ምክር ቤታዊ ምርጫ በደቡብ አፍሪቃ | አፍሪቃ | DW | 08.05.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ምክር ቤታዊ ምርጫ በደቡብ አፍሪቃ

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በዛሬው ዕለት ምክር ቤታዊ ምርጫ ተካሄደ። በዚሁ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚደን ኔልሰን ማንዴላ ከሞቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገሪቱ በተካሄደው ምርጫ የአፍሪቃውያኑ ብሔረተኞች ኮንግረስ፣ «ኤ ኤን ሲ » እንደሚያሸንፍ እና መሪው ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማም ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታትም በሥልጣናቸው እንደሚቆዩ ይጠበቃል።

ብዙ ደቡብ አፍሪቃውያን የዘር አድልዎ መርህ ከተገረሰሰበት ካለፉት ሀያ ዓመታት ወዲህ ዘሬ ለአምስተኛ ጊዜ በተካሄደው ምርጫ ድምፁን ለመስጠት የተመዘገበው የመምረጥ መብት ያለው ወደ 25 ሚልዮኑ የሚሆነው፣ ብሎም ግማሽ የሀገሪቱ ሕዝብ፣ ከጥዋቱ አንድ ሰዓት ጀምረው ደምፁን ሲሰጥ ውሎዋል። በመላይቱ ሀገር 22,000 የምርጫ ጣቢያዎች የተከፈቱ ሲሆን፣ አስመራጩ ኮሚሽን እንዳስታወቀው፣ ከምርጫ ጣቢያዎቹ መካከል 95 ከመቶው በሮቻቸውን በሰዓቱ ከፍተዋል። ምርጫው ከሞላ ጎደል በሰላማዊ መንገድ ቢካሄድም፣ በትልቆቹ ከተሞች መዳረሻ ላይ ባለ አንድ በብዛት ጥቁሮች በሚኖሩበት ከተማ አንድ የምርጫ ጣቢያ በእሳት በመጋየቱ፣ ባንዳንድ ሁከት ባሰጋቸው እና የፖለቲካ ውጥረት በታየባቸው የምርጫ አካባቢዎች መንግሥት ፖሊስ መሰማራቱ ተገልጾዋል።

Wahlkampf aus Südafrika Plakat Zuma

« ኤ ኤን ሲ »

«ኤ ኤን ሲ » ምንም እንኳን የሕዝብ አስተያየት መመዘኛ መዘርዝሮች እንደሚያሳዩት በመንግሥቱ አመራር ላይ በሕዝብ ዘንድ ትልቅ ቅሬታ ቢኖርም፣ ከ60 ከመቶ በላይ የመራጩን ድምፅ እንደሚያገኝ ተገምቶዋል። በ «ኤ ኤን ሲ » አንፃር የሚፎካከከሩት ዋነኞቹ የተቃውሞ ፓርቲዎች በፀረ አፓርታይድ ታጋይ ሄለን ሲለ የሚመራው የ«ዴሞክራቲክ አላያንስ » ፓርቲ እና ከ «ኤ ኤን ሲ » የወጡት ጁልየስ ማሌማ ያቋቋሙት የ « የኤኮኖሚያዊ ነፃነት ታጋዮች » ፓርቲ፣ በምሕፃሩ «ኢ ኤፍ ኤፍ » ሲሆኑ፣ ማሌማ ፓርቲያቸው ለቆመለት ማዕድናት ወደ መንግሥት እጅ ይመለሱ እና የእርሻ መሬትም ለሰፊው ሕዝብ ይከፋፈል በሚል ለያዘው አቋሙ በምክር ቤታዊ ምርጫ በርካታ መንበሮች እንደሚያገኝ ተስፋ አድርገዋል።

Wahlkampf aus Südafrika von Julius Malema

የጁልየስ ማሌማ « ኢ ኤፍ ኤፍ » ፓርቲ

በ«ኤ ኤን ሲ » ላይ አሁንም እምነታቸውን ያላጠፉት በሶዌቶ ድምፃቸውን ከሰጡ መካከል የ60 ዓመቷ ማምፒ ማሉሌኬ አንዷ ናቸው።

« ለዚች ቀን ለመብቃት እና ድምፄን ለመስጠት በጣም ጓጉቼ ነበር ። እኔም፣ ልጆቼም በጣም ጓጉተን ነበር። «ኤ ኤን ሲ»ን እንዲመርጡም ነግሬአቸዋለሁ። ምክንያቱም « ኤ ኤን ሲ » አንድ ቀን እንደሚረዳን አውቃለሁና።»

የሀገሪቱ መንግሥት ባሳሰበው መሠረት፣ በተለይ ለመጀመሪያ ጊዜ የመምረጥ ዕድል ያገኙት እና ከዘር አድልዎ አመራር ካበቃ በኋላ የተወለዱት ወጣት ደቡብ አፍሪቃውያን ወደ ምርጫ ጣቢያ በመሄድ ድምፃቸውን በመስጠታቸው እና የወደፊቱን ዕድላቸውን ራሳቸው መወሰን በመቻላቸው መደሰታቸውን ከገለጹ ት መካከል አንዱ በገዢው «ኤ ኤን ሲ » ያልተደሰተው ፑሜላኒ ኾዛ ነው።

Wahlkampf aus Südafrika von Helen Zille

የ«ዴሞክራቲክ አላያንስ» ፓርቲ መሪ ሄለን ሲለ

« « ኤ ኤን ሲ » የመሬት ድልድሉን ጉዳይ ፣ ማለትም፣ በ20 ዓመታት ውስጥ 30 ከመቶውን ለሰፊው ሕዝብ እንደሚመልስ የገባውን ቃል ባለማክበሩ ከሽፎዋል። የመሬት ባለቤት ለሆኑት ጥቁር ደቡብ አፍሪቃውያን ባለፉት 20 ዓመታት የመለሰው መሬት ሰባት ከመቶ ብቻ ነው። »

አፓርታይድ ከተገረሰሰ ወዲህ አሁን ለ3ኛ ጊዜ ድምፃን የሰጠችው እና በ«ኤ ኤን ሲ » አመራር ቅር የተሰኘችው የ29 ዓመቷ ቼርል ማጌዛም ባሁኑ ምርጫ « ኤ ኤን ሲ» ን አለመምረጧን እና የመንግሥት ለውጥ ይኖራል ብላ ተስፋ ማድረጓን ገልጻለች።

« በኔ እና በልጄ ትውልድ የወደፊት ዕድል ላይ ለውጥ ለማየት ስለምፈልግ የመረጥኩት የ«ዴሞክራቲክ አላያንስ » ፓርቲን ነው። ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ለውጥ እንዲኖር እሻለሁ፣ ለምሳሌ፣ ወንጀል እንዲያበቃ ፣ የትምህርት ሥርዓቱ እና የስራ ዕድል ሁኔታ እንዲሻሻል እፈልጋለሁ። ትምህርታቸውን ጨርሰው የተመረቁት ወጣቶቻችን ቤት ነው ቁጭ ያሉትና። »

በገዢው ፓርቲ ላይ ነቀፌታው ቢፈራረቅም፣ የ«ኤ ኤን ሲ » ምክትል ሊቀቀ መንበር ሲሪል ራማፎዛ ፓርቲያቸው እንደማይሸነፍ በርግጠኝነት ተናግረዋል።

« በሕዝባችን ላይ ጠንካራ እምነት ስላለኝ አልተደናገጥኩም። ሕዝባችን ሀገሪቱን በተሻለ ሁኔታ ያሳድጋል ብለው የሚያስቡትን በሚገባ ያውቃሉ። ድል እንደምንቀዳጅ እርግጠኛ ነኝ። »

አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ

 

 

 

 

Audios and videos on the topic