ሜሢ ለ4ኛ ጊዜ ምርጥ ተጫዋች ተባለ | ስፖርት | DW | 08.01.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ሜሢ ለ4ኛ ጊዜ ምርጥ ተጫዋች ተባለ

አርጀንቲናዊው እውቅ እግር ኳስ ተጫዋች ሊዮኔል ሜሢ ለ4ኛ ጊዜ ምርጥ የአመቱ የአለም እግር ኳስ ተጫዋች በመሆን ተመረጠ። ከሴቶች ደግሞ የዮኤስ አሜሪካ አጥቂ ተጫዋች አቢ ቫምባህ ምርጥ ተጫዋች ተብላለች።

የዓለም እግር ኳስ ፌዴሬሽን በምህጻሩ ፊፋ እአአ በ2009 , 2010 እና 2011 ዓ ም የአመቱ ምርጥ ተጫዋች አድርጎ የመረጠውን የስጳኛውያኑ የእግር ኳስ ቡድን - የኤፍሲ ባርሴሎና አጥቂ ተጫዋች ሊዮኔል ሜሲን ዘንድሮም እንደገና የአለም ምርጥ እግር ኳስ ተጫዋች ሲል በድጋሚ ሰይሞታል። ይህም የ25 አመቱን ወጣት ብቸኛ ባለ ክብረ ወሰን ጠባቂ አድርጎታል።

ሊዮኔል ሜሢ የቡድኑን ባልደረባ አንድሬ ኢኒስታ እና ፖርቱጋላዊውን የ ሪያል ማድሪድ ተጫዋች ክሪስቲያኖ ሮናልዶን በመብለጥ ለ4ኛ ጊዜ «ምርጥ የእግር ኳስ ተጫዋች» ተብሎ በመመረጥ በኳስ የተመሰለውን የወርቅ ሽልማት ተቀብሏል። « ረጋ ብዬ በሁኔታው እየተደሰትኩ ነው። » ነው ያለው ሜሢ ። ሽልማቱ የተሰጠው ጋዜጠኞች፣ ታዋቂ የእግር ኳስ እጩዎች እና የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች በተሰበሰቡበት ነው። 23 የእግር ኳስ እጩዎች ያካተተው የአለም እግር ኳስ ፌደሬሽን -ፊፋ መዘርዝር ላይ በእጩነት ለጀርመን ብሔራዊ ቡድን የሚጫወቱት ማኑኤል ኖየር - ከባየር ሙኒክ እና ሜሱት ኦዚል - ከሪያል ማድሪድ ይገኙበታል። ይሁንና ሌሎች ሁለት ጀርመንያውያን እጩ ተጫዋቾችን ጨምሮ ማንኛቸውም ለሽልማቱ ሊበቁ አልቻሉም።ስለሆነም ብቸኛው የጀርመን ባለክብረወሰን ሎታር ማቲዎስ እኢአ 1990 እና 1991 ዓም ሆኖ ይቆያል።

የባየር ሌቬርኩዝን ተጫዋች እስቴፋን ራይንአርትስት ፤ ሌቨርኩዝን ሰባት ለአንድ በባርሴሎና ሲሸነፍ ራይንአርትስት ስለ ሚሢ እንዲህ ነበር ያለው። «አስገራሚ ነው። አንዳንዴ ምንም ሳይካፈል በኳስ ሜዳ ይቆማል። ማንም ይጫወት እና ኳስ ይደርሰዋል ብሎ እንኳን አይገምትም። ከዛ ባንዴ ከምንም ውስጥ ብቅ ይላል።»

የሜሢ የ4ኛ ጊዜ መመረጥ የዮናይስት እስቴት የሴቶች አጥቂ የእግር ኳስ ተጫዋች -አቢ ቫምባህ ባለድልነትን ጎልቶ እንዳይወጣ ያድርግ እንጂ፤ ቫምባህ ዮኤስ አሜሪካ በለንደን በነበራት የኦሎምፒክ ግጥሚያ አምስት ግብ በማስቆጠር ብቸኛ ተጫዋች ነበረች። የ 32 አመቷ አሜሪካዊት ቅፅል ስሟም ቦምቧ የሚል ነበር። ቫምባህ የቡድን ባልደረባዋን አሌክስ ሞርጋን እና የብራዚል ኮከብ ተጫዋች ማርታን በመቅደም አሸናፊ ሆናለች። ማርታ አምስት ጊዜ የዚህ የአለም ምርጥ እግር ኳስ ተጫዋች ሆና መቆየቷ የሚታወስ ነው። እኢአ ከ 2001-2002 ክብረ ወሰኑን ይዛ ከነበረችው -ሚያ ሃም- በኋላ ቫምባህ ሌላኛዋ ዮ ኤስ አሜሪካዊት መሆኗ ነው።

በሌላ ዜና የ 2012 ምርጥ የአለም አሰልጣኝ በመሆን የስፓኝ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ቪንሴንቴ ዴል ቦስክ ተመርጠዋል። በሴት አሰልጣኝነት ደግሞ ፒያ ሰንዳጌ ተመርጣለች። ሲውዲናዊትዋ አሰልጣኝ የኤስ አሜሪካ ቡድን ለንደን በተካሄደው ጨዋታ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ እንዲሆን ትልቅ ሚና ተጫውታለች።

የፊፋ ፕሬዚዳንትነትን ሽልማት በማግኘት የክብር ተሸላሚ የሆኑት ጀርመናዊው ፍራንስ ቤክንባወርም አንድ በኳስ የተመሰለ የወርቅ ኳስ ባለቤት ሆነዋል። የእግር ኳስ አድናቂዎች በሰጡት ድምፅ ደግሞ ቱርካዊው ሚሮስላቭ እስቶኽ ያመቱን ምርጥ ግብ ከመርብ ያገናኘ ተጫዋች በማለት መርጠውታል።

አንድሪያስ እስቴን ዚሞንስ

ልደት አበበ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic