ምርጫ በደቡብ አፍሪቃ ማወዛገቡ | አፍሪቃ | DW | 11.05.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ምርጫ በደቡብ አፍሪቃ ማወዛገቡ

ደቡብ አፍሪቃ ምርጫ አከናውናለች። ረቡዕ ሚያዝያ 30 ቀን፤ 2011 ዓ.ም በተከናወነው ሀገር አቀፍ ምርጫ ምንም እንኳን ላለፉት 25 ዓመታት ተወዳጅነቱ እያሽቆለቆለ ቢሄድም አንጋፍው የአፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት ፓርቲ (ANC) አሸናፊ መኾን ችሏል። 72% ደቡብ አፍሪቃውያን በምርጫው ይሳተፋሉ ተብሎ ተጠብቆ ለምርጫ የወጡት ግን 65% ብቻ ናቸው። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:47

የአፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት ብዙም ሊኩራራ አይገባም

ደቡብ አፍሪቃ ምርጫ አከናውናለች። በምርጫው ገዢው ፓርቲ ቀንቶታል። 72% ደቡብ አፍሪቃውያን በምርጫው ይሳተፋሉ ተብሎ ተጠብቆ ለምርጫ የወጡት ግን 65% ብቻ ናቸው።  ደቡብ አፍሪቃ ረቡዕ ሚያዝያ 30 ቀን፤ 2011 ዓ.ም ባከናወነችው ሀገር አቀፍ ምርጫ ምንም እንኳን ላለፉት 25 ዓመታት ተወዳጅነቱ እያሽቆለቆለ ቢሄድም አንጋፍው የአፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት ፓርቲ (ANC) አሸናፊ መኾን ችሏል።  

እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1994 ዓ.ም በደቡብ አፍሪቃ የዘር መድልዎ ሥርዓት ከተወገደ አንስቶ ከተከናወኑ የደቡብ አፍሪቃ ስድስት ምርጫዎች ውስጥ ዘንድሮ (ANC)  ያስመዘገበው ውጤት ዝቅተናው ነው ተብሏል።  

የአፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት (ANC) ላለፉት 25 ዓመታት በደቡብ አፍሪቃ ገዢ ፓርቲ ኾኖ ሥልጣኑን እንደተቆጣጠረ ቆይቷል። ኾኖም ፓርቲው ቀደም ሲል በተለይ ለጥቊር አፍሪቃውያን የሰጣቸው ተስፋዎች በአብዛኛው ስኬታማ ሳይሆኑ መክነው ቀርተዋል። መጠነ-ሰፊ ሙስና እና አወዛጋቢ የመሬት ፖሊሲ ገዢው የደቡብ አፍሪቃ ፓርቲ በብርቱ የሚወቀስበት ጉዳይ ነው።  

የደቡብ አፍሪቃ የፖለቲካ ተንታኙ ማኮሲኒ ምጊቲዋ እንደሚሉት ከኾነ ግን ገዢው የአፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት ፓርቲ (ANC)የመራጮችን ልብ ለመያዝ እንቅስቃሴ የጀመረው አስቀድሞውኑ ነው።

«ሰዎች የሚሠሩላቸውን ነው የሚሹት። መልእክቱን ቀረብ ብላችሁ ተመልከቱ። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለANC ዋነኛ ችግሩ ሙስና ኾኖ ቆይቷል። ANC ፕሬዚደንቱን መርጧል፤ መሪውን መርጧል። የመረጠው ደግሞ ስለ ጸረ-ሙስና የሚያወራ ብቻ ሳይኾን፤ የሚታዩ ነገሮችን የሠራ ነው።»

እናም ደቡብ አፍሪቃውያን መራጮች ይህን የገዢውን ፓርቲ ዘመቻ ትኩረት ይሰጡታል ባይ ናቸው የፖለቲካ ተንታኙ። ደቡብ አፍሪቃውያን በየምርጫ የሚደረጉ ቃል ኪዳኖች ተግባራዊ ባለመሆናቸው መራጮች ብዙውን ጊዜ የውጭ ዜጎች ላይ ቊጭታቸውን ሲወጡ ይስተዋላል።

 በዶይቸ ቬለ የአፍሪቃ ክፍል ባልደረባ ደቡብ አፍሪቃዊቷ ጋዜጠኛ ቤኒታ ፋን ኢሲያን ተመራጮች ለተከፉ ደቡብ አፍሪቃውያን ጥያቄ እንደተለመደው መልስ የማይሰጡ ከኾነ ዳግም የውጭ ሃገራት ነዋሪዎች ተጎጂ ሊኾኑ ይችላሉ ስትል ስጋቷን ገልጣለች።

«እንደሚመስለኝ መንግሥት የዜጎቹ ፍላጎት ማሟላት የተሳነው እንደመኾኑ አንጻር ደቡብ አፍሪቃውያን መንግሥት ፍላጎታቸውን ማሟላት እዲሳነው ያደረጉት መጤ የሚሏቸው ሰዎች ናቸው ብለው ሊወስዱ ይችላሉ። 

ተደጋጋሚ ኹከት፤ ብጥብጥ እና ሥርዓት አልበኝነት ባስተናገደችው ደቡብ አፍሪቃ በዘንድሮው ምርጫ የአፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት ማሸነፉ ብዙም ሊያኩራራው የሚገባ አይመስልም። ደቡብ አፍሪቃውያን ለፓርቲው ያላቸው ፍላጎት ከማሽቆልቆሉ ጋር ተደምሮ የማኅበራዊ ፍትኅ ጥያቄያቸው ምላሽ ካላገኘ ዳግም ቀውስ ሊከሰት ይችላል እንደተንታኞች ገለጣ።

በምርጫው ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎሳ የሚመሩት ገዢው የአፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት ፓርቲ እና ምሙሲ ማይማኔ የሚመሩት የዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ጥምረት በትናንትና ውጤት መሰረት 57 እና 20 ከመቶ የመራጮች ድምጽ አግኝተዋል። ዓርብ እለት 35 ትንንሽ ፓርቲዎች ለምርጫ ኮሚሽን ቅሬታቸውን አሰምተዋል። በአዳንድ ቦታዎች ከምርጫ ሥርዓቱ ውጪ የኮኑ ጉዳዮች በመከሰታቸው ሒደቱ እንዲጣራ ጠይቀዋል። ምናልባትም ምርጫው ዳግም ሊካሄድ ይገባል ብለዋል። የደቡብ አፍሪቃ የምርጫ ኮሚሽን ምሶቶ ሞይፔያ ደቡብ አፍሪቃውያንን በምርጫው ያወዛገበው የምርጫ መለያ የጣት ቀለም የሚለቅ ነው፤ ፈጽሞ የማይለቅ ነው የሚለውን ቅሬታ ከእውነት የራቀ ብለውታል።

«ቅሬታዎች አልቀረቡልንም ብለን አንክድም። ነገሩን ግልጽ ለማድረግ ሞክረናል። ይህ ጣት ላይ የሚቀባው ኬሚካል ለየት ያለ ነው። ከምን ከምን ተቀምሞ እንደተሠራ አንናገርም፤ ምስጢር ነው። ምክንያቱም ከምን እንደተሠራ ካወቅህ ቀለሙ ጣትህ ላይ ምን እንደሚያቆየው እና ምን ሊያጠፋው እንደሚችል ታውቃለህ። የጣት ቀለሙን የሚያጠፋ ነገር የለም ማለት አልችልም። ያ ግን በዚህ ምርጫ ተካሂዷል እያልኩ አይደለም። እኔ የምላችሁ ቀለሙን ከጣት ላይ መቼም ፈጽሞ ማጥፋት አይቻልም የሚለውም ከእውነት የራቀ ፈጠራ እንደኾነ ነው። እስኪ ፍትኃዊ እንሁን፤ ቀለሙን ማስለቀቅ ስለተቻለ ብቻ ምርጫው ፍትኃዊ አይደለም ማለት አይደለም። ይኼ እጅግ ከእውነት የራቀ ነው።»

በኔልሰን ማንዴላ የመሪነት ዘመን በርካታ ደቡብ አፍሪቃውያንን በተስፋ ያነቃቃው አንጋፍው የአፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት ፓርቲ (ANC) በዘመኑ የምርጫ ውዝግብ ብቻ ሳይሆን የፓርቲው ኅልውናን የሚፈታተኑ ተግዳሮቶችን አልፎ ዛሬ ላይ ደርሷል። ፓርቲው  በብርቱ በሚተችበት የሙስና ጉዳይ የፓርቲው የቀድሞ መሪ እና የሀገሪቱ የያኔ  ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ ሥልጣናቸውን እስከመልቀቅ ደርሰዋል። አሁን የቀረበው የምርጫ ውዝግብ የምርጫ ኮሚሽን እንደሚለው ከሐሰት የራቀ ኾኖ አንጋፋው ፓርቲ ከደቡብ አፍሪቃውያን ጋር የሚያስታርቀውን እድል ዳግም ያግኝ አለያም ደቡብ አፍሪቃ በምርጫ ውዝግብ ትናጥ አለየለትም።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ 

Audios and videos on the topic