1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«በDJ ሙያ ሀገሬን ወክዬ መስራት እፈልጋለሁ»

ልደት አበበ
ዓርብ፣ ሰኔ 7 2016

ወጣት ምንተስኖት ታደሰ የኮምፒውተር ሳይንስ ምሩቅ፤ የሬዲዮ ፕሮግራም አቅራቢ እና ምናልባትም እሱ እንደሚለው ኢትዮጵያ ውስጥ ተሽከርካሪ ወንበር ላይ የተቀመጠ ብቸኛው ዲጄ ነው። ባለፈው ሳምንት ለአራተኛ ጊዜ የተካሄደ እና «ጣፋች ሕይወት» የተሰኘ ፕሮግራም አስተባባሪም ነው።

https://p.dw.com/p/4h1IS
ምንተስኖት ታደሰ
ምንተስኖት ታደሰምስል privat

«በDJ ሙያ ሀገሬን ወክዬ መስራት እፈልጋለሁ»

 ምንተስኖት ታደሰ  ይባላል። ሌላም መጠሪያ አለው። DJ14K ። ለምን ይህንን መጠሪያ እንደመረጠ ሲያብራራ « ገና ተማሪ እያለሁ ራዲዮ በጣም ነበር የማዳምጠው። ተወልጄ ያደኩት ጅማ ከተማ ነው። እዛም አንድ የማህበረሰብ ሬዲዮ በጅማ ዮንቨርስቲ ተከፈተ እኔም እንደ አድማጭ መሳተፍ ፈለኩኝ። ግን በስሜ መሳተፍ አልፈለኩም። እና እጎአ በ 2008 የተለቀቀ አንድ ፊልም ነበር። እዛ ላይ አንድ ገፀ ባህሪ 14 K ይባል ነበር። እና ስሙን ስለወደደድኩት ይህን ወስጄ መሳተፍ ጀመርኩኝ ፣ በጥያቄ እና መልስ ውድድር ተሳትፌ ሽልማት ወስጇለሁ ። እና ማነው 14k ብለው ሰዎች እቤት ድረስ ይመጡ ነበር  »ይላል።
ምንተስኖት ከራዲዮ አድማጭነት  ወደ ተሳታፊነት ከዛም የራሱ ዝግጅት  አቅራቢ ለመሆን  ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም። ለዚህ ደግሞ ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ያሉ ሚዲያዎች መከታተሉ አድማሱን እንዲያሰፋ እና ለስራው ረድቶታል። « ከማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያው ጋር ቤተሰብ ስንሆን ግብዣው መጣልኝ። እኔ ግን ከማይክራፎን ፊት መቀመጥ ልምዱ አልነበረኝም። እንደዛም ሆኖ እሺ አልኩኝ። እንዴት ፕሮግራም እንደሚሰራ ትንሽ ነው የነገሩኝ። የሆነ ጥበብን በዜማ የሚባል የመዝናኛ ዝግጅት ነበር።  ከዛ ማይክራፎን ፊት ተቀመጥኩ። »እሱም በድፍረት የመጀመሪያውን የራዲዮ ፕሮግራም ከጣቢያው ሰራተኞች ጋር በጋራ አቀረበ። ይህም እስከ ዛሬ ድረስ ለሚሰራው ስራ በር ከፋች ሆኖለታል። ለአምስት ዓመት ያህል እዛው ጅማ ውስጥ ለጣቢያው ካገለገለ በኋላ እዛ የጀመረውን « አበሻ ጣዕም» ዝግጅት ወደ አዲስ አበባ ይዞ ሄዷል።

«አበሻ ጣዕም»

« ፕሩግራሙን አሳድገነው አሀዱ ራዲዮ ላይ ጀመርነው። እዛም ዓመት ከስድስት ወር ከሰራሁ በኋላ አሁን አራዳ FM ላይ በየሳምንቱ ማክሰኞ ምሽት ከ 2 ሰዓት እስከ 4 ሰዓት የሚተላለፍ ፕሮግራም ነው። አራዳ ላይ አንድ ዓመት አልፎናል እና አሁን እዛ ላይም እየሰራሁ እገኛለሁ።»  የአበሻ ጣዕም ዝግጅት« አዝናኝ፣ ነገር ግን ትምህርት የሚቀሰምበት ነው» ይላል ምንተስኖት። ርዕሰ ጉዳዮቹም በአንድ ነገር ላይ ብቻ ያተኮሩ አይደለም።   « የፖለቲካ ጉዳዮችን ነው ብዙም የማንነካው እንጂ፣ አካል ጉዳተኝነትን ፣ ስለ ሴቶች እና ወሊድን በሚመለከት እናነሳለን። ፕሮግራሙን ስንቀርፀው ከ 15 ዓመት እስከ 49 ዓመት ያሉ ሰዎን እንዲያዳምጡት ነው። » 

 ምንተስኖት ለምን ኮምፒውተር ሳይንስ ለመማር ወሰነ?

« እስከ 5 ዓመቴ ድረስ በእግሬ መሄድ እችል ነበር። ከዛ ግን በውል ባልታወቀ ምክንያት ዊልቸር ተጠቃሚ ሆኛለሁ። በሀይማኖትም በህክምናውም ሞክረናል። አልሆነም። ከዛ በኋላ ስለ ትምህርት ሳስብ ኮምፒውተር ሳይንስ ብማር ብዬ ወሰንኩ።…» ምንተስኖት ከሚዲያ ተሳትፎው በተጨማሪ ቅፅል ስሙም እንደሚጠቁመው ዲጄ ሆኖ ይሰራል። « እንግዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ አካል ጉዳተኛ ሆኖ ዲጄ የሆነ እስካሁን አላጋጠመኝም።  ለእኔ የሚስማማኝ አይነት ሆኖ ያገኘኋቸው ዝግጅቶች ላይ እሰራለሁ። ከዛ ውጪ በዲጄ ሙያ ሀገሬን ወክዬ መስራት እፈልጋለሁ። ግን እኛ ዲጄዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በትምህርት መታገዝ አለብን ብዬ አስባለሁ»

ዲጄ
«በዲጄ ሙያ ሀገሬን ወክዬ መስራት እፈልጋለሁ። ግን እኛ ዲጄዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በትምህርት መታገዝ አለብን ብዬ አስባለሁ»ምስል YAY Images/IMAGO

ምንተስኖት «ጣፋጭ ህይወት» ዝግጅት ላይ ያለውስ ተሳትፎ ምንድን ነው?

የዝግጅቱ አጋዥ ኃይል ነኝ የሚለው ምንተስኖት  የዝግጅቱን አላማ ጨምሮ ያብራራል። «ጣፋጭ ህይወት» ዓመታዊ የምስጋና ቀን ነው። ማህበራዊ ሚዲያን ተጠቅሞ ለማህበረሰቡ ጥሩ ስራ የሰራን ግለሰብ ወይም ተቋም እናመሰግናለን የሚል የሽልማት ስነ ሥርዓት ነው። ሁሌ ግንቦት 30 ላይ ይካሄዳል። ባለፈው ሳምንት ግንቦት 30 ላይ አራተኛውን አድርገናል። 4 ዓመት ሆኖናል ማለት ነው። ዋና አዘጋጁ አንተነህ ተስፋዬ ይባላል። እሱ ነው ሀሳቡን አመንጭቶ የጀመረው። እኛ ጓደኞቹ ደግሞ እናግዘዋለን። » ምንተስኖት ስለግል ህይወቱ ፊልም ለመስራት ይመኛል። ይህም ለወደፊት ብሎ ከያዛቸው በርካታ እቅዶቹ አንዱ ነው።  «ከዛ ውጪ በዲጄ ስራ ትልቅ ቦታ መድረስ እና ሀገሬን መወከል እፈልጋለሁ። እንዲሁም በሚዲያ ስራውም  ከዚህ በኋላም ትላልቅ ስራዎች እሰራለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ለሰዎች ትንሽ ነገር አበርክቶ ማለፍ እፈልጋለሁ»

«ጣፋጭ ህይወት» ዝግጅት
«ጣፋጭ ህይወት» ዓመታዊ የምስጋና ቀን ነው። ማህበራዊ ሚዲያን ተጠቅሞ ለማህበረሰቡ ጥሩ ስራ የሰራን ግለሰብ ወይም ተቋም እናመሰግናለን የሚል የሽልማት ስነ ሥርዓት ነው።ምስል Roberto Fichera Photo

እንደሱ ጠንካራ ላልሆኑ አካል ጉዳተኛ ወጣቶች ምን ይመክራል?

« ሰው አካል ጉዳተኛ ሆነም አልሆነ እዚህ ምድር ላይ በሁለት ህግ ነው የሚያልፈው ብዬ አስባለሁ። ጥሩም አለ መጥፎም አለ። እኔ እስከ 5 ዓመቴ ድረስ ሁሉ ነገሬን በእግሬ ነበር የማደርገው። የት ጋር መጥፎ ነገር እንደሚመጣ አናውቀውም። ስንማር መውደቅ መነሳት ይኖራሉ። ስራ ማግኘት ማጣት እና ብዙ ፈተናዎች አሉ። በመጀመሪያ ደረጃ ይህንን መቀበል ያስፈልጋል። ብዙ ወጣት አጭር ነገር ይፈልጋል። ቶሎ ነገሮችን ማግኘት የሚፈልግበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። ያ ግን አይሆንም። ወደ ፊት ማየት ያስፈልጋል። ሱስ ውስጥ ካለን ያንን መተው ነው።  እውቀት የሚያንሰን ከሆነ መማር ነው። ይህንን ስናደርግ ለሰው እና ለሀገር ጥሩ ነገር እናደርጋለን ብዬ አስባለሁ። »

ልደት አበበ

ኂሩት መለሰ