ሜርክል ኢትዮጵያ የደወሉበት ጊዜ ያጠያይቃል | ዓለም | DW | 13.02.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ሜርክል ኢትዮጵያ የደወሉበት ጊዜ ያጠያይቃል

የጀርመን መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ጠቅላይ ሚንሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ትናንት በስልክ ደውለው ማነጋገራቸውን በተመለከተ፦ ጀርመን የሚገኘው ለተጨቆኑ ሕዝቦች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ኃላፊ ኡልሪሽ ዲሊዮስ «ሜርክልና መንግሥታቸው እስካሁን የት ነበሩ?» ሲሉ ተችተዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:16

«ሜርክል እና መንግሥታቸው እስካሁን የት ነበሩ?» - ዲሊዮስ

የጀርመን መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ጠቅላይ ሚንሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ትናንት በስልክ ደውለው ማነጋገራቸውን የፌደራል ጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በድረ ገፁ ትናንት ይፋ አድርጓል። ጀርመን የሚገኘው ለተጨቆኑ ሕዝቦች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት (Gesellschaft für bedrohte völker) ኃላፊ ኡልሪሽ ዲሊዮስ «ሜርክል እና መንግሥታቸው እስካሁን የት ነበሩ» ሲሉ የስልክ ንግግሩ ለኢትዮጵያ መንግሥት የሚጠቅም ነው በማለት ተችተዋል። 

የጀርመን መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ከጠቅላይ ሚንሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ትናንት በስልክ መነጋገራቸው «ጊዜውን የጠበቀ» አለመኾኑን ኡልሪሽ ዲሊዮስ ተናገሩ። ጀርመን የሚገኘው ለተጨቆኑ ሕዝቦች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ኃላፊው ኡልሪሽ ዲሊዮስ የጀርመን መንግሥት ኢትዮጵያውያን በሚፈልጉበት ወቅት አልደረሰላቸውም ሲሉ ትናንት የተደረገውን የስልክ ንግግር ተችተዋል። 

«ዕውነቱን ለመናገር የስልክ ንግግሩ የተደረገበት ጊዜ እኛም ቢሆን ግራ ነው የሆነብን። የጀርመን መንግሥት ላለፉት ሰባት ወራት ድምጹን አጥፍቶ ቆይቶ ነበር። በኢትዮጵያ ኹኔታዎች በከፉበት ወቅት ጀርመን ያለችው የተሰማ ነገር  የለም። አሁን ይቅርታ ተደረገ ሲባል ድንገት የጀርመን መንግሥት ብቅ ብሎ እንዴት ያለ ድንቅ ነገር ነው አለ። ያ ጥሩ ነው፤ ግን ከልብ የኾነ አይደለም። የጀርመንን ድምጽ በምንፈልግበት ወቅት ሰዎች በሚታሰሩበት ወቅት አጥተናል።»


የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድረ ገጽ ትናንት «የጀርመኗ መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር የስልክ ንግግር» ማድረጋቸውን አስነብቧል። ስለ ኢትዮጵያ የውስጥ ፖሊቲካ ሁኔታ መራኂተ መንግሥቷ በስልክ ንግግራቸው ወቅት ማንሳታቸውንም ጽሑፉ ጠቅሷል። ይህ የስልክ ንግግር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይሆን ለመንግሥት የሚጠቅም መኾኑን ነው ዴሊዩስ የሚናገሩት። 

«እንደሚመስለኝ ብዙ የሚያመጣው ነገር የለም። ለኢትዮጵያ በእርግጥ፦ ይኸው መራኂተ-መንግሥቷ ደውለው ላደርግነው ነገር እንኳን ደስ ያላችሁ አሉን በማለት የሚያወሩበትን ዕድል ይሰጣል። ይበልጥ ዲሞክራሲያዊ መንገዶች እንዲመቻቹ መራኂተ-መንግሥቷ ምኞታቸውን መግለጣቸው ጥሩ ነው፤ ግን የፖለቲካ እስረኞች ተከታታይ እንክብካቤ ይሻሉ። ታዲያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ዘብጥያ ለወረዱ 50 ሺህ 60 ሺህ ለሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች ጀርመን ያደረገችው እንክብካቤው የት አለ? ስለዛ የሰማነው ነገር የለም።»

መራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ትናንት ከጠቅላይ ሚንሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ያደረጉት የስልክ ንግግር ለጀርመን መንግሥት የእስረኞችን መፈታትን በተመለከተ ቀድሞም «ብለን ነበር» ከማለት የዘለለ ፋይዳ የለውም ሲሉም አክለዋል። 


«ለጀርመን የሚያመጣው ብቸኛው ነገር ቢኖር የውጭ ጉዳይ ሚንሥትሩ እና የመራኂተ-መንግሥቷ ጽ/ቤት ለዲሞክራሲ የበለጠ ርምጃ ሊወሰድ ይገባል ስንል ቀደም ሲል አስጠንቅቀን ነበር ማለት መቻላቸው ነው። ያ ጥሩ ነው፤ ግን  ያው እንዳልኩት ያ በቂ አይደለም።»

ትክክለኛ ፍትኅ ቢኾን ኖሮ እስረኞችን ይቅርታ አደረግኹ ብሎ መልቀቅ ሳይኾን ክሳቸውን አንስቶ «ጥፋተኞች አይደላችሁም ማለት ነበር» ብለዋል። «ጀርመን የኢትዮጵያ የልማት ተባባሪ ሀገር ናት» ያሉት ኡልሪሽ ዲሊዮስ፦ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ጭቆናው ሲበረታ ያን ለማስቆም ያደረገችው አንዳችም ነገር የለም ሲሉ ተችተዋል። ይልቁንም ጀርመን ሀገሯ ያሉ ስደተኞች ጉዳይ ይበልጥ ያሳስባታል ብለዋል። የጀርመን ልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ማቅናታቸውንም ጠቁመዋል። 

«በእርግጥ ስለልዑካኑ ጉዞ ሰምተናል፤ ግን የመነጋገሪያ አጀንዳው ምን እንደሆነ የምናውቀው ነገር የለም። የምናውቀው ነገር ቢኖር የስደተኞች እና ፍልሰተኞች ጉዳይ ጀርመን ውስጥ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መኾኑን ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ የስደተኞች መሸጋገሪያ ሀገር ናት፤ ለምሳሌ ከኤርትራ። ከዛው ከኢትዮጵያም እጅግ በርካታ ሰዎች ይሰደዳሉ። ባለፉት ሦስት ዓመታት እንኳን እዚህ ጀርመን ሀገር ለደህንነታቸው ጥበቃ ሲሉ የመጡ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አሉ። እናም እነሱን በተመለከተ ምን ማድረግ ይገባል የሚለውም ጉዳይ አብይ ጥያቄ ነው።»

ለተጨቆኑ ሕዝቦች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ኃላፊው ኡልሪሽ ዲሊዮስ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚከሰተው የሰብአዊ መብት ጥሰት ጀርመን  ኃላፊነት አለባት ብለዋል። ለዚህም የጸጥታ ኃይላት ሥልጠና መስጠቷን፣ መንግሥት በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ይኾናል በሚል ተስፋ ብዙ መጠበቋን ጠቅሰዋል።  በኢትዮጵያ አያሌ ነገሮች ሲከሰቱ ጀርመን ፊቷን ማዞሯን ግን ታቁም ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic