ምዕራቡ ዓለም ና ፀረ-አይ ኤሱ ትግል | ዓለም | DW | 05.12.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ምዕራቡ ዓለም ና ፀረ-አይ ኤሱ ትግል

ምዕራባውያን ሃገራት ራሱን «እስላማዊ መንግሥት» ብሎ በሚጠራው በእንግሊዘኛ ምህፃሩ IS ላይ በከፈቱት ዘመቻ ከሶሪያ ጦር ጋር ተባብረው ለመሥራት እያሰቡ ነው። ትብብሩን ያቀዱት ምዕራባዉያን ሃገራት በሌላ ወገን ደግሞ የሶርያ መንግሥትን የሚቃወሙ ኃይላትን ይደግፋሉ።

ጠላቶቹን እየደገፉ ከሶሪያ ጦር ሠራዊት ጋር በጋራ ሊካሄድ የታሰበው ይህ ውጊያ እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን እያጠያየቀ ነው። ሃሳቡ የመጣው ከፈረንሳይ በኩል ነው። የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሎሮን ፋብዩስ ናቸው ራሱን «እስላማዊ መንግሥት»ብሎ በሚጠራው በIS ላይ በተጀመረው ዘመቻ ከሶሪያ ወታደሮች ጋር ተባብሮ የመሥራቱን ሃሳብ ያቀረቡት። ምዕራቡ ዓለም አብሮ ለመሥራት ያሰበው በሶሪያው ጦርነት ከሀገሪቱ ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ጎን ሆነው አሸባሪ ሚሊሽያዎችን እንዲሁም በምዕራባውያን የሚደገፉ ለዘብተኛ አቋም አላቸው የሚባሉ አማፅያንን ከሚወጉ ወታደሮች ጋር ነው። ሆኖም ይህ ሁሉ እንዲደረግ የሚፈለገው በሶሪያ የፖለቲካ ሽግግር ከተካሄደ እና አሳድም ከተነሱ በኋላ ነው ተብሏል። የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን ZDF ለተባለው የጀርመን ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት አስተያየት አሳድ ከተነሱ በኋላ ሊኖር ይችላል ስለሚባለው ትብብር ግልፅም ባይሆን አለ ያሉትን ተስፋ ተናግረዋል።

በእርሳቸው አባባል ከሶሪያ ወታደሮች የተወሰኑት በጣም ጥሩ የሚባሉ እና በፀረ IS ትግል ሊሳተፉ የሚችሉ ናቸው። ሆኖም የትኛዎቹን ማለታቸው እንደሆነም በግልጽ አላሳወቁም። እናም ከምዕራባውያን ጋር ተባብረው ሊሠሩ የሚችሉት አጋሮች እነማን ይሆናሉ? በእርስ በርሱ ጦርነት ሲዋጉ የቆዩት እንዲሁም፣ ሩስያና ምዕራባውያንን ጨምሮ በተለያዩ ኃይሎች የሚደገፉት ወገኖች ወደፊት ጎን ለጎን ሆነው ሲዋጉ የሶሪያ መንግሥት ታማኞችስ ምን ዓይነት ሚና ይኖራቸዋል? በጀርመኑ የሳይንስና የፖለቲካ ጥናት ተቋም የመካከለኛ ምሥራቅ ጉዳዮች አዋቂ ምዩርየል አሰቡርግ እንደሚሉት በምዕራባውያኑ ሃሳብ፣ አብሮአቸው እንዲሠራ የሚፈልጉት የሶሪያ ጦር፣ የአሳድ ታማኞችን አይጨምርም።

«ሃሳቡ እምነት የሚጣልበት እና ሁሉን አሳታፊ፣ የጦር ሠራዊቱ የበላይ አዛዥ የሆነ የሽግግር መንግሥት እንዲኖር ነው። ወታደሮቹም የአሁኑን መንግሥት የመደገፍ ግዴታ የማይሰማቸው፣ ነገር ግን አዲሱን መንግሥት የሚደግፉ እንዲሆኑ ነው።»

ይሁንና በአሰቡርግ አስተያየት ይህን መሰሉ ትብብር ተግባራዊ ይሆናል ብሎ ማሰቡ ግን አስቸጋሪ ነው።

«በርግጥ በእርስ በርሱ ጦርነት የሚካፈሉና አንዳቸው ሌላኛቸውን ሲወጉና በተለያዩ ኃይሎች ሲደገፉ የቆዩ ወገኖች ድንገት አንድ ላይ ሆነው ሌላ ሦስተኛ

ኃይል ይወጋሉ ብሎ ማሰቡ ይከብዳል።»

ISን ለመውጋት የተጀመረው ዓለም ዓቀፍ ህብረት ብዙ ሃገራትን አቅፏል። በዘመቻው ምዕራባውያን ሃገራት ብቻ ሳይሆኑ ብዙ የአረብ ሃገራት እና በሶሪያው ጦርነት ከሶሪያ መንግሥት ጎን የቆመችው ሩስያም አለችበት። አብዛኛዎቹ የሶሪያ ወታደሮች በሙሉ ፈቃደኝነት አይደለም ለአሳድ መንግሥት የሚዋጉት። ከመካከላቸው ብዙዎቹ ከድተዋል። ከአማጽያን ጋር ቅርበት ያለው የሶሪያ የሰብዓዊ መብቶች ታዛቢ ቡድን እንደሚለው ወደ 70 ሺህ የሚጠጉ የሶሪያ ወታደሮች አገልግሎታቸውን አቋርጠዋል። ሆኖም ይህን መረጃ በሌላ ዜና ምንጭ ማረጋገጥ አልተቻለም። አንዳንዶች ደግሞ የደረሱበት አይታወቅም። ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ጦርነቱ ከተጀመረበት ከጎርጎሮሳዊው መጋቢት 2011 አንስቶ 80 ሺህ የመንግሥት ኃይሎችና ተባባሪ ሚሊሽያዎች እንደተገደሉ ይገመታል። በአሳድ ጦር ውስጥ አለመተማመኑ ብሷል። በሶሪያ ጦር ውስጥ የሺአ እስልምና ተከታይ የሆኑት አላዊቶች ያመዝናሉ። ከአጠቃላዩ ህዝብ ወደ 12 በመቶ የሚሆኑት እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በወታደሩ ውስጥ ከፍተኛ ማዕረግም አላቸው። አሰበርግ እንደሚሉት አላዊቶች የአሳድ መንግሥት ታማኞች ናቸው ።

«ይህ ማለት የዚህ እምነት ተከታዮች አሉ። ይህም አገዛዙም በነርሱ ላይ ብቻ እምነቱም መጣሉን ያንፀባርቃል። በዚህ የተነሳም ከመደበኛው ጦር አብዛኛው ፈፅሞ በውጊያ አይካፈልም።»

አላዊቶች በታሪካዊ ምክንያቶች የኤኮኖሚ ተጠቃሚ አልነበሩም። በዚህ መንስኤ ወደውትድርና ሙያ ሊሳቡ መቻላቸው ይነገራል። ከዚህ ሌላ የአሳድ አገዛዝ ምርጫዎችም ናቸው። በእግረኛዎቹ ወታደሮች ውስጥ ሱኒዎችም አሉ። ሆኖም እነዚህ ወታደሮች በወታደራዊው ስለላ ክፍል ቁጥጥርና ክትልል ይካሄድባቸዋል እንደ አሰቡርግ። ISን በመዋጋቱ የጋራ ትግል ወሳኙ ጉዳይ ወታደራዊው እርምጃ ብቻ አይደለም። ሰላማዊውን ህዝብ ከጎን ማሰለፍም ጭምር እንጂ። ይህ አሁን የተተወ ነው የሚመስለው። በIS ላይ የሚካሄደው የአየር ድብደባ ተቃራኒ ውጤት ያመጣ ይመስላል። ምክንያቱም በአየር ድብደባው በተለይ ህዙቡ ክፉኛ እየተሰቃየ ነው። ይህም ህዝቡን በIS ላይ ከተጀመረው ጦርነት ጎን ለማሰለፍ ጥሩ ስልት ሆኖ አልተገኘም እንደ አሰቡርግ

ክርስና ሩታ

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic