ምዕራብ ሃገራትና የሴት ልጅ ግርዘት ስጋት | ጤና እና አካባቢ | DW | 17.02.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

ምዕራብ ሃገራትና የሴት ልጅ ግርዘት ስጋት

አፍሪቃ ዉስጥ በየዓመቱ 3 ሚሊዮን የሚሆኑ ልጃገረዶች በዘልማዳዊዉ የአኗኗር ይትበሃል መሠረት የመዋለጃ አካላቸዉ ይተለተላል ወይም ለዚህ ችግር የተጋለጡ መሆናቸዉን የዓለም የጤና ድርጅት ይገልፃል።

በ28 በአብዛኛዉ የአፍሪቃ ሃገራት እንዲሁም በመካከለኛዉ ምሥራቅና እስያ ዉስጥ የሚፈፀመዉ የሴትን ልጅ የመዋለጃ አካል የመተለልተል ጎጂ ልማድ ወይም Femail Genital Mutilation አፈፃፀሙ ሶስት ዓይነት እንደሆነ ነዉ ድርጊቱን በቅረበት የመረመረ ጥናት የሚገልፀዉ። የዓለም የጤና ድርጅት በመላዉ ዓለም ከመቶ እስከ 140 ሚሊዮን የሚገመቱ ልጃገረዶችና ሴቶችም ከተጠቀሱት ሶስት የግርዘት ዓይነቶች አንዱ እንደተፈጸመባቸዋል ያመለክታል። በተጨማሪም አፍሪቃ ዉስጥ 91,5 ሚሊዮን ልጃገረዶችና ሴቶች ለዚሁ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት የተጋለጡ መሆናቸዉን በቅርቡ የወጡ መረጃዎችን ያመለክታሉ። በተለይ ይህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ከሚፈጸምባቸዉ አካባቢዎች ምሥራቅ እና ሰሜን ምዕራብ አፍሪቃ ዉስጥ እጅግ ሥር መስደዱም ይነገራል። ከእነዚህ ሃገራት አንዷ በሆነችዉ ታንዛኒያ በቅርቡ የወጡ መረጃዎች ከኬንያ ጋ በሚጎራበተዉ ሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል ባለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ከግርዛት አምልጠዉ ወደሌላ አካባቢዎች ለመሰደድ የተገደዱት ልጃገረዶች ቁጥር 634 ደርሷል። ከዚያ ቀደም ብሎ በነበረዉ ዓመትም እንዲሁ የዚህ ግማሽ የሚያህሉቱ በሽሽት ራሳቸዉን ማዳን መቻላቸዉ ሰሞኑን ተሰምቷል። በአንፃሩ ይህን ለማስቆም እንቅስቃሴ ከተጀመረ በኋላ ደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብና ሰሜናዊ አፍሪቃ ዉስጥ የሚገኙ በርካታ ሃገራት ድርጊቱን ከመፈፀም መታቀባቸዉ እየታየ ነዉ።

Sensibilisierung im Dorf mit einem Theaterstück FGM

ጊኒ ዉስጥ ድርጊቱ ሲፈጸም

ምንም እንኳን የሴት ልጅን የመዋለጃ አካል መተልተልን ለማስቆም የተለያዩ እንቅስቃሴዎች በዓለም እና አገር አቀፍ ደረጃ ቢካሄዱም እስካሁን ግን ጨርሶ መፈፀሙን ለማስቆም አልተቻለም። እንደዉም ይኸዉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት የአፍሪቃና የመካከለኛዉ ምሥራቅ ጉዳይ ብቻ መሆኑ ቀርቶ አዉሮጳና አሜሪካንም ስጋት ዉስጥ ከከተተ ከራረመ።

ከአንድ ሳምንት በፊት ይህን ድርጊት የማስቆሙ እርምጃ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታሰብ ከኒዉዮርክ የወጣ ዘገባ ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ ለግርዛት የተጋለጡ ወይም የሚያሰጋቸዉ ልጃገረዶችና ሴቶች ቁጥር ካለፉት 15 ዓመታት ወዲህ ከግማሽ ሚሊዮን መብለጡን ይፋ አድርጓል። ቁጥሩ የበዛበት ዋናዉ ምክንያትም እንደዘገባዉ ይህ በባህል ስም የሚፈፀም የጭካኔ ድርጊት ከተስፋፋባቸዉ የአፍሪቃ ሃገራት ወደአሜሪካ የሚገቡ የተሰዳጆች ቁጥር ከፍ በማለቱ ነዉ። ለትርፍ ያልቆመዉ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የስነኅዝብ የመረጃ ቢሮ የፆታዎች ጉዳይ መርሃግብር ዳይሬክተርና የዚህ ዘገባ ጸሐፊ ሻርሎቴ ፌልድማን ጃኮብ፤ ይህን መረጃ ለአደባባይ ለማብቃት የወሰኑት የሚመለከታቸዉ የመንግሥት አካላት የችግሩን መስፋፋት ተመልክተዉ ዉሳኔ ለመስጠት እንዲያመቻቸዉ እንደሆነ ገልጸዋል። እሳቸዉ እንደሚሉት ዘገባዉ ልጃገረዶቹም ሆኑ አዋቂዎቹ ሴቶች ከየት እንደመጡ፣ የት እንዳሉና ስንት እንደሆኑ ማሳየቱ የጉዳዩን አሳሳቢነት የደረሰበትን ደረጃ ያመላክታል። ድርጊቱ በሚፈፀምባቸዉ አብዛኞቹ ሃገራት የሴትን የመዋለጃ አካል የዉጭኛ ክፍል በከፊል ወይም ሙሉ ለሙሉ የማስወገዱ ርምጃ ቋሚ አካላዊና ስነልቡናዊ ጉዳት ከማድረሱም በላይ፤ ለሞትም የሚዳርግበት አጋጣሚ በተደጋጋሚ ታይቷል። ለዘመናት በሃይማኖት ስም ሲፈፀም የነበረዉ ይህ ድርጊት በተደረገዉ የማስተማር ጥረት ጎጂነቱ በመታወቁ አሁን በበርካታ የአፍሪቃ ሃገራት በሕግ እንዲቆም ተደርጓል። በባህል ስም ድርጊቱ ከሚፈጸምባቸዉ ሃገራት ወደተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የተሰዳጁ መጠን እየበረከተ መሄዱ ይህ በማይታወቅበት ማህበረሰብ ዉስጥ ትልቅ የመነጋገሪያ እንዲሁም የስጋት ምክንያት ለመሆን በቅቷል።

Screenshot Facebook Stop FGM Iran

ኢራን በኢንተርኔትም ዘመቻዉን ታካሂዳለች

ዩናይትድ ስቴትስ ይህን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ከጎርጎሪዮሳዊዉ 1996ዓ,ም ጀምሮ ያገደች ሲሆን በዚሁ የዘመን ቀመር በ2012 ደግሞ ሴት ልጆችን ለማስገረዝ ከአሜሪካን ወደሌላ ሀገር መዉሰድ ሕገ ወጥ መሆኑን የሚደነግግ ሕግ አጽድቃለች። ከአንድ ሳምንት በፊትም የኒዮርክ እና ቴክሳስ የዴሞክራት ፓርቲ ተጠሪዎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቱን መፈጸምን ያለመታገሱ ዘመቻ አካል በመሆን መንግሥት በዚያች ሀገር በጥገኝነት የሚኖሩ ግርዛትን ባህል ብለዉ ከሚከተሉ ሰዎች ልጃገረዶችን የሚያስጥል ብሄራዊ የድርጊት መርሃግብር እንዲነድፍና ስራ ላይ እንዲያዉል ግፊት ማድረግ ጀምረዋል። ቀደም ሲል የተጠቀሰዉ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መረጃ ይፋ የሆነዉ ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ የጉዳዩ አሳሳቢነት ትልቅ ስፍራ ይዞ ማነጋገር በያዘበት ወቅት መሆኑን ስለሚያመለክት አሜሪካ ዉስጥ በተለያዩ ግዛቶች ወደሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ስልክ ደዉዬ ነበር። ይህ ጉዳይ እዚያ በሚገኘዉ ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰብ ዘንድ ምን ያህል ይታወቃል? 27ዓመታት እዚያ እንደኖረች የገለፀችልኝ የልጆች እናት የሆነችዉ ወ/ሮ ትዕግስት ልዑልሰገድ የአትላንታ ኗሪ ናት።

የአትላንታ አድማስ ራዲዮና ድንቅ መጽሔት አዘጋጅ የሆነዉ ቴዎድሮስ ኃይሌ በበኩሉ ከዚህ ቀደም የተከሰተ ገጠመኝን ይጠቅሳል። እንደዘገባዉ ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ የግርዛት አደጋ ካንዣበበባቸዉ 506 ሺህ 795 ሴቶችና ልጃገረዶች መካከል 55 በመቶዊ የሚሆኑት ግብፅት፣ ኢትዮጵያ ወይም ሶማሊያ የተወለዱ ፤ አለያም ከዚያ ሀገር ከመጡ ወላጆች የተገኙ መሆናቸዉን ጥናቱ አመልክቷል። ቀሪዎቹ ደግሞ አንድም ከናይጀሪያ፣ ላይቤሪያ፣ ሴራሊዮንና ሱዳን፣ እንዲሁም ኬንያ፣ ኤርትራ እና ጊኒ ናቸዉ። የጥናቱ አቅራቢዎች የሀገሪቱ መንግሥት የችግሩን ስፋት እንዲመለከት ነዉ የሚጠይቁት። በጥናቱ ከተጠቀሱት አካባቢዎች አንዱ በሆነዉ በሲያትል ከተማ ኗሪ የሆነችዉ ጋዜጠኛ ንግሥት ሰልፉ ይህን ጉዳይ የምትመለከትበት አቅጣጫ ለየት ይላል፦ ሰዉ ሲሰደድ እኮ ከነባህሉ ነዉ ትላለች፣

EndFGM Campagin logo

በየጊዜዉ ወላጆችን የሚያስተምሩ እንቅስቃሴዎች መኖራቸዉን የጠቆመችዉ ንግስት የየሀገሩን ባህላዊ አመለካከት የሚያስረዳ ኤትኖሜድ የተሰኘ ድረገጽም መኖሩን ገልጻልናለች። ይህ የተደረገበት ምክንያትም ችግሩ በስዉር በመኖሩ እንደሆነ ነዉ የምታስረዳዉ።

በተመሳሳይ ይኸዉ ጉዳይ የብሪታንያን መንግሥትም እጅግ በማሳሰቡ ባለፈዉ ዓመት ሐምሌ ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ወላጆች ሴት ልጆቻቸዉን ከመገረዝ ማዳን ካልቻሉ ፍርድ ቤት መቆም እንደሚጠብቃቸዉ አስጠንቀዋል። ብሪታንያ ከጎርጎሪዮሳያዉ 1985ዓ,ም ጀምሮ ነዉ ሴትን ልጅ መግረዝም ሆነ ማስገረዝ ከባድ ወንጀል መሆኑን በሕግ ያጸናችዉ። ከዚሁ የዘመን ቀመር 2003ዓ,ም ጀምሮ ግን ልጆቹን ወደሌላ ሃገራት እየወሰዱ እንደሚያስገርዙ ተደርሶበታል። ሆኖም ባለፉት አራት ዓመት ከ140 የሚበልጥ ይህን የሚያሳዩ መረጃዎች ለፖሊስ ቀርበዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic