«ምድራዊው ማርስ» በአፋር | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 22.06.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

«ምድራዊው ማርስ» በአፋር

ከዓለማችን እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ በሚነገርለት እና አሳተ-ገሞራ የሚተፋ ከፍተኛ ሙቀት ባለበት የአፋር ማዕዘናዊ ረባዳ ስፍራ ሕይወት ያላቸው ነገሮች መኖራቸው ተገልጧል። ግኝቱ የተነገረው በወጣቷ ኢትዮጵያዊት ተመራማሪ ወይዘሪት ሉሊት ጥላሁን ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:49

ሕይወት በአፋር ማዕዘናዊ ሥፍራ

ከኤርትራ የዳህላክ ደሴቶችን ይዞ በቀይ ባሕር ጠረፍ ታች ታቹን አሰብን ይሻገርና ጅቡቲን ያጠቃልላል። ወረድ ብሎም ከፊል የሶማሊያ ሰሜናዊ የባሕር ጠረፎችንም ይነካል። እንዲህ ከሰሜን ደቡብ የቀይ ባሕር ጠረፈማ መሬቶችን እየታከከ የተዘረጋው መስመር ወደ ጎን ወደ ኢትዮጵያ እየጠበበ በመግባት አፋር ውስጥ ሲደርስ የሦስት ማዕዘን ቅርጽ ይዞ ይገናኛል። የአፋር ማዕዘን፤ ብዙዎች የአፋር ስምጥ ሸለቆ ይሉታል። በዝቅተኛነቱ ከዓለማችን ወደር የማይገኝለት ይኽ እንደ ነበልባል የሚፋጅ ሞቃታማ ስፍራ ለሕይወት እጅግ አስቸጋሪ ነው። ሕይወት ያለው ነገር ይኖራል ተብሎ በማይታሰብበት በዚህ ፈታኝ ስፍራ ግን ሕይወት መኖሩ ተነግሯል።

«የምድራዊ ገጽታ በደንብ አታይበትም። በቃ ሌላ ዓለም ላይ የሄድክ ነው የሚመስለው» ሲሉ መደመማቸውን የገለጡት ኢትዮጵያዊቷ ተመራማሪ ሉሊት ጥላሁን፤ ምርምራቸውን ባከናወኑበት የዳሎል ረባዳ ስፍራ የሚገኘው እሳተ ገሞራ በጨው ክምር ውስጥ እንደሚገኝ ተናግረዋል። «ይኼ ዳሎል የምንለው እሳተ ገሞራው ከከርሰ ምድር የሚፈልቁ የጨው አይነቶች ከላይ ሸፍነውት እሳተ ገሞራውን በቀላሉ ማየት አትችልም በዐይን። ከሥር እየተራመድከው ነው የምትሄደው» ሲሉም አክለዋል።

የአፋር ማዕዘናዊ ረባዳማ ስፍራ ልዩ መልክአ ምድር፤ የውጭ ሀገር ተመራማሪዎች ቦታውን «ምድራዊው ማርስ» ሲሉ ይገልጡታል።

የአፋር ማዕዘናዊ ረባዳማ ስፍራ ልዩ መልክአ ምድር፤ የውጭ ሀገር ተመራማሪዎች ቦታውን «ምድራዊው ማርስ» ሲሉ ይገልጡታል።

የመልክአ ምድር አጥኚዎች እና የከርሰ ምድር ተመራማሪዎች የአፋር ሰሜናዊ ማዕዘንን «ምድራዊው ማርስ» ሲሉ ይጠሩታል።
እነዚህ በአፋር ማዕዘናዊ ረባዳማ ስፍራ፤ በእሳተ ገሞራው እየፈሉ የሚወጡት የደናከል ጥልቅ ውኃማ አካላት ለዐይን ማራኪ የሆኑ የተለያዩ ቀለማት ያላቸው ንጥረ ነገሮች ይገኙባቸዋል። ንጥረ ነገሮቹ ውስጥ ሕይወት ያላቸው ደቂቃን (microorganism) ተቀይጠው እንደሚገኙ አስደማሚውን ግኝት ያበሰሩት ኢትዮጵያዊቷ ወጣት ተመራማሪ ሉሊት ጥላሁን ናቸው።

ተመራማሪዋ የመስክ ጥናት ስላከናወኑበት አካባቢ ገጽታ ሲያብራሩ «አይደለም ሕይወት ሊኖር በጣም ለሕይወት አደገኛ ተብሎ የሚታሰብ ቦታ ነው» ሲሉ አደገኛነቱን ገልጠዋል። የዛሬ ሁለት ዓመት ናሙናዎችን ለመሰብሰብ ወደ ቦታው ሲያመሩም በአካባቢው ሕይወት አለ የለም የሚል የጦፈ ክርክር አድርገውም ነበር ከቡድኑ አባላት ጋር። አካባቢው እጅግ አስቸጋሪ ከመሆኑ የተነሳም ከወይዘሪት ሉሊት ጋር ወደ ቦታው አብረው ያቀኑ የአጥኚ ቡድኑ አንዳንድ አባላት አካባቢው ላይ ሕይወት አይኖርም ብለው ነበር። «አይደለም ሕይወት ያለው ነገር ሊኖር ይቅርና ለመመርመሪያ የወሰድናቸው መሣሪያዎች እንኳን ሲበላሹ፣ ወይም ከዚህ በፊት ተበላሽቶባቸው ሲማረሩ እንሰማለን» ያሉት ወጣቷ ተመራማሪ ከቦታው በጥንቃቄ በአውሮፕላን አጓጉዘው የወሰዱትን ናሙና ቤተ ሙከራ ውስጥ ሲመለከቱት ያዩትን ማመን አቅቷቸው ነበር። «ሕይወት ያለው ነገር በውስጡ ሲተራመስ ስናይ እኔ በበኩሌ እንባ እንባም ብሎኝ ነበር» ሲሉም አክለዋል።

ኢትዮጵያዊቷ ወጣት ተመራማሪ ሉሊት ጥላሁን በአፋር ማዕዘናዊ ረባዳማ ስፍራ

ኢትዮጵያዊቷ ወጣት ተመራማሪ ሉሊት ጥላሁን በአፋር ማዕዘናዊ ረባዳማ ስፍራበደናከል ረባዳማ ስፍራ ውኃማ አካላቱ ከጨው ግግር ስር ነው የሚገኙት። ከጨዋማው ግግር ስር ንቁ እሳተ-ገሞራ እንደሚንተከተክ ይነገራል። ጨዋማው ግግር ሲረገጥ እያፈተለከ የሚወጣው ውኃማ አካል ከፍተኛ የአሲድነት ጠባይ አለው። በዓለማችን ዝቅተኛ እንደሆነ የሚነገርለት የአፋር ማዕዘን ከባሕር ጠለል በታች 155 ሜትር ላይ ይገኛል።

ከወርሃ ግንቦት እስከ ጥቅምት መጨረሻ ድረስ የአፋር ማዕዘናዊ ረባዳማ ስፍራ ንዳድ እስከ 65 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሚደርስበት አጋጣሚ አለ። «በዚህን ወቅት በአካባቢው መገኘት በራስ ላይ እንደመፍረድ ይቆጠራል» ሲሉ ተመራማሪዋ የሙቀቱን አስቸጋሪነት ገልጠዋል። በዘመናዊ መሣሪያዎች ዐየሩን ተመጣጣኝ አድርገው በቦታው ላይ ምርምር የሚያደርጉ ድርጅቶች ግን አይጠፉም። ቀደም ሲል በቦታው ላይ ሕይወት እንደሚገኝ ቢቢሲ ዘግቦ ነበር። የወጣቷ ምርምር ቀደም ሲል ከቀረበው ዘገባ በምን ይለያል? ወጣቷ ተመራማሪ፦ «እነሱ የወሰዱት ናሙና እዛ አካባቢ ካሉት አፈር ነው። እኔ ደግሞ የወሰድኩት፤ ሕይወት መኖሩን ያረጋገጥኩት ከውኃማው አካሉ ነው፤ ሕይወት ሊኖር አይችልም ተብሎ ከታሰበበት ነው።»

በአፋር ስምጥ ሸለቆ የደንከል ረባዳ ስፍራ ላይ የተወሰደው ናሙና በአጉልቶ መመልከቻ መነጽር እይታ እና በሌሎች መሣሪያዎች ጥልቅ ጥናት እና ምርምር ተደርጎበት አንድ እመርታ ላይ መደረሱ ተገልጧል።

ኢትዮጵያዊቷ ወጣት ተመራማሪ ሉሊት ጥላሁን በአፋር ማዕዘናዊ ረባዳማ ስፍራ ከሌሎች ተመራማሪ የቡድኑ አባላት ጋር

ኢትዮጵያዊቷ ወጣት ተመራማሪ ሉሊት ጥላሁን በአፋር ማዕዘናዊ ረባዳማ ስፍራ ከሌሎች ተመራማሪ የቡድኑ አባላት ጋርይኽ የምርምር ውጤት ወደፊት በሌላ ዓለም ላይ ሕይወት መኖር አለመኖሩን ለመፈተሽ እገዛ ያደርጋል ተብሏል። የደንከል ረባዳ ስፍራ እሳተ ገሞራ እንቅስቃሴ እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል። በአካባቢው የሚገኙ ነገሮች በፈጣን ሁኔታ በሚለዋወጡበት ስፍራ ላይ ሕይወት ያላቸው ነገሮች መገኘታቸው ለቀጣይ ምርምር በር ከፋች እንደሆነ ወጣቷ ተመራማሪ ተናግረዋል።

እጅግ ዝቅተኛ፣ እጅግ ሞቃታማ፣ እጅግ አሲዳማ በሆነው በዚህ ረባዳማ ስፍራ ሕይወት ያለው ነገር እንዴት እና መቼ ሊከሰት ቻለ? የሣይንሱ ዓለም እንቆቅልሹን ለመፍታት ሌት ተቀን እየባዘነ ነው። ምናልባት እንቆቅልሹ በኢትዮጵያዊቷ ወጣት ተመራማሪም ሊፈታ ይችል ይኾናል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ


Audios and videos on the topic