ማዳጋስካር እና የመለያው ምርጫ | አፍሪቃ | DW | 02.11.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ማዳጋስካር እና የመለያው ምርጫ

ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በደሴቲቱ ማዳጋስካር ከዘጠኝ ቀናት በፊት የተካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የመጀመሪያ ውጤቶች እንዳሳዩት፣ በተወዳዳሪነት ከቀረቡት 33 ዕጩዎች መካከል አንዱም ለድል የሚያበቃውን ድምፅ ባለማግኘቱ በሀገሪቱ እአአ የፊታቸን ታህሳስ ፣ 2013 ዓም ሁለተኛው ዙር ምርጫ ይደረጋል።

በመጀመሪው ዙር ምርጫ ዦን ልዊ ሮቢንሶ 28 ከመቶ፣ ኦንሪ ራዦናሪማምፒያኒና ደግሞ 15 ከመቶ የመራጭ ድምፅ በማግኘት በሁለተኛው ዙር ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ላይ እንደገና ይወዳደራሉ። ከአራት ዓመት በፊት ከሥልጣን የተወገዱት እና በደቡብ አፍሪቃ በስደት የሚኖሩት የማርክ ራቫሎማና ደጋፊዎች ድምፃቸውን በርሳቸው የሥልጣን ዘመን የስፖርት እና የጤና ጥበቃ ሚንስትር ለነበሩት ዕጩ ዦን ልዊ ሮቢንሶን ሲሰጡ፣

ከ2009 ዓም ወዲህ ማዳጋስካርን በመምራት ላይ ያሉት የአንድሬ ራዦሊና ደጋፊዎች ደግሞ በራዦሊና መንግሥት ውስጥ ቀድሞ በገንዘብ ሚንስትርነት ላገለገሉት ለኤሪ ራዦናሪማምፒያኒና ሰጥተዋል። የሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ራቫሎማናናም ሆኑ ራዦሊና በምርጫው እንዳይወዳደሩ ከልክለዋል።

የማዳጋስካር ምርጫ በሀገሪቱ አመራር ላይ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የጠበቀውን ለውጥ የሚያስገኝ አይመስልም። ፉክክሩ በታገዱት ራዦሊና እና ራቫሎማናና መካከል ሳይሆን በተከታዮቻቸው መካከል ይሆናል የሚካሄደው። ከ90 ከመቶ የሚበልጠው ሕዝቧ በድህነት በሚኖርባት ማዳጋስካር ውስጥ በተካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ዘመቻ ወቅት የዕጩዎቹ መርሀግብር ትኩረት እንዳላገኘ የሕግ ባለሙያዋ እና የመብት ተሟጋቿ ሳሆንድራ ራበናሪቮ ገልጸዋል።

« ፕሮግራማቸው በሁለቱ ወገኖች መካከል የተካሄደው የሥልጣና ሽኩቻ ጥላ አጥሎበት ነበር። »

ብዙዎች የመለያው ምርጫ ማዳጋስካርን ከአራት ዓመት ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ያላቅቃል በሚል ተስፋ አድርገዋል። ይሁንና፣ ብዙዎቹ የሀገሪቱ ዜጎች ዦን ልዊ ሮቢንሶ በመለያው ምርጫ ቀንቷቸው የሚያሸንፉበት ውጤት ይህን የሕዝቡን ተስፋ ማሟላቱን ብዙዎች እንደሚጠራጠሩት እና በሀገሪቱም እንደገና መፈንቅለ መንግሥት ሊያስነሳ እንደሚችል መስጋታቸውን በመዲናይቱ አንታናናሪቮ የሚገኙት እና ከሁለት ሣምንታት በፊት የዦን ልዊ ሮቢንሶን የምርጫ ዘመቻ የተከታተሉት የጀርመናውያኑ የፍሪድሪኽ ኤበርት ተቋም ባልደረባ ማርኩስ ሽናይደር አስታውቀዋል።

« ሥልጣን ቢይዙ በመጀመሪያ የሚያደርጉት ከአራት ዓመት በፊት ከሥልጣን የተወገዱትን የማርክ ራቫሎማናናን ባልተቤት ላላዎ ራቫሎማናናን ጠቅላይ ሚንስትር አድርገው እንደሚሾሙ፣ ቀጥለውም ራሳቸውን ማርክ ራቫሎማናናን በስደት ከሚኖሩበት ከደቡብ አፍሪቃ ወደሀገራቸው እንደሚመልሱ ነበር የተናገሩት። »

ይህ ዓይነቱ ርምጃ ደሴቲቱን ወደ ሁከት ሊያመራት ይችላል በሚል ነው በወቅቱ ብዙዎች የሰጉት። ይህን የህዝቡን ስጋት የሕግ ባለሙያዋ እና የመብት ተሟጋቿ ሳሆንድራ ራበናሪቮ አረጋግጠዋል።

« ብዙው ሕዝብ ማርክ ራቫሎማናና ወደሀገራቸው ሊመለሱ ይችሉ ይሆናል መባሉን በስጋት እየተከታተለው ነው። ምክንያቱም ቂመኛ መሆናቸው የሚታወቁት ራቫሎማናና የበቀል ርምጃ እንዳይወስዱ ፈርቷል። ከሥልጣን ከመወገዳቸው በፊት የነበራቸው ብዙ ቢልዮን ዶላር ያወጣ የምግብ ማምረቻ ፋብሪካቸው ከተዘረፈ በኋላ በጠቅላላ ወድሞዋል፣ እና ከተመለሱ በመጀመሪያ ይህን ለማስመለስ መሞከራቸው የማይቀር ይሆናል። »

እንደሚታወሰው የቀድሞው ፕሬዚደንት ማርክ ራቫሎማናና ከሥልጣን የተወገዱበትን ሤራ ከሀገሪቱ ፖለቲከኞች መካከል ሁለት ሦስተኛው እና ብዙዎቹ የጦር ኃይሉ አባላት ነበሩ ያቀነባበሩት። በዚህም የተነሳ እነዚህ ወገኖች ዦን ልዊ ሮቢንሶ ካሸነፉ የበቀል ርምጃ እንዳይፈፀምባቸው እና የኤኮኖሚ እና የፖለቲካ ጥቅማቸውን እንዳያጡ መስጋታቸው እንዳልቀረ ማርኩስ ሽናይደር ገልጸዋል።

« ሮቢንሶ ካሸነፉ በማዳጋስካር መፈንቅለ መንግሥት የሚነሳበት ስጋት ሊፈጠር ይችላል። »

በእውነትም፣ ቀደም ባሉት ዓመታት በሀገሪቱ የተፈጠሩ ቀውሶችን የሚያስታውስ ግለሰብ የዚህኑ ስጋት አሳሳቢነት በሚገባ ይረዳዋል። ማዳጋስካር ከምርጫ በኋላ በተደጋጋሚ ቀውስ ውስጥ ወድቃለች። ለምሳሌ እአአ ከ2002 ዓም ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በኋላ በሀገሪቱ ለብዙ ወራት የርስበርስ ጦርነት ዓይነት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ይሁን እንጂ፣ የሀገሪቱን የኤኮኖሚ ሁኔታን ማሻሻልን በተመለከተ የሕግ ባለሙያዋ እና የመብት ተሟጋቿ ሳሆንድራ ራበናሪቮ ለዘብተኛ የምጣኔ ሀብት መርህ ይከተሉ የነበሩት ራቫሎማናና የሚደግፉዋቸው የሮቢንሶ ድል ለሀገሪቱ ጠቃሚ እንደሚሆን ተስፋቸውን ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

« አዎ፣ ሮቢንሶ ሥልጣን ቢይዙ የብዙ ለጋሾችን ቀና አመለካከት የምናገኝ ይመስለኛል። »

ለሀገሪቱ ልማት አስፈላጊ የሆነውን ገንዘብ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ መርህ ድርጅት «አይ ኤም ኤፍ » እና ከዓለም ባንክ ልታገኝ እንደምትችል ነው የሚገምቱት።

Madagaskar Flagge

ፕሬዚደንት ኦንድሬ ራዦሊና የሚደግፉዋቸው ኤሪ ራዦናሪማምፒያኒና ካሸነፉ ደግሞ ራዦሊናን ጠቅላይ ሚንስትር አድርገው እንደሚሾሙ እና ሁኔታዎች አሁን እንዳሉት እንደሚቀጥሉ ይጠበቃል። ራዦናሪማምፒያኒና ከቀናቸው የሚያቋቁሙት መንግሥት በሀገሪቱ መሠረተ ልማት ላይ ፣ማለትም፣ በትምህርት ቤቶች፣ መንገዶች እና ሀኪም ቤቶች ግንባታየሚያሳርፈው ተፅዕኖ ከፍ እንዲል የማድረግ ዓለማ አለው፣ ምንም እንኳን ገንዘቡ ከየት እንደሚመጣ እስካሁን ባይናገሩም፣።

የፕሬዚደንታዊው ምርጫ የመጨረሻ ይፋ ውጤት የፊታችን ዓርብ ይወጣል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ እንደ የሕግ ባለሙያዋ እና የመብት ተሟጋቿ ሳሆንድራ ራበናሪቮ አስተሳሰብ፣ በመለያው ምርጫ የሚያሸንፈው ዕጩ በጉልህ የድምፅ ብልጫ ቢያሸንፍ መልካም ነው፣ ምክንያቱም ይህ የሚሸነፈው ዕጩ ሽንፈቱን የሚቀበልበትን ሁኔታ ከፍ ሊያደርግ ይችላል።

« ሁላችንም የሚያሸንፈው ዕጩ በ60 ወይም በ65 ከመቶ የድምፅ ብልጫ እንዲያሸንፍ ነው የምንፈልገው። »

የፍሪድሪኽ ኤበርት ተቋም ባልደረባ ማርኩስ ሽናይደር ምርጫው እንደታቀደው የሚካሄድበት ድርጊት ራሱ ማዳጋስካርን ካለችበበት ቀውስ የሚያላቅቅ አዎንታዊ ርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።

« በመለያው ምርጫ ማንም አሸነፈ ማን ማዳጋስካር ድል አድርጋለች። »

ሂልከ ፊሸር/አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic