ሞሮኮ እና ንጉስዋ | ኢትዮጵያ | DW | 25.07.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ሞሮኮ እና ንጉስዋ

የሞሮኮ ንጉስ መሀመድ ሳድሳይ ስልጣን ከያዙ ባለፈው ሀሙስ አስር ዓመት ሆናቸው። በነዚሁ አስር ዓመታት ውስጥ በሰሜን አፍሪቃዊቱ ውስጥ ብዙ ለውጦች ታይተዋል። የተካሄዱት ለውጦች የሀገሪቱን ንጉስ ተወዳጅ አድርጎዋቸዋል። ሆኖም፡ የሀገሪቱ ህዝብ ብዙ የሚጠብቀው ነገር እንዳለ ነው የተሰማው።

default

ንጉስ መሀመድ ሳድሳይ

የሞሮኮ ንጉስ መሀመድ ሳድሳይ ስልጣን ከያዙበት ጊዜ አንስቶ ወጣቱ የተሀድሶ ለውጥ አራማጁ ንጉስ ተብለው ነው የሚጠሩት። የሰላሳ አምስት ዓመቱ ንጉስ ከአስር ዓመት በፊት ዘውድ ሲጭኑ ለሀገሪቱ አዲስ ገጽታ ነበር የሰጡዋት። የተአበሩ ግን እጅግ ይፈሩ የነቡት አባታቸው የንጉስ ሀሰን ዳግማዊ አመራር ዘመን ወዲያው ነበር የያከተመው። በንጉስ መሀመድ ሳድሳይ ዘመን ሞሮኮ ብዙ ለውጥ አሳይታለች። ብዙዎች ግን የሚጠብቁት ገና ብዙ ነው።
በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ስለወጣቱ የሞሮኮ ንጉስ ብዙም አይሰማም። መጓዝ እንደሚወዱ፡ ብዙ ጊዜም ወደ ፓሪስ፡ ስዊትዘርላንድ ወይም ዩኤስ አሜሪካ እንደሚጓዙ ይታወቃል። በዓለም አቀፍ የፖለቲከድ መድረክ ላይ ግን ብዙም አይሳተፉም። በሀገራቸው ቴሌቪዥን ከታዩም የአካል ተጎጂዎች መጠለያ ወይም ተመሳሳይ ማህበራዊ ተቋማትን መርቀው ሲከፍቱ ነው። ይህ ተግባራቸው ተወዳጅ ያደረጋቸው ከመሆኑም በላይ በሀገሪቱ የድሆቹ ንጉስ የሚል መጠሪያ አትርፎላቸዋል። በንጉስ መሀመድ ሳድሳይ አመራር ስር የምትገኘዋ ሞሮኮ በተቃዋሚዎች ላይ ብርቱ ክትትል ይደረግባትና የጸጥታ ኃይላትም ጠንካራ ርምጃ ይወስዱባት ከነበረችው በቀድሞው ንጉስ በአባታቸው ዘመን ከነበረችው እጅግ የተሻለች ቦታ መሆንዋ የሞሮኮ ህዝብ አረጋግጦዋል።

Marokkos neuer König Mohammed VI.

ዘውድ የጫኑ ዕለት ንግግር ሲያሰሙ

ሰፊ ተነባቢነት ያለውና ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳረፈው ሳምንታዊው ጋዜጣ ቴል ኬል ዋና አዘጋጅ አህመድ ቤንሸምዚ ስለዛን ጊዜው ሲያስታውስ፡
« ዛሬ የምንጠይቀው የትኞቹ ጉዳዮች ናቸው የተከለከሉት ብለን ነው። ከአስር ዓመት በፊት ቢሆን ኖሮ ግን የትኞቹ ጉዳዮች ናቸው የተፈቀዱት ተብሎ ነበር የሚጠይቀው። ይህ ዓቢይ ለውጥ ነው። ነጻ ፕሬስን፡ አስተያየት በነጻ የመሰንዘርንና እና በይፋ መሰብሰብን በተመለከተ ሁኔታዎች በጉልህ ተሻሽለዋል። »
ይሁን እንጂ፡ ሌላውን የቤተ መንግስቱን ገጽታም የማየት ዕድል እንዳጋጠመው የሚናገረው ቤንሸምዚ ንጉሱ ባሰሙት አንድ ዲስኩር አኳያ በጻፈው ሂስ አዘል አንቀጽ የተነሳ ለምርመራ ቀርቦ ክስም እነደተመሰረተበት አመልክቶዋል። ገና እልባት ባላገኘው በዚሁ ክስ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ እስከ አምስት ዓመት እስራት ሊበየንበት ይችላል። ሞሮኮ ውስጥ በንጉሱ ስልጣን አንጻር አስተያየት መሰንዘር አሁንም በህግ ያስቀጣል። ይህም ቢሆን ግን ሀገሪቱ ባለፉት አስር ዓመታት ትልቅ ለውጥ አስመዝግባለች። የባህሉን ዘርፍ ብንመለከት ለምሳሌ ቤተ መዘክሮች ተከፍተዋል፡ የፊልሙ ኢንዱስትሪ ተስፋፍቶዋል፡ የሂፕ ሆፕ ዘፋኝ ቡድኖች ተቋቁመዋል። ዘፋኞች፡ የፊልም አዘጋጂዎች፡ ደራሲዎች ሁሉም ድሮ በፍጹም የማይነሱ የነበሩ ጉዳዮችን ያነሳሉ። ለዚህም በሀገሪቱ የሚታየው ሁኔታ የተመቻቸበት ሁኔታ ድርሻ ማበርከቱን የንጉሱ አማካሪ ኦንድሬ አዙላይ አስታውቀዋል።
«ንጉስ መሀመድ ሳድሳይ ስልጣን ከያዙ ወዲህ ያስገኙዋቸውን ለውጦች ለማሻሻል እና ለማጠነከር ነው የሚጥሩት። የሞሮኮ ህዝብ እየተሻሻለ፡ ተሀድሶ ለውጥ እያደረገ፡ ፖለቲካዊ፡ ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ መሻሻል እያስገኘ ከሄደ፡ የህዝቡ ፍላጎትም እያደገ መሄዱ አይቀርም፡ ይህ የሚጠበቅ ነው።
በሞሮኮ ካለፉት ዓመታት ወዲህ የቤተሰብ ህግ ተሻሽሎዋል። በተሻሻለው ህግ መሰረት ባለትዳር ሴቶች ተጨማሪ መብት አግኝተዋል፤ ለምሳሌ ፍቺን በተመለከተ። የሞሮኮ መሰረተ ልማትም ከአውሮጳ ህብረት በተገኘ ርዳታ አማካይነት ተሀድሶ ተደርጎበታል። ትላልቅ አውራ ጎዳኖዎች ተሰርተዋል። ፈጣኑ የኢንተርኔት መገናኛ ተዘርግቶዋል። የውኃ እና ኮሬንቲ አቅርቦትም እንዲሁ። ህብረቱ በምላሹ ርዳታ ተቀባይዋ ሀገር ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን እንድትተክልና የህግ የበላይነትን እንድታከብር ይፈልጋል። ሆኖም፡ ሞሮኮ ውስጥበዚሁ አኳያ ብዙም ለውጥ አልተደረገም። በብዙ ታዛቢዎች አመለካከት፡ ሞሮኮ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የምትከተል ሀገር አይደለችም። እርግጥ፡ በሀገሪቱ ብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢኖሩምና ሀገሪቱ በምክር ቤትና እና በጠቅላይ ሚንስትር ብትተዳደርም፡ በሀገሪቱ የሚተላለፉትን ውሳኔዎች ሁሉ የሚወስዱት ንጉሱ መሆናቸውን ነው የቴል ኬል ዋና ስራ አስኪያጅ አህመድ ቤንሸምዚ የሚያስረዳው።
« ንጉሱ ፍጹሙ ስልጣን አላቸው። ያረፈባቸው ብቸኛው ገደብ በህገ መንግስቱ የሰፈረው አንቀጽ አስራ ዘጠኝ ብቻ ነው። አንቀጹ እንደሚለው፡ በንጉሱ ስልጣን ላይ ሊያርፍ የሚችለውን ገደብ ሊያሳርፍ የሚችለው ንጉሱ ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር፡ የሞሮኮ የፖለቲካ ስርዓት መቀየር ካለበት፡ ይህን ለውጥ ማድረግ የሚችሉት ንጉሱ ራሳቸው ንጉሱ ብቻ ናቸው። »
በዚህም የተነሳ፡ ሞሮኮ የመንግስት አመራስ ለውጥ የሚኖር አይመስልም፡ ምክንያቱም፡ ንጉሱ በፖለቲካው ብቻ ሳይሆን በኤኮኖሚውም ዘርፍ አሁንም ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳሳረፉ ነው የሚገኙት።
ማርክ ዱገ/አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic