1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምዕመናን ደም እንዲለግሱ ተጠየቀ 

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 12 2014

ኢትዮጵያ ዉስጥ ለሕሙማን የሚሰጥ የደም ክምችት ሲበዛ ማነሱን የሐገሪቱ ብሔራዊ ደም ባንክ አስታውቋል።ባንኩ እንደሚለዉ አሁን ያለው የመጠባበቂያ ደም ክምችት ከአምሥት ቀናት አገልግሎት አይበልጥም። የእስልምና እና የክርስትና እምነት ተከታዮች በቅርቡ የሚያከብሯቸዉን በዓላት ምክንያት በማድረግ ደም እንዲለግሱ ጠይቋል።

https://p.dw.com/p/4AACy
Äthiopien Blutbank Addis Abeba
ምስል Seyoum Getu /DW

አሁን ያለው የደም ክምችት ከአምስት ቀናት በላይ አይዘልቅም።


ኢትዮጵያ ዉስጥ ለሕሙማን የሚሰጥ የደም ክምችት ሲበዛ ማነሱን የሐገሪቱ ብሔራዊ ደም ባንክ አስታውቋል።ባንኩ እንደሚለዉ አሁን ያለው የመጠባበቂያ ደም ክምችት ከአምሥት ቀናት አገልግሎት አይበልጥም። የእስልምና እና የክርስትና እምነት ተከታዮች በቅርቡ የሚያከብሯቸዉን በዓላት ምክንያት በማድረግ ደም እንዲለግሱ ጠይቋል።
በብሔራዊ ደም ባንክ  የደም ለጋሾች ዘርፍ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ተመሥገን አበጀ ለዶቼ ቬለ እንደገለፁት በሀገሪቱ በተለያዩ አደጋዎች እና በሽታዎች የህክምና ተቋማት የደም ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ያም ሆኖ በአሁኑ ወቅት የደም ለጋሾች ቁጥር በፍላጎቱ ልክ አለመሆኑን ገልጸዋል።የደም ልገሳ መቀነስ ከሁለቱ ታላቅ የሀገሪቱ እምነቶች ፆም  ጋር ተያይዞ የተለመደ ነበር የሚሉት ሀላፊው፤ የዘንድሮው ግን አሳሳቢ በሆነ መልኩ መቀነሱን ተናግረዋል።
በዚህ የተነሳ በተለይ «ኦ» ተብሎ የሚጠራው የደም ዓይነት  እንዲሁም ለካንሰር ታማሚዎችና የደም መፍሰስ ችግር ላለባቸው ታካሚዎች የሚሰጠው «ፕላትሌት» የሚባለው የደም ተዋፅዖ እጥረት ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በደም ባንክ የሚገኘው የደም ክምችት በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሺህ ከረጢት በታች ነው የሚሉት ሀላፊው ፤ይህም ለአምስት ቀናት እና ከዚያ በታች የሚያገለግል ብቻ በመሆኑ እጥረቱ አሳሳቢ የሚባል ደረጃ ላይ መድረሱን ገልፀዋል።
በመሆኑም ህብረተሰቡ ይህንን ችግር ተገንዝቦ የትንሳኤ  እና የኢድ በዓላትን  ደም በመለገስ እንዲያከብር እና የታካሚዎችን ህይወት እንዲታደግ  ሀላፊው ጥሪ አቅርበዋል።

 


ፀሀይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ