሺህ የሚበልት ሰዎች ተገድሎዋል። በተመድ ዘገባ መሠረት፡ ከየካቲት ወር ወዲህ ከመዲናይቱ ነዋሪዎች መካከል አንድ አምስተኛው መሸሹ ተመልክቶዋል። ውጊያው አሁን እንደገና የፈነዳበት ድርጊት የሞቃዲሾን ሁኔታ ሊያካርረው እንደሚችል ያመለከተው አዌስ በወቅቱ በመዲናይቱ ፀጥታ መስፈኑን አስታውቋል።
/እስካሁን መዲናይቱ በጣም ተረጋግታለች፤ ምንም እንኳን አንዳንድ ሰዎች ጓዛቸውን ይዘው ትናንት ሌሊት ውጊያ ከተካሄደባቸው አካባቢዎች ሲሸሹ ቢታዩም። »
በሌላ ዜና ደግሞ፡ በሞቃዲሾ ተጠናክሮ በቀጠለው ውጊያ ሰበብ፡ ወደ ሰማንያ ዘጠኝ የሚጠጉ የኢትዮጵያ ወታደሮች በሁለት ትናንሽ መርከቦች የኤደን ባህረ ሠላጤ ተሻግረው ደቡባዊ የመን መግባታቸውን የጀርመን ዜና ወኪል ዴ ፔ አ የአል አያም ድህረ ገፅን ጠቅሶ ትናንት ዘግቦዋል። ከከፊል የፑንትላንድ የቦሳሶ ከተማ ተነሱ የተባሉት ኢትዮጵያውያኑ ወታደሮች አሁን በጦር ኃይል ተሽከርካሪዎች ወደ የመን ወደ ከተማ ወደ ኤደን መወሰዳቸውን አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የየመን ባለሥልጣን ለዴፔአ አመልክተዋል። ይህንን ዜና ለማረጋገጥ ወደ ኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር እና ዠኔቭ ወደሚገኘው የተመድ የስደተኞች ተመልካች መሥሪያ ቤት ስልክ በመደወል ያደረግነው ሙከራችን አልተሳካልንም። ይህ በዚህ እንዳለ፡ የሶማልያ የሽግግር ምክር ቤት ሠላሣ አንድ እንደራሴዎቹን ከሥራ አሰናብቶዋል። እንደራሴዎቹ ለምን እንደተባረሩ ጋዜጠኛውን አዌስ ጠይቄዋለሁ።
« ከምክር ቤቱ ተባረዋል፤ ምክንያቱም፡ ፓርላማው ቢያንስ ወደ አርባ ሁለት ለሚጠጉ ከሀገር ውጭ ለሚገኙ እንደራሴዎች በሠላሣ ቀኖች ውስጥ ባይዶዋ በሚገኘው የሀገሪቱ ምክር ቤት ሥራቸውን እንዲጀምሩ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር። በዚህም መሠረት፡ አስራ አንዱ ወደ ባይዶዋ በመሄድ በምክር ቤቱ የመጨረሻ ጉባዔ ላይ ተሳትፈዋል። ሠላሣ አንዱ ግን ወደ ባይዶዋ ባለመመለሳቸው የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አደን ማዶቤ እንደራሴዎቹ እንደተባረሩ ትናንት በይፋ አስታውቀዋል። »
በዚህም የተነሳ፡ እንደራሴዎቻቸው የተባረሩባቸው ጎሣዎች እነዚህን የምክር ቤት አባላትን የሚተኩ እንደራሴዎችን እንዲመርጡ ጠይቀዋል።