ምርጫ በናይጀሪያ | አፍሪቃ | DW | 16.04.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ምርጫ በናይጀሪያ

ባሳለፍነዉ ሳምንት መጨረሻ ቅዳሜ ዕለት በናይጀሪያ ለ36ቱ ፌደራል ግዛቶች የምክር ቤት አባላትንና ገዢዎችን ለመምረጥ 60ሺ ህዝብ ወጥቷል።

ምርጫ በናይጀሪያ

ምርጫ በናይጀሪያ

ይህ ደግሞ ብሄራዊ ምርጫ በአገሪቱ ሊደረግ አንድ ሳምንት ሲቀረዉ የተከወነ ነዉ። ከምርጫዉ በፊት ቢያንስ ለ100 ሰዎች ህልፈተ ህይወት ምክንያት የሆነ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ ታይቷል። በምርጫዉ ዕለትም መላ አገሪቱ ሰላም ዉላለች ማለት አይቻልም።

ከተለያዩት የምርጫ ጣቢያዎች አጠራጣሪ የተባለዉ ዉጤት ወደፌደራላዊ ሌጎስ ግዛት የምርጫ ፅህፈት ቤት ማዕከል ትናንት መጥቷል። በአብዛኛዉ የናይጀሪያ ፌደራላዊ ግዛቶች የምርጫ ኮሚቴ ማምሻዉ ላይ እንኳን የተመረጡትን ሰዎች ማንነት በይፋ አጠናቆ ሊያሳዉቅ አልቻለም። ሁኔታዉ በተለያዩ ፓርቲዎች ደጋፊዎች ዘንድ መከፋትን ፈጥሯል። በተለይ ደግሞ በመጀመሪያዉ ዉጤት ወደኋላ የቀሩት ፓርቲዎች ባጠቃላዩ ዉጤት ላይ ተቃዉሟቸዉን አሳይተዋል።

በሌላ በኩል በሌጎስ ምክትል ፕሬዝደንቱ አቲኩ አቡባከር የሚመሩት አክሽን ኮንግረስ ፓርቲ እንደታሰበዉ ማሸነፊ ተሳክቶለታል። በአገር ዓቀፍ ደረጃ ደግሞ የፕሬዝደንት ዖባሳንጆ people’s Democaratic Party አሸናፊ ሆኖ እንደሚወጣ ተገምቷል። በምርጫዉ ዕለት በተለይ ሌጎስ የሚያስገርም ሰላም ነበር የተስተዋለባት። መኪና ለማሽከርከር የተከለከለባቸዉን ጎዳናዎችም ወጣቶች እግር ኳስ ሲጫወቱባቸዉ ዉለዋል። በማዕከላዊ ቪክቶሪያ ደሴት በርካታ መራጮች በመጀመሪያ ያዩትን ፀጥታ አላመኑም ነበር። ጥቂቶቹም የምርጫ ጣቢያዎቹ ሊዘጉ አንድ ሰዓት ገደማ ሲቀራቸዉ ነዉ ድምፃቸዉን ሰጥተዉ ያጠናቀቁት።

«ነገሮች በሰላም መካሄዳቸዉን ሳስተዉል ቤቴን ትቼ ለመርጥ መጣሁ። ከምርጫዉ በፊት ሰዎች እዚህም እዚያም ችግር ሊፈጠር ይችላል ሲሉ ነበር።»
XXXXXX
«ሁሉም ነገር በደህና ሁኔታ ላይ ነዉ የሚገኘዉ፤ ችግር የለም!»
XXXXXX
«በእኔ እምነት እዚህ ካልተገኘህ ጥሩ መሪ መምረጥ አትችልም። መዉጣትና ለእነሱ ድምፅ መስጠት አለብን። ያሰደደን የለም፤ ከማንም ጉቦ አልተቀበልኩም። ራሴ ነኝ የመጣሁት ምክንያቱም የናይጀሪያ ህብረተሰብ አካል ነኝ።»

በምርጫዉ ሊያሸንፍ ይችላል ብለዉ ተስፋ ስለሚያደርጉት ፓርቲም ሲጠየቁ ለእነሱ ዋናዉ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይልና የዉሃ አቅርቦት ሊያደርግ የሚችለዉ ወገን መሆኑን ነዉ የሚናገሩት። ሌላዉ ቀርቶ በዘመናዊቷ የሌጎስ ከተማ ባለፀጎቹ ብቻ ናቸዉ ይህን ሊያገኙ የሚችሉት። እንዲያም ሆኖ ብዙዎች ከምርጫዉ ያን ያህል የተሻለ ለዉጥ አይጠብቁም፤ ለዚህም ነዉ እየተጠራጠሩ ድምፅ ለመስጠት የወጡት። የናይጀሪያ የጠበቆች ቢሮ ሊቀ መንበርና ከምርጫ ታዛቢዎች አንዱ ዖሊሳ አግባኮባ የሰዉ ስሜት ማጣት እንዳሳስገረማቸዉ ይናገራሉ፣

«ህዝቡ በእዉነትም ፍላጎት የለዉም። ምክንያቱም ማንን ነዉ የሚመርጡት? የምርጫዉ ሂደት ይከበራል ብለዉ አያምኑም።»
ከዚህ ሌላ ግን የሌጎሱ የምርጫ ታዛቢ ከተማዋ በሰላም መዋሏን ነዉ የሚናገሩት። በአንፃሩ ምርጫዉ አንዳንድ ችግር እንዳለበት ተጠቅሷል። ለምሳሌ በርካታ የምርጫ ጣቢያዎች በጣም ዘግይተዉ ነዉ የተከፈቱት። ብሄራዊ ጉባኤ ከተባለዉ ተቋም ዎሌ ዖኩኒ ይህንና መሰል ግድፈቶችን በመንቀስ ይተቻሉ

«አንዳንድ መራጮች ስማቸዉን ማግኘት አልቻሉም። ለመምረጥ የተመዘቡት ማለት ነዉ። የት ተመዘገቡ? አንዳንድ ባለስልጣናት ወደምርጫ ጣቢያ እየመጡ እንዲያጣሩ ይነግሯቸዋል። ስማቸዉ ይገኝ እንደሆን። ግማሾቹ አሁንም ስማቸዉን ሊያገኙ አልቻሉም። ያ ካጋጠመን መሰረታዊ ችግሮች አንዱ ነዉ። ከዚህ ሌላ ወታደሮችን ወደየከተማዉ የማሰማራት ነገር አለ። ያ ደግሞ ሰዎችን የሚያስፈራ ነዉ። በሌጎስ ደሴት አካባቢ የሚገኙ አንዳንድ ሰዎች ሊወጡ አልፈለጉም።»

ከዚህም በተጨማሪ የምርጫ ቁሳቁስ መዘግየት ቀድመዉ አልተዘጋጁበትም አስብሎ የምርጫ ኮሚቴዉን አስወቅሷል። የምርጫ ኮሚሽኑ ደግሞ የለም በሚል የራሱን መከላከያ ያሰማል

«ቁሳቁሱ በሰዓቱ ነበር በየስፍራዉ የደረሱት። ግጭት የሚባል አልተከሰተም ሁሉም ሰላም ነበር። እኔ በነበርኩበት ጣቢያ ደግሞ ለምርጫ የወጣዉ ህዝብ ከፍተኛ ነበር።»

ስለጉዳዩ ከየአቅጣጫዉ የተሰማዉ ዘገባ እንደሚያሳየዉ የምርጫ ቁሳቁስ እስኪደርስላቸዉ ለረዥም ሰዓታት ያልተከፈቱ ጣቢያዎች እንደነበሩ ነዉ። ከሌጎስ በቀር በበርካታ ከተሞች የመንግስት ኃይል በስፋት ተሰማርተዉ ነበር። በኒጀር ዴልታ ሃርኮት በርካታ የፖሊስ ጣቢያዎች ጥቃት ሲደርስባቸዉ በተፈጠረዉ ግጭትም ስምንት ሰዎች ሞተዋል። በደቡብ ምስራቅ ናይጀሪያ ደግሞ ምርጫዉ ትናንት ተሰርዟል። በርካታ የምርጫ ሳጥኖች ተሰርቀዋል፣ የምርጫ ረዳቶችም ታግተዋል።የናይጀሪያ ፖሊስ እንዳስታወቀዉ ከምርጫዉ ጋ በተገናኘ በ87 ስፍራዎች ችግር ተቀስቅሶ 218 ሰዎች ታስረዋል። ለናይጀሪያ ግን ይህን የመሰለ የሰከነ ምርጫ ተደርጎ አይታወቅም ተብሏል።