1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በምክር ቤት የተገኙት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 21 2017

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ «ቅጥረኞች አይደለንም» ሲሉ መንግሥታቸው ከኢትዮጵያ ልማት በቀር የማንም አጀንዳ አስፈፃሚ እንዳልሆነ ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለፁ። «ማንም ላይ ጦር የመስበቅ ፍላጎት የለንም» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ «ማንም ኢትዮጵያን እንዲደፍር አንፈቅድም» በማለትም በጎረቤት ሃገራት የመወረር ሥጋት እንደሌለ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4mSPD
የኢትዮጵያ ምክር ቤት
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዲስ አበባ ፎቶ ከማኅደር ምስል Solomon Muchie/DW

"ቅጥረኞች አይደለንም"-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ 

 

 ከአዲስ አበባ ሰሎሞን ሙጬ ዝርዝር ዘገባ አለው።

መንግሥታቸው በአማራ ክልል ያለውን ቀውስ ለመፍታት ከሰላማዊ ይልቅ ወታደራዊ አማራጮችን መምረጡ ተጠቅሶ ችግሩን በድርድር ለመፍታት ለምን እንዳልቻለ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ ሰላም ፈላጊ መሆናቸውን ጠቅሰው ጥረቱ አለመሳካቱን ጠቁመዋል። ያም ሆኖ ግን «በኃይል የሚያሸንፈን የለም» ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በዛሬው መደበኛ ጉባኤ ላይ የሰላምና ፀጥታ፣ የኢኮኖሚ፣ የዲፕሎማሲ እና ሌሎች ጉዳዮችን የተመለከቱ ጥያቄዎችን አንስተዋል።

ሕግ የማስከበር ሥራ እና ሰላማዊ አማራጮችን እንዴት ጎን ለጎን ማስኬድ ይቻላል? የሰላም እና ፀጥታ ችግሮችን ለመፍታት በተለይ በአማራ ክልል መንግሥት የኃይል አማራጭ ለምን መረጠ፣ ችግሮችን በእውነተኛ ድርድር ለመፍታት ግልጽና ይፋዊ ጥሪ አቅርቦ ያንን መስመር መከተል ለምን አልመረጠም በሚል ተጠይቋል።

«በመላዉ ሀገሪቱ ያለው ጅምላ የንፁሃን ግድያ፣ ሕገ ወጥ ጅምላ እሥር፣ ጾታዊ ጥቃት፣ መፈናቀል፣ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት፣ አግባብ ያልሆነ የቤቶች ፈረሳ ያኔም ነበረ አሁንም እንደቀጠለ ነው»።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድዓመቱ «ሀገራዊ መንሰራራት የሚጀመርበት» መሆኑን በመጥቀስ በጀመሩበት ማብራሪያቸው «ከማንም በላይ ሰላም እንፈልጋለን» ሆኖም ግን በኃይል የሚያሸንፈን የለም ሲሉ ተደምጠዋል።

«የሰላም አማራጭ አትመርጡም ወይ? በግልጽ አታውጁም ወይ? ለተባለው በተደጋጋሚ ማወጃችንን እናንተም ሕዝቡም ያውቃል። የሀገር ሽማግሌዎች ልከን በእምብርክክ መመለሳቸውንም እናንተም እኛም እናውቃለን» ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሃገራት ጋር በሰላም መኖር ምርጫዋ መሆኑን፣ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ግን የሚቀለበስ አለመሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ከማንም ጋር የመዋጋት ፍላጎት የላትም፣ እንወረራለን የሚል ሥጋትም የለብንም ብለዋል።

ምክር ቤት
ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል። ፎቶ ከማኅደር ምስል Solomon Muchie/DW

«ነገ ዉጊያ ይነሳል ብለው የሚያስቡ ሰዎች፣ አንዋጋም ከማንም ጋር። ሁለተኛ ጉዳይ ኢትዮጵያን ሊወርሩ ይችላሉ - ሃገራት የሚል ሥጋት ያለባቸው ሰዎች አልፎ አልፎ ስለሚኑሱ ኢትዮጵያን ማንም ሰው ዛሬ በኃይል መውረር አይችልም»።

በዛሬው ጉባኤ ሁለት የምክር ቤት አባላት ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የቁጫ እና የዘይሴ ማኅበረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ስለቀረቡ ብቻ በአካባቢው መስተዳድር እጅግ የከፋ ግፍ እየተፈፀመባቸው መሆኑን በዝርዝር ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኑስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት በ8.4 በመቶ ዕድገት ታስመዘግባለች ብለዋል። ኢትዮጵያ ለሥራ ከተጓዙባቸው ሃገራት ሁሉ በታች ያለች፣ እጅግ ወደ ኋላ የቀረች ሀገር መሆኗን መገንዘባቸውንም ጠቅሰው ሰፊ ሥራ መሥራት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

አክለውም መስተዳድራቸው የጀመረው «የኮሪደር ልማት» የተባለው ተግባር ቀጣይ እንደሚሆን፣ ኢትዮጵያን መዝረፍ መብት እንደሆነ የሚያስቡ ሃገራት መኖራቸውን፣ አዲስ አበባ ውስጥ በውጭ ምንዛሪ የጥቁር ገበያ ውስጥ የተሰማሩ ያሏቸው ኤምባሲዎች መኖራቸውንም በገለፃቸው አመልክተዋል።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር