ሜርክል እና የስደተኞች መርሃቸው | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 23.08.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

ሜርክል እና የስደተኞች መርሃቸው

ጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ስደተኞች በብዛት ወደ ጀርመን እንዲገቡ ከፈቀዱ ወደ አንድ ዓመት እየተጠጋ ነው ። በወቅቱም ጉዳዩ ላሰጋቸው ወገኖች «እንወጣዋለን» በማለት ህዝባቸውን አበረታተው ነበር ።ይህንኑ አባባላቸውን ከአንድ ወር በፊትም ደግመውታል

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:21

ሜርክል እና የስደተኞች መርሃቸው

ካለፈው ዓመት የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የበጋ ወራት አንስቶ ነበር ፣ የባልካን የጉዞ መስመርን ተከትለው በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሶርያውያን አፍጋናውያን እና ኢራቆች የሚያመዝኑባቸው ስደተኞች ጀርመን መግባት የጀመሩት ።ይህ የሆነውም ጀርመን ሳይታሰብ ድንበሯን ክፍት ካደረገች በኋላ ነው ። በዚሁ መሠረት ከጎርጎሮሳዊው መስከረም 2015 እስከ ሐምሌ 2016 ፣ 900,623 ስደተኞች ጀርመን መግባታቸው ተመዝግቧል ። ያኔ ጀርመን በሯን ለስደተኞች ክፍት ማድረጓ በተቀረው ዓለም ሲደነቅ ከሃገር ውስጥ እርምጃውን የደገፉ እንደነበሩ ሁሉ የተቃወሙም አልጠፉም ። በወቅቱ ስጋታቸውን ለሚገልጹ ወገኖች መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ማድረግ እንችላለን እንወጣዋለን ሲሉህዝቡ ስደተኞችን እጁን ዘርግቶ እንዲቀበል ማድረግ ችለው ነበር ።ሆኖም ጀርመን ስደተኞቹን የምታስገባበት መንገድ ፣ በአንዳንድ አካባቢዎችም በቂ ቅድመ ዝግጅት አለመደረጉ ፣ከገቡም በኋላ አንዳንድ አስተዳዳራዊ ችግሮች መከሰታቸው ሲያወዛግብ ሰንብቷል ።በአጠቃላይ ጀርመን ባለፈው አንድ ዓመት 1.1 ሚሊዮን ስደተኞችን ማስገባቷ ብቻ ሳይሆን በሯን ለስደተኞች ክፍት ማድረጓ መቀጠሉም እንዲሁ ሌላው አከራካሪ ጉዳይ ነው ። ከተገመተው በላይ ስደተኛ ሲገባ ፣እርምጃውን በቅጡ ያልታሰበበትና አቅምን ያላገናዘበ ነው የምንቀበላቸው ስደተኞች ቁጥር ገደብ ይኑረው ሲሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ፖለቲከኞች መቃወም ጀመሩ ። ከሁሉ በላይ ስደተኞች በብዛት የሚገቡበት የባየርን ፌደራዊ ክፍለ ሃገር አስተዳዳሪ የክርስቲያን ሶሻል ህብረት ፓርቲ በምህፃሩ የCSU ተቃውሞ የበረታ ነበር ። የባየርን ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ጠቅላይ ሚኒስትር ኾርስት ዜሆፈር

ሜርክል ጀርመን ድንበሯን ለስደተኞች ክፍት እንድታደርግ የደረሱበትን ውሳኔ የተቃወሙት ገና ከመነሻው ነበር ።

«ይህ ስህተት ነበር ። ሊደገም የማይገባው ስህተት ።የስደተኞቹ ቁጥር እየጨመረ አሁን እንደሆነው ሙሉ በሙሉ ከቁጥጥር ውጭ ይሆናል ።»

ሜርክል ግን ለእህት ፓርቲያቸውም ሆነ ለህዝቡ ደጋግመው የሚያስተላፉት መልእክት አንድ ነበር ። «ማድረግ እንችላለን» እንወጣዋለን የሚል።

«ጀርመን ጠንካራ ሃገር ናት ። ጉዳዩን በሚመለከት ልንከተለው የሚገባን አካሄድ ይህ ሊሆን ይገባል እስካሁን ብዙ ነገሮችን ማድረግ ችለናል ፤ ይህንንም ማድረግ እንችላለን ፤ እናደርገዋለንም መንገዳችንም ላይ መሰናክል ካጋጠመን መወጣት ይኖርብናል ። ይህ ነው መደረግ ያለበት»

ከአንድ ዓመት በኋላ ሜርክል በዚሁ አቋማቸው እንደፀኑ መሆናቸውን ነበር ጀርመን ውስጥ ከመካከላቸው ሁለቱ በስደተኞች የተፈፀሙ ተከታታይ ጥቃቶች ከደረሱ በኋላ በሰጡት መግለጫ ያሳወቁት ።ባሳም ቲቢ የፖለቲካ ሳይንቲስት ናቸው ። በትውልድ ሶሪያዊው ቲቢ ከጎርጎሮሳዊው 1973 እስከ 2009 በገቲንገን ዩኒቨርስቲ መምህር ነበሩ ። የሜርክል «እንወጣዋለን እንዲሁ የሚነገር እንጂ የሚጨበጥ ነገር የለውም ይላሉ ።

«እንወጣዋለን ለኔ መፈክር ነው ።ይህ ጥሩም መጥፎም ሊሆን ይችላል ። ያ እኔን ብዙም አያስጨንቀኝም ።የሚያሳስበኝ ነገር ሜርክል ይህን ሲሉ እንዴት ሊያሳኩ እንዳሰቡ እቅድ አላቸው ወይ የሚለው ነው ። እኔ ይህን አላገኘሁም ። ሰዎች ስሜት አላቸው ። የስሜታችን ዋናው ጥቅም መማር መቻላችን ነው ። ወይዘሮ ሜርክል እንችለዋለን ባሉ በዓመቱ ጀርመን ውስጥ በሐምሌ ወር በደረሱት ተከታታይ አደጋዎች ምክንያት እረፍታቸውን አቋርጠው በርሊን ከተመለሱ በኋላ ተምረው ተመልሰዋል ተብሎ ነበር የታሰበው ።ሆኖም «እንችለዋለን » ነው ያሉት ።ይህን እንደሰማሁ የት ነው የምኖረው ነበር ያልኩት»

በባሲም ቲቢ አባባል ሜርክል ችግሩን የተገነዘቡ አይመስልም ። ይህ እንደርሳቸው ሞኝነት ነው ። ከአምና አንስቶ እንወጣዋለን ማለታቸውም በርሳቸው አስተያየት ሞኝነት ሆኖ ነው የሚሰማቸው ። ለርሳቸው ሜርክል የሚያደርጉት

የሞራል ሃላፊነት መውሰድ እንጂ መፍትሄ አይደለም ። የኤኮኖሚ ምሁር አቶ ስዩም ጀርመን ሲኖሩ 40 ዓመት ሆኗቸዋል ። ሜርክል የዛሬ አንድ ዓመት ስደተኞች ጀርመን እንዲገቡ የፈቀዱበትን ውሳኔ ይደግፋሉ ። በርሳቸው አስተያየት ውሳኔው የሃገሪቱን ህግ መነሻ ያደረገ በመሆኑ ትክክለና ነበረ ።

ዶክተር ፀጋዮ ደግነህም የኤኮኖሚ ምሁር ናቸው ጀርመን ለ30 ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ኖረዋል ። ሜርክል እንወጣዋለን ሲሉ ስደተኞች ማስገባታቸው ሙሉ በሙሉም ባይሆን በተወሰነ ደረጃ ተሳክቷል ይላሉ ።

ክላውስ ቡዮን ዛርላንድ የተባለው የጀርመን ፌደራዊ ክፍለ ሃገር የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናቸው ። በርሳቸው አስተያየት እስካሁን ብዙ ተደርጓል የሚቻለው ሁሉ ተሰርቷል ።ውጤቱን ለማየት ግን ትዕግስት ያስፈልጋል ይላሉ ።

«እቅዳችንን ልናሳካ የምንችለው ሰዎችን ሰዎቹን በተቻለ ፍጥነት ከህብረተሰቡ ጋር ማዋሃድ ስንችል በተለይም በተቻለ ፍጥነት ቋንቋ ቅንዲማሩ ስናደርግ ነው ።ከመጡት ስደተኞች አብዛኛዎቹ ከና የትምህርት ደረጃ ጋር የሚስተካከል ትምሕርት የላቸውም ።በተለይም ሴቶቹ የሙያ ስልጠና የላቸውም ።ይህ መፍትሄ ሊፈለግለት የሚገባ ጉዳይ ነው ። ለምሳሌ የቋንቋ ትምሕርት የሚከታታሉ ሴቶች አምስት ሰዓት ላይ ወደ ቤታችን እንሂድ ይላሉ ። ለምን ሲባሉ ምግብ ማብሰል አለብን ነው ምክንያታቸው ። ቤት ያሉት ባሎቻቸው እነርሱ ምግብ እንዲያበስሉላቸው ነው የሚጠብቁት ።ይሄ ሁሉ ሊተኮርበት ይገባል ።

ዶክተር ፀጋዮም ጀርመን የሚመጡ ስደተኞች ከህብረተሰቡ ጋር ተቀራርበው ለመኖር እና ተቀባይነትም ለማግኘት የበኩላቸውን ጥረት ማድረግ አለባቸው ይላሉ ።

ጀርመን በርካታ ስደተኞችን ካስገባች ከአንድ ዓመት በኋላ ሜርክል እንወጣዋለን ያሉት ምን ያህል እንደተሳካላቸው ወደ ኋላ መለስ ብሎ የተመለከተው የዛሬው አውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅታችን በዚሁ ያበቃል ። አስተያየት ጥቆማ እንዲሁም ጥያቄ ካላችሁ በኢሜል በSMS በፌስቡክ እንዲሁም በስልክ ተዉልን እናስተናግዳለን ።

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች