ምዕራቡ ዓለምና ኢራን | ዓለም | DW | 02.08.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ምዕራቡ ዓለምና ኢራን

እስራኤል የኢራንን የኒኩሊየር መርሃ ግብር ለማስቆም ወታደራዊ ርምጃ መዉሰድ ይቻላል የሚለዉ ማስተማመኛ ብቻዉን በቂ አይደለም አለች። እስራኤልን የጎበኙት የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስትር ሌዮን ፓኔታ የቴህራንን የኒኩሊየር ጦር መሳሪያ

የመጨበጥ ምኞት ለመግታት ከጦር ዉጪ ያሉ አማራጮችን ሁሉ አሟጦ መጠቀም ይገባል ባይ ናቸዉ። ሰሞኑን በተከታታይ ወደ መካከለኛዉ ምስራቅ ጎራ ያሉት የዋሽንግተን ባለስልጣናት የአሜሪካንን የእስራኤል አጋርነት ያሳያል ያሉትን አቋም በንግግራቸዉ ለማንፀባረቅ ቢጥሩም እስራኤልን ያረኩ አይመስልም። ዋሽንግተን ማንኛዉንም ዓይነት ወታደራዊ ጥቃት ቴህራን ላይ መሰንዘርን በአሁኑ ሰዓት እንደማትደግፍ ነዉ ዘገባዎች የሚያመለክቱት። በተቃራኒዉ በቅርቡ የሚሰሙ ጭምጭምታና ግምቶች እስራኤል ኢራን ላይ ወታደራዊ ርምጃ መሰንዘሯ የጊዜ ጉዳይ ብቻ እንደሆነ ያመለክታሉ። የኢራን መሪዎች ደጋግመዉ የአይሁዶች ግዛት ከዓለም ካርታ ላይ መወገድ አለበት በማለት በይፋ መናገራቸዉ ያሰጋት እስራኤል፤ ኢራንን እንደአደጋ መመልከቷ ግልፅ ነዉ።

መካከለኛዉ ምስራቅ ዉስጥ ጉብኝታቸዉን የቀጠሉት የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስትር ሌዮን ፓኔታ ወደቴልአቪቭ ሲያመሩ ስለወታደራዊ ርምጃ አንድ ይላሉ ተብሎ ነበር። ሆኖም ፓኔታ በይፋ ትናንት የተናገሩት ሀገራቸዉ ኢራን በኒኩሊየር መርሃግብሯ መግፋቷን እንድታቆም ከማዕቀብ ሌላ አማራጮች እንዳሏት ነዉ። ከእስራኤሉ አቻቸዉ ኤሁድ ባራክ ጋ በኒኩሊየር ስጋት ላይ እንደሆነ የተገመተ ንግግራቸዉን ጨርሰዉ ሊዮን ፓኔታ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ አሜሪካ አላት ስላሉት አማራጭ ምንነት ግን በግልፅ አልተናገሩም።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ምንም እንኳን ዩናይትድ ስቴትስ የኢራንን የኒኩሊየር መርሃግብር ለማስቆም፤ ወታደራዊ ርምጃን በአማራጭነት መዉሰድ እንደሚቻል ብታረጋግጥም ብቻዉን በቂ እንዳልሆነ አመልክተዋል። ፓኔታ ግን ወደወታደራዊ ርምጃ ከማለፍ አስቀድሞ ሊሟጠጥ የሚገባዉ በርካታ አማራጭ ስልት አለ ባይ ናቸዉ፤

«እንደሚመስለኝ አሟጠን መጠቀም ይኖርብናል፤ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ እያንዳንዷን አማራጭ መፈተሽ፤ ወታደራዊ ርምጃን ከመወሰናችን በፊት እያንዳንዱን ጥረት ማሟጠጥ ይኖርብናል። እንደሚመስለን ይህ አስፈላጊ ነዉ።»

የአሜሪካን ምክር ቤት ኢራን ላይ ተጨማሪ የኤኮኖሚ ጫና ያስከትላል ያለዉን፤ በቴህራን የኃይል፤ የመርከብ ማጓጓዣ እና የፋይናንስ ተቋማት ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ተስማምቷል። የዋሽንግተን ምክር ቤት 421 ለ 6 በሆነ ድምፅ ያሳለፈዉን ረቂቅ፤ ሴኔቱም አፅድቆታል። የፕሬዝደንት ባራክ ኦባማን ፊርማ ይጠብቃል። የአሁኑ ማዕቀብ ከኢራን ማዕከላዊ ባንክ ጋ በአጋርነት የሚሠሩ ትላልቅ የፋይናንስ ተቋማትን ይመለከታል።

እንዲያም ሆኖ እስራኤል በተደጋጋሚ ማዕቀብና የዲፕሎማሲ ጥረት ኢራን ጊዜ እንድትገዛ የሚጠቅም ካልሆነ በቀር ካሰበችዉ የሚገታት አይደለም ስትል ተደምጣለች። ከሌዮን ፓኔታ ጋ የተነጋገሩት የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ባራክም እንዲሁ ማዕቀብም ሆነ ዲፕሎማሲ ኢራንን ከጀመረችዉ የኒኩሊየር ቅመማ ተግባር መግታቱን እንደሚጠራጠሩ ነዉ ያመለከቱት። በአሜሪካዉ ምክር ቤት የሪፑብሊካን ተወካይ ኢሊያና ሮዝም በበኩላቸዉ፤ ይህን በማድረጋችን ኢራንን በኒኩሊየር መርሃግብሯ ከመግፋት ገደብናት ወይ? ካሉ በኋላ ያን ማድረግ ካልቻልን ለአሜሪካን ህዝብም ሆነ ለአጋራችን እስራኤል ፋይዳ የለዉም ነዉ ያሉት።

ሰሞኑን ወደመካከለኛዉ ምስራቅ ጎራ ያሉት የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት መንግስታቸዉ ለእስራኤል ህልዉና ያለዉን ቁርጠኝነት ለማሳየት ሲጥሩ ታይተዋል። ሁለቱም ግን የየትኛዉንም ወገን ልብ በወጉ ያገኙ አይመስሉም። ፓኔታ ወታደራዊ ጥቃት ስለመሰንዘር ያወጋሉ ተብሎ ሲጠበቁ ተጨማሪ አማራጮችን ወደጠረጴዛዉ ለማምጣት መጣራቸዉ የእስራኤልን መሪዎች አላጠገበም። ብሪታንያ፤ እስራኤልና ፖላንድን የጎበኙት ሪፑብሊካኑ ፕሬዝደንታዊ እጩ ሚት ራምኒም በአዉሮጳዉያኑ 2008ዓ,ም ባራክ ኦባማ ለተመሳሳይ ዓላማ ባደረጉት ጉብኝት ያገኙትን ትኩረት ሩብ እንኳ አልተሳካላቸዉም።

እስራኤል ዉስጥ ፍልስጤማዉያንን አስከፍተዉ በዘረኝነት ተተችተዉ፤ በተለያዩ ምዕራባዉያን ተነባቢ ጋዜጦች ተብጠልጥለዋል። ኦባማ በወቅቱ እንደእሳቸዉ ለምረጡኝ ወደየሀገሩ ብቅ ሲሉ የፖፕ ሙዚቃ ኮከብ የሚጎርፍለት ዓይነት አድናቆት እንደዛቁ ነዉ ዘገባዎች የጠቆሙት። እሳቸዉም ቢሆኑ ግን ኢራንን አስፈራርተዉ፤ አምባገነኖችን ወዮላችሁ ብለዉ፤ ለፍልስጤም እስራኤል ዉዝግብ ፍቱን አብነት አለኝ ብለዉ እንዳሉ ለሌላ ምርጫ ዝግጅት ይዘዋል። እስራኤልም ቀጥታ የሶስትዮሽ ድርድር፤ ከዲፕሎማሲ- ከማዕቀብ ሲመረጥ አንድም ከፍልስጤም አንድም ከኢራን ተፋጣ ተቀምጣለች። ኢራንም ምዕራቡ ዓለም የሚጠራጠረዉን የኒኩሊየር መርሃ ግብሯን አላቆመችም።

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች