ምናንጋግዋ ቀጣዩ የዚምባብዌ ፕሬዚደንት ይሆኑ ይሆን? | አፍሪቃ | DW | 18.11.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ምናንጋግዋ ቀጣዩ የዚምባብዌ ፕሬዚደንት ይሆኑ ይሆን?

በዚምባብዌ የቀድሞው ምክትል ፕሬዚደንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ቀጣዩ ርዕሰ ብሔር እንደሚሆኑ አንዳንድ የፖለቲካ ታዛቢዎች ይናገራሉ። ከጥቂት ሳምንታት በፊት ፕሬዚደንቱ ከስልጣን ያነሱዋቸው አዞው የሚል ቅጽል ስም የተሰጣቸው ምናንጋግዋ ማን ናቸው?

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:04

ኤመርሰን ምናንጋግዋ

በዚምባብዌ የጦር ኃይሉ ባለፈው ረቡዕ፣ በጎርጎሪዮሳዊው  ህዳር 15፣ 2017 ዓም ስልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ የቀድሞው ምክትል ፕሬዚደንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ በብዙ የሀገሪቱ ዜጎች ዘንድ  እንደቀጣዩ ርዕሰ ብሔር እየታዩ ነው። የ75 ዓመቱ ምናንጋግዋ ላለፉት አሰርተ ዓመታት ከረጅም ጊዜው ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ ጎን በመሆን፣ ምንም እንኳን  አልፎ አልፎ ከርዕሰ ብሔሩ ጋር አልፎ አልፎ ልዩነት ቢኖራቸውም፣  በዚምባብዌ  ፖለቲካ መድረክ ላይ ዋና ሚና መጫወታቸውን በፕሪቶርያ የሚገኘው የደቡብ አፍሪቃ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ጥናት ተቋም፣ በምህፃሩ አይኤስኤስ ተንታኝ ዴሬክ ማቲሻክ ለዶይቸ ቬለ  ተናግረዋል።
«  ምናንጋግዋ ላለፉት 50 ዓመታት ከሙጋቤ ጎን በመሆን ሰርተዋል። ፕሬዚደንቱ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች አስወጋጅ ሆነውም ነው የሚታዩት። »
በዚምባብዌ ፖለቲካ ውስጥ ብዙም ድምፃቸው ሳይሰማ ስራቸውን እንደሚሰሩ የሚነገርላቸው የቀድሞው ምክትል ፕሬዚደንት ሲያስፈልግ ድንገት ጭካኔ የተመላበት ርምጃ እንደሚወስዱ ነው ማቲሻክ ያስታወቁት። በዚሁ ተክነውበታል በተባለው አሰራራቸውም የተነሳ አዞው የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቷቸዋል።  ከጦር ኃይሉ መፈንቅለ መንግሥት በኋላ ዚምባብዌ ምን ዓይነት የወደፊት እጣ እንደሚጠብቃት በወቅቱ አይታወቅም። ብሔራዊው የመገናኛ ብዙኃንን ተቆጣጥሯል። ይህን ቁጥጥሩንም የሚያላላ እንደማይመስል ታዛቢዎች ይናገራሉ። 
ኤመርሰን ምናንጋግዋ ልክ እንደ ሙጋቤ የብሪታንያ ቅኝ ግዛት በነበረችው የቀድሞዋ ደቡባዊ ሮዴዥያ የውሁዳኑ ነጮች አገዛዝ ዘመን ባደረጉት የነፃነት ትግል ይታወቃሉ።

በዚሁ ጊዜ በጎርጎሪዮሳዊው 1965 ዓም ታስረው የሞት ቅጣት ተፈርዶባቸው ነበር፣ግን በኋላ ብይኑ ወደ 10 ዓመት እስራት ተቀይሮላቸዋል። ከእስር ከተፈቱ በኋላ ወደ ዛምቢያ በመሄድ የሕግ ትምህርት ተከታትለዋል። የቀድሞዋ ሮዴዥያ በጎርጎሪዮሳዊው 1980 ዓም በይፋ ዚምባብዌ የሚል መጠሪያ ይዛ  ነፃነቷን በተጎናጸፈችበት ጊዜ  ወደ ትውልድ ሀገራቸው ተመልሰው በአዲሱ ነፃ መንግሥት ውስጥ የብሔራዊ የደህንነት ሚንስትር ሆነው ተሾሙ፣ በቀጠሉት ዓመታት በገንዘብ እና በመከላከያ ሚንስትርነት፣ እንዲሁም፣ የምክር ቤት አፈ ጉባዔ ሆነው አገልግለዋል።
ምናንጋግዋ በጭካኔአቸው በተለይ የታወቁት ሰሜን ኮርያ የሰለጠኑ ወታደሮች በ1980ኛዎቹ ዓመታት በመንግሥቱ  ተቃዋሚዎች አንፃር ያካሄዱትን እና ጉኩራሁንዲ በመባል የሚታወቀውን አስከፊ የኃይል ተግባር የታከለበትን ዘመቻ በመሩበት ጊዜ ነው። በዚሁ ዘመቻ ወደ 20,000 የሚጠጉ የንዴቤሌ ጎሳ አባላት እንደተገደሉ ነው የሚገመተው። 
« ምናንጋግዋ እንደ ጨካኝ፣ ብልጥ እና ነገሮችን አስቀድመው የሚያሰሉ በመሆን ይታወቃሉ። እና ብዙ ሰዎች እጅግ ይፈሯቸዋል። ዴሞክራትም አይደሉም። አንዳንድ በፍፁም ዴሞክራሲያዊ ያልሆኑ ሕጎች እንዲፀድቁ ገፋፍተዋል። በመሆኑም፣ ፕሬዚደንት ሙጋቤ የሚሞገሥ ዴሞክራሲያዊ አሰራር በተከተሉ ግለሰብ ይተካሉ የሚል የተሳሳተ እምነት ሊኖራቸው አይገባም። እንዳዚያ ዓይነት ሰው አይደሉም። »
የቀድሞው ምክትል ፕሬዚደንት ምናንጋግዋ ቀደም ባሉ ዓመታት በዕድሜ የገፉት የሮበርት ሙጋቤ ተተኪ ይሆናሉ ተብለው ይታዩ ነበር። ነገር ግን ፣ በ2004 ዓም ከገዢው ዛኑ ፒ ኤፍ ፓርቲ ዋና ጸሐፊነት ስልጣናቸው ተነሱ፣ ከአራት ዓመት በኋላ ግን ሙጋቤ ምናንጋግዋን እንደገና ወደ ስልጣን በመመለስ የፕሬዚደንታዊው ምርጫ ዘመቻ ዋና ኃላፊ አድርገው መሾማቸው ይታወሳል። አካራካሪ ከሆነው ምርጫ ፍፃሜ በኋላ ዩኤስ አሜሪካ እና የአውሮጳ ኅብረት ምናንጋግዋን በመርጫው ወቅት ተጫውተውታል ባሉት ሚና ማዕቀብ ጥለውባቸዋል፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ን ጭካኔ በታከለበት ርምጃ አሳደዋል ሲሉም ወቅሰዋቸዋል። ሆኖም፣ በሙጋቤ መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ስልጣን በመያዝ፣ በ2014 ዓም የዚያን ጊዜውን ምክትል ፕሬዚደንት ጆይስ ሙጁሩን ተክተዋል።  


የአይኤስኤስ ተንታኝ ማቲሻክ በሙጋቤ እና በምናንጋግዋ መካከል ባለፉት ጊዚያት የታዩት ልዩነቶች ለተከተሉት ስልታዊ አጋርነት ሁነኛ ማስረጃ መሆኑን አስረድተዋል። 
« የሁለቱ ግንኙነት ከወዳጅነት ይበልጥ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ነው  የሚመስለው።  ምናንጋግዋ የሙጋቤ ጉዳይ አስፈፃሚ እና የማይመቹ ጉዳዮችን አስወጋጅ ሆነው ቆይተዋል። እርግጥ፣ አብረው ሰርተዋል። አንዱ የሌላውን ሚስጥር ያውቃል። በመካከላቸው የሆነ አስተሳሳሪ ግንኙነት ተፈጥሯል ብለህ ልታስብ ትችላለህ። ግን፣ ሙጋቤ ምናንጋግዋን ከስራ ያባረሩበት መንገድ ሙጋቤ በምናንጋግዋ አኳያ በፍፁም ታማኝ አለመሆናቸውን የሚጠቁም ነው።  »
ይኸው ግንኙነታቸውም መበላሸት የጀመረው በምናንጋግዋ እና በፕሬዚደንቱ ባልተቤት ግሬስ ሙጋቤ  መካከል የ93 ዓመቱን ርዕሰ ብሔር በሚተካው ግለሰብ ጉዳይ ላይ ንትርክ ከተፈጠረ ወዲህ ነው። ቀዳማዊቷ እመቤት መፈንቅለ መንግሥት አሲረዋል በሚል በመውቀስ በአንድ ወቅት የፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ ተጓዳኝ በነበሩት ምናንጋግዋ አንፃር ግዙፍ ዘመቻ አካሂደውባቸዋል፣ የምናንጋግዋ ደጋፊዎችም በበኩላቸው ግሬስ ሙጋቤ ምናንጋግዋን ለመመረዝ ሞክረዋል በሚል ወቀሳ ሰንዝረዋል። 

Simbabwes ehemaliger Vizepräsident Emmerson Mnangagwa

ሳይመን ካያ ሞዮ


ከዚያ ህዳር ስድስት፣ 2017 ዓም ሮበርት ሙጋቤ ምክትላቸውን ታማኝነታቸውን አጉድለዋል በሚል ከስልጣናቸው እንዳባረሯቸው የማስታወቂያ ሚንስትር ሳይመን ካያ ሞዮ አስታውቀዋል።
« ምናንጋግዋ ኃላፊነታቸውን በመወጣቱ አሰራራቸው ላይ ወላዋይነት እንደታየባቸው ግልጽ ሆኗል። ምክትል ፕሬዚደንቱ በተደጋጋሚ እምነት እና አክብሮት የማጉደል፣ የተንኮለኝነት እና አስተማማኝ ያለመሆን ጸባይ  አሳይተዋል። ስራቸውን በትክክል በማከናወኑም ላይ ንዑሱን ጥረት ብቻ ነው ያደረጉት። »
ከስልጣን የተባረሩት ምናንጋግዋ ግን ርምጃውን በመቃወም፣ ፕሬዚደንቱም ሆኑ ባልተቤታቸው የዛኑ ፒኤፍ ፓርቲን እንደ ግል ንብረታቸው እንደፈለጉት ሊጫወቱበት እንደማይችሉ አስታውቀዋል። እና ለደህንነታቸው በመስጋታቸው ወደ ደቡብ አፍሪቃ የሸሹት  ምናንጋጋግዋ ጦር ኃይሉ ስልጣኑን ከያዘ በኋላ ወደ ትውልድ ሀገራቸው እንደተመለሱ አንዳንዶች ቢናገሩም፣ በወቅቱ የት እንደሚገኙ እስከትናንት ድረስ የሚታወቅ ነገር እንደሌለ የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

አርያም ተክሌ/ዳንየል ፔልስ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic