ምድርን ከኅዋ ቅኝት | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 25.05.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ምድርን ከኅዋ ቅኝት

ኅዋ ላይ ከጭለማው ወደ ብርሃናማው የምድር ጥግ በእየአንድ ሰአት ተኩሉ ከሚመላለሰው ዓለም አቀፉ የጠፈር ምርምር ጣቢያ ሆኖ ምድርን ደጋግሞ ቃኝቷል። ከ2 ዓመት በፊት በማዕከሉ ለ6 ወር ያኽል ቆይቷል። በ166ኛ ቀኑም ምድር ተመልሷል። የጣቢያው አዛዥ ሆኖ ከ2 ዓመት በኋላ ወደ ኅዋ እንዲመጥቅ ተሹሟል። ጀርመናዊው ጠፈርተኛ አሌክሳንደር ጌርስት።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:30
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:30 ደቂቃ

ጀርመናዊው ጠፈርተኛ አሌክሳንደር ጌርስት

ጀርመናዊ ጠፈርተኛ አሌክሳንደር ጌርስት የዓለም አቀፉ የጠፈር የምርምር ጣቢያ አዛዥ ሆኖ ወደ ኅዋ እንዲመጥቅ በቅርቡ ተሹሟል። ቀደም ሲል ከጣቢያው አስደናቂ ምስሎችን ለማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተከታዮቹ እና አድናቂዎቹ ወደ ምድር ሲልክ ነበር። ኮለኝ ከተማ በሚገኘው የጀርመን የበረራ እና የኅዋ ማዕከል ውስጥ ያለፈው ሣምንት ረቡዕ የጀርመን መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ተገኝተው ጠፈርተኛውን አወድሰዋል።

ከምድር በላይ በ400 ኪሎ ሜትር ርቀት ኅዋ ላይ እያረበበ የምንኖርባት መሬትን ይዞራል። በሰአት 28.000 ኪሎ ሜትር እየከነፈከዓለማችን አንዱ ጥግ ሌላኛው ጋጥግ ከተፍ ይላል። ዓለም አቀፉ የጠፈር ምርምር ጣቢያ (ISS)። ከእዚህ ጣቢያ ውስጥ ሆኖ ጀርመናዊው ጠፈርተኛ አሌክሳንደር ጌርስት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2014 ዓመት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የትዊተር እና የፌስቡክ የማኅበዊ መገናኛ አውታር ተከታዮቹን እለት በእለት ሲያስደምም ነበር። የምድር ምስሎችን በቀጥታ ከኅዋው ወደ ምድር እየላከ ብዙዎችን አስደንቋል። ዝግ የብረት አክምባሎ በሚመስለው፤ ግን ደግሞ በሁሉም አቅጣጫ መመልከቻ መስተዋት በተበጀለት እና ጣቢያው ላይ ተሰክቶ እንዳሻው በየትኛውም አቅጣጫ በሚጠማዘዘው ክፍል ውስጥ የምድርን አስደናቂ ገጽታ በተደጋጋሚ ቃኝቷል።

«በእውነቱ ይኽ አክምባሎዋማ ቅርጽ ያለው ክፍል ከገነባናቸው ቁሶች ሁሉ ምርጥ የምንለው ነው። ያለዚህ ክፍል ብዙ ነገር አዳጋች በሆነ ነበር። ከውጭ የምንመለከታቸውን ድንቅ እይታዎችንም ማግኘት ባልቻልን ነበር። አክምባሎዋማው ክፍል ባሰኘው አቅጣጫ 360 ዲግሪ ይሽከረከራል። የምድር ግማሽንም በ180 ዲግሪ ይመላለስባታል። እጅግ ሲበዛ ድንቅ ነው።»

ዓለም አቀፉ የጠፈር የምርምር ጣቢያ ላይ በተገጠመው ክፍሉ ውስጥ ሆኖ ጀርመናዊው ጠፈርተኛ በቀን ለ16 ጊዜያት ምድርን እየዞረ ተመላልሶባታል። በእየ አንድ ሰአት ተኩሉ ልዩነትም ከምድር ብርሃናማው ክፍል ወደ ጨለማው ደርሶ ተመልሷል። ተመልሶም ሄዷል።

ምድር ከዓለም አቀፉ የጠፈር የምርምር ጣቢያ ላይ ስትታይ

ምድር ከዓለም አቀፉ የጠፈር የምርምር ጣቢያ ላይ ስትታይ

በምሽቱ ድባብ እንቅልፋቸውን የሚያጣጥሙ ሰዎች ከሚበዙበት የዓለም ክፍል ተነስቶ ከማለዳው ብርሃን ጋር ለጥድፊያ ወደሚነቁት ምንዱባን ለመድረስ 90 ደቂቃ ብቻ ይበቃዋል። ለጀርመናዊ ጠፈርተኛ አሌክሳንደር ጌርስት የኅዋ ማዕከሉ አክምባሎዋማ ክፍል ውስጥ ሆኖ ምድርን ሲሽከረከር እመሬት ላይ የሚቀያየረው እይታ ፍጹም ልዩ ነው።

«አክምባሎዋማው ክፍል ከኅዋ ምርምር ማዕከሉ ጋር እንደተጣበቀ በመጀመሪያ ወደ ምድር አቅጣጫ ተዘቅዝቆ ይጓዛል። ከዚያም ድንገት በመሬት ሌላኛው አቅጣጫ ሲዞር እና ምድርም ከአናት በላይ ተዘርግታ ስትንሳፈፍ ማየቱ እጅግ አስደናቂ ነው። በምሽት ወቅት ይህ እይታ ልዩ ነው። በተለይ አንዳችም ብርሃን በማይታይበት የሰላማዊ ውቅያኖስ ጭለማማ አቅጣጫ ሲዞር ምድር ልክ እንደ ግዙፍ ጸሊም አክምባሎ ጭንቅላት ላይ የተደፋች ነው የምትመስለው። አንዳች የሞት ጥላ በጥቁር ግዙፍ አክምባሎ ተመስሎ አናት ላይ የሚንሳፈፈፍ ስለሚመስል እይታው አንዳንዴ አስፈሪ ነው»

ጠፈርተኛው ከኅዋ የምርምር ጣቢያው አቅጣጫ ቁልቁል ሲቃኝ ኢትዮጵያን ጨምሮ ምሥራቅ አፍሪቃ የምሽት እይታው ምን እንደሚመስል ባይገልጥም፤ አውሮጳ ግን እኩለ-ሌሊት ላይ በብርሃን ስትሽቆጠቆጥ በተደጋጋሚ አይቷል።

«በምሽት በአውሮጳ በኩል ሲታለፍ፤ በብርሃናት የተጥለቀለቀች ባሕር ነው የምትመስለው። ብርሃናቱን በመመልከት ብቻ እያንዳንዱን ሃገር መለየት ይቻላል። ከእኛ ዘመን ሁለት መቶ ዓመታት በፊት እይታው ምን ይመስል ነበር ተብሎ ቢታሰብ አሁን በብርሃን የሚሽቆጠቆጠው ክፍል ያኔ ምን ያኽል በጭለማ የተዋጠ እንደነበር መገመት ይቻላል።»

ሰሜን ጣልያን በምሽት ከዓለም አቀፉ የጠፈር የምርምር ጣቢያ የተነሳ ፎቶ

ሰሜን ጣልያን በምሽት ከዓለም አቀፉ የጠፈር የምርምር ጣቢያ የተነሳ ፎቶ

ጠፈርተኛው ከዚህ ክፍል ውስጥ ሆኖ ምድርን በተደጋጋሚ አንዴ ቁልቁል እየቃኘ ሲሻው ደግሞ ሽቅብ ማትሯታል። የሰው ልጅ ከጋዛ እስራኤል የሮኬት ድብደባ እስከ ሶሪያ ጦርነት እርስ በእርስ ለመገዳደል ሲጣደፍ የሚፈጠሩ ብልጭታዎችን ከላይ ሆኖ እንደ ዘበት ቃኝቷል። የብራዚሉ አማዞን ጥቅጥቅ ደን በአስደንጋጭ ሁኔታ መጨፍጨፉን እንደ መጽሐፍ እያገላበጠ ተመልክቷል። እይታውንም አስደናቂ በተባለላቸው ፎቶዎቹ እና የቪዲዮ ምስሎቹ መዝግቦ ዓለምን አስደምሟል፤ ጀርመናዊው ጠፈርተኛ። በከፍተኛ ደረጃ የተጨፈጨፈው የአማዞን ደን አደጋን የሚያሳየው ምስሉ በእርግጥም አደጋው የከፋ መሆኑን አመላካች ነው።

«የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ እያንዳንዱ ተሳታፊን ወደ ኅዋ የምርምር ማዕከሉ ወስዶ ለሰአታት ቁልቁል አማዞንን እንዲመለከቱ ማድረግ ይገባል። ያ ቢደረግ አንዳንድ ዓለም አቀፋዊ ውሳኔዎች በተለየ መልኩ ውሳኔ በተደረሰባቸው ነበር።»
አሌክሳንደር ጌርስት ከኅዋ በሚልካቸው ፎቶዎቹ በርካታ አድናቂዎቹን ማስደመም ችሏል። እናም ውብ ፎቶዎችን ብቻ አይደለም ለሌሎች የሚያጋራው፤ የምድር አስደንጋጭ ገፅታንም ያካፍላል። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2014 ሐምሌ ወር ላይ ቁልቁል ወደ ምድር ሲቃኝ ያስተዋለው አንዳች ክስተት ግን እጅግ አስደንግጦታል።

«ለነገሩ ድንገት ነው ያየሁት። በመስኮት በኩል እንደ አጋጣሚ ቁልቁል ስመለከት ከዚህ ቀደም የማላቀውን ነገር አየሁ። ወደ ምድር ሲታይ የሆነ የሚንቀሳቀስ ነጥብ ሆኖ አልፎ አልፎ ድንገት ብልጭ ይላል። መጀመሪያ ላይ የት እንደሆነ ማወቅ አልቻልኩም ነበር። ቀስ እያልኩ ነገሩን ሳጤነው ለካ የምመለከተው ሰዎች እርስ በእርስ ሲጨራረሱ ኖሯል።»

የዓለም አቀፉ የጠፈር የምርምር ጣቢያ ውስጥ ተመራማሪው አሌክሳንደር ጌርስት

የዓለም አቀፉ የጠፈር የምርምር ጣቢያ ውስጥ ተመራማሪው አሌክሳንደር ጌርስት

ጀርመናዊው ጠፈርተኛ ከጋዛ ሠርጥ ወደ እስራኤል ይወነጨፉ የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን ተመልክቷል። በሶሪያ ጦርነት በርካቶችን ለእልቂት የዳረጉ ፍንዳታዎችን ታዝቧል። የምንኖርባት ምድር ምን ያኽል ውብ እናም ደግሞ ለአደጋ የተጋለጠች መሆኗን ከላይ ሆኖ በሚያነሳቸው ምስሎቹ አሳይቷል። አሌክሳንደር ጌርት ወደ ኅዋ ምርምር ጣቢያው በመንኲራኲር አቅንቶ ለስድስት ወራት ገደማ የቆየው ሰማያዊ ነጥብ (blue dot) በተሰኘው ተልዕኮ ስር ነበር።

«ተልዕኮውን ሠማያዊ ነጥብ የሚል ስያሜ የሰጠነው መሬት ከምድር ውጪ ስትታይ ያላትን ገጽታ በመንተራስ ነው። መሬትን ከምድር ንፍቀ-ክበብ ውጪ ሆነን ስንመለከታት ማብቂያ በሌለው ጽልመት መሀል ያለ ጥበቃ ወዲያ ወዲህ የምትርገበገብ ሰማያዊ ነቁጥ ሆና ነው። እናም እይታው በእውነቱ ለእኛ ዋጋ ያለው ነው። ለመሆኑ እኛ ማን ነን? ምድራችንስ ለፍጥረተ-ዓለም (Universe) ዋጋዋ እስከምን ድረስ ነው? በእርግጥ ምንም ማለት ይቻላል፤ ግን ይህች ፕላኔት ለእኛ ለሰው ልጆች ምን ያኽል ጠቃሚ ናት። ሁሉም ነገራችን እኮ ናት። ሌላ አማራጭ የለን፤ መኖሪያችን።»

ሰማያዊ ነጥብ ምድር ከ6 ቢሊዮን ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ቮዬጀር አንድ (Voyager 1) በተሰኘው መንኲራኲር በተደጋጋሚ ፎቶ ከተነሳች በኋላ ለተመረጠው ምስል የተሰጠ ስያሜ ነው። ሰማያዊ ነጥብ ምስል ይፋ የሆነው እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1990 ዓመት ነው። በሰማያዊ ነጥብ ተልዕኮ በኅዋ ምርምር ሲያደርግ የቆየው ጀርመናዊ ጠፈርተኛ ዓለምን እውስጧ እየኖረ እና ከውጪ ሲመለከታት የተሰማውን ስሜት እንዲህ ይገልጣል።

«የኅዋ ጉዞው ለእኔ እንደ ሰው በውስጤ የፈጠረብኝ ነገር አለ። ሁሉን ነገር ምድር ውስጥ ሆነን ስንመለከት እያንዳንዱ ነገር እጅግ ግዙፍ የሆነ፤ምንም ማብቂያ የሌለው፣ የተፈጥሮ ሀብቱ የማያልቅ፣ ከባቢ አየሩም በጣም ሰፊ ነው የሚመስለው። ምድርን ከውጭ ሆኖ ሲመለከቷት ግን ሁሉም ነገር ትክክል እንዳልሆነ ወዲያው ነው ግልጥ የሚሆነው። ሁሉም ነገር አላቂ እንደሆነ፤ ምድራችንም ትንሽ እንደሆነች፣ እውስጧ ያለው ነገር በመላም የተወሰነ መሆኑ፤ የምንጠቀመው ነገር በአጠቃላይ በአንድ ወቅት እንደሚያልቅ እና እንደሚያከትምለት ግልጽ ይሆንልሀል።»

ጠፈርተኛው አሌክሳንደር ጌርስት ለጀርመን መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል የምርምር ጣቢያውን ሲያስጎበኝ፤ ኮሎኝ ከተማ

ጠፈርተኛው አሌክሳንደር ጌርስት ለጀርመን መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል የምርምር ጣቢያውን ሲያስጎበኝ፤ ኮሎኝ ከተማ

አሌክሳንደር ጌርስት ተምሮ የተመረቀው በምድር እና አካባቢዋ ጥናት ፊዚክስ (Geophysics) እንዲሁም በእሳተ-ገሞራ ምርምር የሞያ ዘርፍ ነው። ገና ህጻን ልጅ ሳለ ምድር እንዴት ተከሰተች፣ አውሎ ንፋሳት፣ የምድር ነውጥ እንዴት ነው የሚፈጠሩት የሚሉ ጥያቄዎች ይመስጡት እንደነበረም ተናግሯል። እናም አሁን ምድርን ከውስጧ ሳይሆን ከውጪዋ ሆኖ መመራመሩ እንደሚያስደስተው ገልጧል።

ጀርመናዊ ጠፈርተኛ አሌክሳንደር ጌርስት የዓለም አቀፉ የጠፈር የምርምር ጣቢያ ውስጥ ሆኖ 160 የተለያዩ ቤተ-ሙከራዎችን አከናውኗል። ኅዋ ላይ ያከናወናቸው ምርምሮቹ በአብዛኛው ምድር ላይ ቢሆን እውን ሊሆኑ የማይችሉ ናቸው። ለአብነት ያኽልም ከሁለት እስከ ሦስት ሺህ ዲግሪ ሴንቲግሬድ በሚደርስ ሙቀት የቀለጠ የብረት ፍሳሽን አየር ላይ ለበርካታ ደቂቃዎች በማንሳፈፍ ብረቱ የተዋቀረበት ገጽታን ማጥናት ይገኝበታል። መሰል ምርምር በኅዋ ውስጥ ስበት ስለሌለ ስኬታማ ሊሆን ይችላል።

ምድር ላይ ግን የትኛውም ያኽል ገንዘብ ቢፈስ የሰው ልጅ አሁን ባለው ስልጣኔ መሆን የማይችል ነው። መረጃዎቹን በኮምፒውተር ወደ ምድር በመላክም መሬት ላይ መተንተን ይቻላል። እንዲህ አይነት ረቂቅ ጥናቶችን ለማከናወን ጠፈርተኛው አሌክሳንደር ጌርስት ዳግም ወደ ኅዋ ይመጥቃል። ያኔ ግን ተግባሩ መመራመር ብቻ ሳይሆን የኅዋ ጣቢያውንም ለተወሰነ ጊዜ ማስተዳደር ይሆናል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic