ምክርቤታዊና ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በጋና | የጋዜጦች አምድ | DW | 07.12.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ምክርቤታዊና ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በጋና

ጋና ውስጥ ዛሬ ምክርቤታዊና ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ይካሄዳል። የምርጫው ዘመቻ በሣምንቱ መጨረሻ ላይ ነበር ያበቃው። ሁለቱ ዓበይት ፓርቲዎች---ማለት መንግሥቱን የሚመራው የፕሬዚደንት ጆን ኩፉር “ብሔራዊ ሐርበኛ ፓርቲ” እና የዚህ ተቃዋሚ “ብሔራዊ ዴሞክራታዊ ኮንግረስ” ናቸው በተለይ የሚቀናቀኑት።

የመምረጥ መብት ካላቸው ከአሥር ሚሊዮኑ ነዋሪዎች መካከል ጥቂቶቹ ባለፈው ቅዳሜ ነበር በየምርጫ ጣቢያቸው ድምጽ መስጠት የጀመሩት። ከእነዚሁ መካከል ብዙዎቹ የፖሊስና የጦርሠራዊት ባልደረቦች፣ ጋዜጠኞች፣ የምርጫው ኮሚሲዮን አባላትና የመንግሥት ሠራተኞች ሲሆኑ፣ የዛሬው ምርጫ ያለ እክል እንዲካሄድ የሚጠባበቁት እነርሱው ናቸው። የመምረጥ መብት ያለው የእያንዳንዱ ዜጋ ስም በአንድ የመራጮች መዝገብ ውስጥ መስፈር አለበት። የእያንዳኑ መራጭ ፎቶ በምርጫ መብት ካርዱ ላይ መታየት አለበት ጭብርብርን ለማስወገድ። በሺህ የሚቆጠሩ ዝንጉዎች ይህንኑ ግዴታ ለመፈፀም ባለመብቃታቸው ድምጽ ሳይሰጡ ቀርተዋል።
ጋና ምክርቤት ውስጥ ባሏት መናብርት መጠን በ፪፻፴ የምርጫ አካባቢዎች ነው የተከፈለችው። አብዝሁ የምርጫ ሥርዓት ነው ጋና ውስጥ የሚሰራበት---ይኸውም፥ በአንዱ የምርጫ ወረዳ ለውድድር የቀረበው ሰው በዚያው ቦታ ብዙውን ድምጽ ካገኘ፣ ለምክርቤቱ መንበር አሸናፊ ይሆናል። በዚሁ የምርጫ ሥርዓት ሥር ትንንሾቹ ፓርቲዎች የምክርቤት አባል የሚሆኑበት ዕድል የመነመነ ነው። በዚህ አንፃር ደግሞ፥ ፕሬዚደንት ለመሆን የሚወዳደረው ሰው በመጀመሪያው የምርጫ ዙር አሸናፊ ይሆን ዘንድ፥ ከተሰጠው ድምጽ ከ፶ በመቶ የሚበልጠውን ማግኘት አለበት።

ለርእሰብሔሩ ሥልጣን ከሚወዳደሩት ወገኖች መካከል አንዳቸውም ይህንኑ ግዴታ ካላሟላ እጅግ ብዙውን ድምጽ ያገኙት ሁለቱ በ፫ ሣምንታት ውስጥ ለማጣሪያው ምርጫ መቅረብ ይኖርባቸዋል። በዚሁ ሥርዓት መሠረት ነበር ከአራት ዓመታት በፊት ያሁኑ ፕሬዚደንት ጆን ኩፉር በተቀናቃኛቸው ጆን አታ ሚልስ አንፃር ድልን ያገኙት። አሁን ታዲያ፥ ሁለቱ ሰዎች እንደገና ለውድድር መቅረባቸው ነው።

ጋና ከተቀሩት ያፍሪቃ አካባቢዎች ለየት በማለት፥ ከ፲፪ ዓመታት በፊት ጀምራ የዴሞክራሲውን ሥርዓት ስታራምድ ነው የቆየችው። ከጋናም ውጭ ከፍተኛውን ዕውቅና ያተረፈው የፖለቲካው ተንታኝና የቴሌቪዚዮን ጋዜጠኛ ኒይ ዓላቢ ስለ ምርጫው ያለውን አስተያየት እንዲህ ያቀርበዋል፥ “........ከአራት ዓመታት በፊት የተካሄደው ምርጫ አንድ የለውጥ ምዕራፍ ነበር። ይኸውም፥ጋና ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ሥልጣኑን በሕዝብ ለተመረጠው ሌላው መንግሥት መልቀቁ ነው። ያሁኑም ምርጫ የጋና ሕዝብ ያለፈውን ሁሉ ለሁልጊዜ ወደ ኋላ ትቶ ወደ ዴሞክራሲና ወደ ፍትሓዊው የመንግሥት ሥርዓት በሚመራው በአስቸጋሪው ጎዳና ላይ ለመጓዝ የደረሰውን ውሳኔ የሚያጠብቅለት ይሆናል።”

ፕሬዚደንት ጆን ኩፉር ላሁኑ ውድድራቸው ያሉበት ሥልጣን ትልቅ መከታ ነው የሚሆናቸው። እርሳቸው የሚከተሉት መፈክር “ልማት በነፃነት” ይሰኛል። እስካሁን ያስገኙት የልማት ክንውን የሚያስሞግስ ሆኖ የሚያዩት ፕሬዚደንት ኩፉር ለመራጮቹ ያቀረቡት ማሳሰቢያ፥ “....እኔን እና ኤንፒፒ ፓርቲዬ የሚመራውን መንግሥት እንድትደግፉ አጥብቄ አሳስባችኋለሁ።”

በዚህ አንፃር ደግሞ የእርሳቸው ተቀናቃኝ ጆን ሚልስ እና ፓርቲያቸው ኤንዲሲ እስካሁን የተገኘው የልማት ክንውን ጨርሶ የማያረካ መሆኑን በማስገንዘብ ነው የሚወዳደሩት፤ እንዲያውም በፕሬዚደንት ጆን ኩፉር አስተዳደር ሥር ሙስና የተስፋፋ መሁኑንም ነው የሚያመለክቱት። በመፈንቅለመንግሥት አማካይነት ሥልጣን ይዘው የነበሩትና አሁንም ተወዳጅ የሆኑት የቀድሞው መሪ ጀሪ ሮውሊንግስ አሁን የሚያቀርቡት ማስገንዘቢያ፥ ያሁኑን መስተዳደር በመፈንቅል አድማ ሳይሆን በመራጮች ድምጽ አማካይነት ማስወገድ እንደሚገባ ያመለክታል። ተወዳዳሪው ሚልስ የጀሪ ሮውሊንግስን ቃል በመከተል በምሬት ሲያስገነዝቡ፥ “..........ሙስናው አለቅጥ ነው የተባባሰው። ይህንኑ ሁኔታ ለመቀየር ነባሮቹን ሕግጋት በንቃት የሚከተል፣ ለወዳጆችና ለፖለቲካ ሽርኮች ደንታ የማይሰጥ ቅን አመራር እንዲኖር ያስፈልጋል። ግን በዚህች ሀገር ይህ ሁሉ ይጓደላል፣ ስለዚህም ነው በሙስና አንፃር አንዳች ርምጃ የማይወሰደው።”

እንግዲህ ታዛቢዎች እንደሚገምቱት ያሁኑ ምርጫ እምብዛም ለውጥ የሚያመጣ፣ የሥልጣን ለውጥ የሚያስገኝ መስሎ አይታይም፤ አሁን ሥልጣን ላይ ያሉት መሪ በዚያው የሚቀጥሉ እንደሚሆኑ ነው የሚገመተው።

ተዛማጅ ዘገባዎች