ምድራችንና የስባሪ ከዋክብት አደገኝነት | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 20.02.2013
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ምድራችንና የስባሪ ከዋክብት አደገኝነት

ባለፈው ሳምንት ዓርብ፤ ከኅዋ በኩል ሁለት አስገራሚም፣ አስደንጋጭም ዜና ለፕላኔታችን ደርሷት ነበር። አንድ የኳስ ሜዳ የሚያክል ፣ 65 ሜትር ርዝማኔ ያለውና 400,000 ቶን ያህል የሚመዝን ስባሪ ኮከብ ከጨረቃ ምኅዋር 15 እጥፍ ለመሬት ቀረብ በማለት፣

default

ፕላኔታችንን አቋርጦ በመወንጨፍ፣ ይኸው ፤ «2012 DA 14» የሚል መለያ ስያሜ የተሰጠው ግዙፍ የስባሪ ኮከብ አካል፣ ከምድራችን ጋር ሳይላተም፣ እንዲሁ አስፈራርቶን በ 28 ,000 ኪሎሜትር ገደማ ርቀት የያዘውን ምኅዋር እንደጠበቀ ገልል ብሎልናል ። ከኅዋ ተስፈንጥሮ ከባቢ አየራችንን ሰንጥቆ መሬት ላይ የወደቀው አካል ፣ በእርግጥ የስባሪ ኮከብ አካል ወይስ ሰው የሠራው ብረታ ብረት ቢጤ ነው?

ኃይለ ቃል በመናገር የታወቁ ናቸው የሚባሉት ፣ የሩሲያ ብሔርተኛ ፓርቲ መሪ፣ ቫላዲሚር ዥርኖቭስኪ፣« ከኅዋ የወደቀ ስባሪ ኮከብ የለም፤ አሜሪካውያን ለፍተሻ የተኮሱት አዲስ ጦር መሳሪያ » ነው ማለታቸው ነው የተጠቀሰው። የሩሲያ የሳይንስ አካደሚ አባላት ግን የሥነ ቅመማ ፍተሻ በማድረግ ፤መሬት ላይ ያረፉት ጠጠሮች ምንጫቸው ኅዋ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ፤ ነው ያሉት። በዑራል ፌደራል ዩንቨርስቲ የተካሄደውን የኅዋ ጠጠር ፍለጋ የመሩት ቪክቶር ግሮኮቭስኪ እንደገለጹት 50 ጥቃቅን ጠጠሮችን ለመሰብሰብ ተችሏል።

በሥነ ፈለክ ጠበብት፣ ንዑስ ፕላኔት ተብሎ ልዩ ስያሜ ስለተሰጠው ስባሪ ኮከብ በዳርምሽታት፤ ጀርመን ፤ የአውሮፓ የኅዋ ምርምር ድርጅት የኅዋ በረራ ጉዳይ ኢንጅኔር ራይነር ክሬስከን---

«ንዑሱ ፕላኔት 2012 DA 14 ---ወርዱ 50 ሜትር ሲሆን፤ ምናልባት ሙሉ- በሙሉ ዐለት ወይም ድንጋይ ነው። ስባሪ ከዋክብት በረዥሙ የፍጥረተ-ዓለም ታሪክ ከመሬት ጋር የተላተሙበት አጋጣሚዎች ነበሩ። ከኅዋ የሚወረወሩ አካላት ከሞላ ጎደል በሺ ዓመት አንድ ጊዜ ከመሬት ጋር ይጋጫሉ። ዩናይትድ እስቴስ ውስጥ በ አሪዞና ግዛት፤ አንድ ከሞላ ጎደል ክብ ቅርጽ ያለው የተደረመሰ ጉድጓድ መሰል ቦታ አለ። ይህም በስባሪ ኮከብ የተደረመሰ፤ 3 ኪሎሜትር ወርድ ያለው ነው። ይህን የመሰለ ጉድጓድ ሊፈጥር የሚችል መሬትን የሚሰረጉድ አደጋ ምንጊዜም ሊያጋጥም ይችላል። ያን መሰል የሰማይ አካል ዐቢይ ጥፋት ሊያስከትል ይችላል፤ ነገር ግን ዓለም አቀፍ ውድመት ተደርጎ የሚታይ አይደለም። »

ሩሲያ ዕጣ ፈንታዋ ሆኖ ከ 105 ዓመታት በኋላ እንደገና በአስደንጋጭ ሁኔታ ኅዋ ባሰወነጨፈው ድንጋይና ፣ ከባቢ አየራችን ውስጥ ሲደርስ ፣ በተፈረካከሰ ጠጠር ተመትታለች።

ባለፈው ዓርብ ፣ ሩሲያ ውስጥ በዑራል ተራሮች፤ ከመሬት 20 ኪሎሜትር ገደማ ርቀት ላይ የፈነዳ የስባሪ ኮከብ ፍርካሽ ፣ 5 ክፍላተ ሀገራትን አስጨንቆ ፣ ጠጠር እንደ በረዶ በማዝነም ፣ ያው የኮከብ ፍርካሽ ከምድር ጋር ተላትሞም ባስከተለው ፍንዳታና ነውጥ 1,500 ሰዎች ከመጎዳታቸውም ፣ 5,000 ያህል ቤቶች ፣ በተለይም የብዙ ህንጻዎች ጣሪያ መፈራረሱና መስኮቶች መድቀቃቸው ታውቋል።

እንደ አውሮፓ የኅዋ ምርምር ድርጅት ገለጣ፤ ከባቢ አየር ላይ የፈነዳው ስባሪ ኮከብ 17 ሜትር ወርድ፤ እንዲሁም ከ 7,000-10,000 ቶን የሚመዝን እንደነበረና ፣ ዑራል ውስጥ፣ ቸልያቢንስክ በተባለ ቦታ ተፈረካክሶ ሲወድቅ ፤ ፍንዳታ ከማስከተሉም፣ በአካባቢው በሚገኙ ቢያንስ በ 6 ከተሞች ላይ ነው ጉዳት ያደረሰው። አንዳንድ የከተሞቹ ኑዋሪዎች ያነሷቸው የግል ተንቀሳቃሽ ምስሎች ፣ ነጸብራቅ የነበረው ነጭ የጋለ ድንጋይ ዝቅ ብሎ አየር ላይ ሲጎን አሳይተዋል። ። የስባሪ ኮክቡ ፍርካሽ ዝቅ ብሎ ሲጎን የተመለከቱ የአካባቢው ኑዋሪዎች እጅግ ተጨንቀውና በፍርሃት ተውጠው ኅልፈተ ዓለም የተከሠተ መስሎአቸው እንደነበረ ነው በዕለቱ የተገለጠው።

የሩሲያ ፌደራሲዮን ብሔራዊ የድንገተኛ አደጋ መከላከያና የሲቭሎች ደኅንነት ጥበቃ ማዕከል ባልደረባ ፤ ቭላዲሚር እስቴፓኖቭ ያኔ እንዲህ ነበር ያሉት---

«በዑራል ፌደራላዊ ግዛት፤ በ ኩርጋን፤ ቸላያቢንስክ፤ ስቬርድሎቭስክ እና ቱመን አካባቢዎችእንዲሁም በካዛኽስታን ግዛት ከስባሪ ኮከብ የተፈረካከሰ ጠጠር እንደበረዶ ወርዶባቸዋል። ይህም በህንጻዎችና በመስኮቶች ላይ ጉዳት አድርሷል። »

ስብርባሪ ከዋክብት መጠናቸው አነስተኛም ቢሆን ፤ ሊያደርሱ ስለሚችሉት ብርቱ ጉዳት ፤ ከዳርምሽታት ፣ ጀርመን ፤ የአውሮፓ የኅዋ ምርምር መ/ቤት ተጠሪ ራይነር ኬርስከን ፣ እንዲህ ማለታቸው የሚታወስ ነው።

«ራቅ ካለው ኀዋ ወደምድራችን ተስፈንጥሮ የሚወድቅ ማንኛውም ገዝፍ ያለው አካል ፍጥነቱ በሴኮንድ ፤ ቢያንስ 11,2 ኪሎሜትር ነው።ይህ ደግሞ ብርቱ የስበት ኃይል ነው ያለው። የብስ ላይ ሲጋጭ የሚመነጨው ኃይል መጠን ወሰን የለውም። የሚያስከትለው ጥፋትም በቀላል የሚገመት አይሆንም።»

ከስባሪ ኮከብ ተፈረካክሶ አየር ላይ የተበታተነው ጠጠር ፣ ጉልበቱ ፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ ላይ ሂሮሺማ ፤ ጃፓን ላይ ከተወረወረው የአቶም ቦንብ በ 30 እጥፍ የሚበልጥም መሆኑ ነው የተነገረለት።

ከኅዋ፤ የምድር ከባቢ አየርን ጥሶሰው መሬት ላይ በመውደቅ ብርቱ ጥፋት ሊያስከትሉ የሚችሉ የስባሪ ከዋክብትን አደጋ እንዴት መከላከል ይቻላል? የ ESA ባልደረባ ዴትሌፍ ኮሽኒ፣ አንድ የኅዋ አካል መሬት ላይ ከመውሰቁ በፊት በጥቂት ሰዓቶች ልዩነት ሁኔታውን አጣርቶ በማወቅ ማስጠንቀቂያ ማቅረብ ይቻላል ባይ ናቸው። ለዚህም እንደ ምሳሌ የጠቀሱት በሱዳን በረሃ እ ጎ አ በ 2008 ዓ ም የወደቀውን ከኅዋ የተወነጨፈ አካል ከመሬት ጋር ከመላተሙ 20 ሰዓቶች ቀደም ብሎ ማወቅ ተችሎ እንደነበረ ነው።

09.04.2010 DW-TV Projekt Zukunft Meteoriten 04

ግንባር ቀደም የኑክልየር ባለቤቶች ፣ ዩናይትድ እስቴትስና ሩሲያ ፣ ፕላኔታችንን የሚያሠጋ ከኅዋ የሚወነጨፍ አካልን ፤ አንድም ከሩቁ ሚሳይል በተጠመደ መንኮራኩር በማንጎድ አደጋውን ማስቀረት ወይም መቀነስ ፤ አለበለዚያም አደጋ ሊያደርስ የሚችል አካል በኅዋ ላይ እንዳለ ምኅዋሩን እንዲለውጥ በማድረግ፤ አማራጭ መፍትኄዎችን መሻት እንደሚችሉ ነው የሚነገረው።

ስባሪ ከዋክብት እንደሚባለው፤ ከ 4,6 ቢልዮን ዓመታት ገደማ በፊት ፀሐይና ተጫፋሪዎችዋ ፕላኔቶች ፈር ሲይዙ ፣ እንደተፈረካከሱ የቀሩ የፕላኔቶችና የከዋክብት አካላት ናቸው።

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 20.02.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17iMI
 • ቀን 20.02.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17iMI