ማዳጋስካርና የምትገኝበት የቀውስ ሁኔታ | ኢትዮጵያ | DW | 02.05.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ማዳጋስካርና የምትገኝበት የቀውስ ሁኔታ

በቀድሞው የማዳጋስካር ፕሬዚደንት ማርክ ራቫሎማናና እና በተቀናቃኛቸው የሀገሪቱ የሽግግር መንግስት ፕሬዚደንት አንድሬይ ራዦሊና መካከል የተፈጠር ውዝግብ አሁንም ገና መፍትሄ አልተገኘለትም።

default

ከአንድ ወር ገደማ በፊት ስልጣናቸውን የለቀቁት የቀድሞው የማዳጋስካር ፕሬዚደንት ማርክ ራቫሎማናና ህጋዊው የሀገሪቱ መሪ አሁንም እርሳቸው መሆናቸውን በድጋሚ በማስታወቅ ተቀናቃኛቸው አንድሬይ ራዦሊና ከሚመሩት የሽግግሩ መንግስት ጎን ለጎን የሚሰራ የራሳቸውን መንግስት ከጥቂት ቀናት በፊት አቋቁመዋል፤ ማናንዳፋይ ራኮቲኒናንም ጠቅላይ ሚንስትር አድርገው ሾመዋል። እኒሁ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ራኮቲኒሪና ግን ከጥቂት ጊዜ በፊት በራዦሊና የሽግግር መንግስት ጸጥታ ኃይላት የመታሰር ዕጣ ገጥሞአቸዋል። ጭምብል ያደረጉ ወደ ሀያ የሚጠጉ የጸጥታ ኃይሉ አባላት ራኮቲኒሪና የመንግስታቸውን መንበር ካደረጉበት በመዲናይቱ ከሚገኘው የካርልተን ሆቴል ካሰሩዋቸው በኋላ ወዴት እንደወሱዋቸው እስካሁን በውል አልታወቀም። ራኮቲኒሪና ከመታሰራቸው አንድ ቀን ቀደም ሲል ባለፈው ረቡዕ የመንግስታቸውን ከፊል የካቢኔ አባላትን ስም ማውጣታቸው የሚታወስ ነው። የአፍሪቃ ህብረት የማዳጋስካርን ቀውስ ለማስወገድ ጥረት በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት ራኮቲኒሪና መታሰራቸው በሽግግሩ መንግስት መሪ አንድሬይ ራዦሊና እና በቀድሞው ፕሬዚደንት ማርክ ራቫሎማናና ደጋፊዎችመካከል የተፈጠረውን ውዝግብ ይበልጡን እንዲባባስ አድርጎታል።

ከአራት ወራት ወዲህ በደሴቲቱ ማዳጋስካር የሚታየው ቀውስ አሁንም ገና አልበረደም። የቀድሞው የመዲናይቱ አንታናናሪቮ ከንቲባ አንድሬይ ራዦሊና የሚመሩት ከአንድ ወር ገደማ በፊት የተቋቋመው የማዳጋስካር የሽግግግር መንግስት ያደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ ቢከለክልም፡ የቀድሞው ፕሬዚደንት ማርክ ራቯሎማናና ታማኝ ደጋፊዎች ይህንኑ ትዕዛዝ በመጣስ፡ ራቫሎማናና ስልጣናቸውን መልሰው እንዲረከቡ ለመጠየቅ ሰሞኑን አደባባይ ወጥተዋል። በዚሁ ጊዜም ከጸጥታ ኃይላት ጋር ተጋጭተው ሁለት የራቫሎማናና ደጋፊዎች ተገድለው በርካቶችም ቆስለዋል። አምባገነን እያሉ ከሚወቅሱዋቸው ከአንድሬይ ራዦሊና ጋር ስልጣን ለመጋራት ቀደም ሲል ፈቃደኝነታቸውን ገልጸው የነበሩት በስደት በደቡብ አፍሪቃ የሚገኙት ማርክ ራቫሎማናና የስልጣን መጋራቱን ሀሳብ አሁን ውድቅ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል። ይህ የአቋም ለውጥ በደሴቲቱ ለሚታየው ቀውስ ሰላማዊ መፍትሄ ማፈላለግ የያዘውን የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ጥረት አዳጋች እንደሚያደርገው ተንታኞች ገምተዋል።

የሽግግሩ መንግስት ፕሬዚደንት አንድሬይ ራዦሊና ደጋፊዎች የነበሩት የተቃውሞው ወገን የቀድሞው ፕሬዚደንት ራቯሎማናና ስልጣናቸውን እንዲለቁ በመጠየቅ አደባባይ ይወጡ በነበረበት ጊዜ ከቀድሞው መንግስት ጸጥታ ኃይላት ጋር በተፈጠረ ግጭት አንድ መቶ ሰላሳ አምስት ሰዎች መገደላቸው የሚታወስ ነው። በዓመት ለሀገሪቱ ሶስት መቶ ዘጠና ሚልዮን ዶላር ገቢ የሚያስገኘው የቱሪዝሙ ዘርፍም፡ በለንደን የሚገኘው የምጣኔ ሀብት ሂደትን የሚያጠናው የ «ኤኮኖሚክስ ኢንተሊጀንስ ዩኒት» ተንታኝ ኤድዋርድ ጆርጅ እንደሚሉት፡ ከጥር እስከ መጋቢት ወር በቀጠለው ግጭት ትልቅ ጉዳይ ነበር የደረሰበት።

« ቀውሱ በቱሪዝሙ ዘርፍ ላይ መጥፎ ተጽዕኖ አሳርፎዋል። እንዲያውም ማዳጋስካርን ሊጎበኙ ካቀዱት መካከል ዘጠና አምስት ከመቶ ያህሉ ጉዞዋቸውን ሰርዘዋል። የቱሪዝሙ ዘርፍ ለማዳጋስካር መንግስት ዋነኟው የገቢ ምንጭ ነው። »

የስልጣን መጋራቱ ሀሳብ ማዳጋስካር በወቅቱ ከምትገኝበት አሳሳቢ ውዝግብ ልትላቀቅ የምትችልበት ብችኛው አማራጭ መሆኑንም ተንታኙ ኤድዋርድ ጆርጅ ይገምታሉ። ስልጣናቸውን ባረፈባቸው ግፊት የለቀቁትና በቅርቡም በስደት ከሚገኙባት ደቡብ አፍሪቃ ወደ ማዳጋስካር እንደሚመለሱ የገለጹት የቀድሞው ፕሬዚደንት ራቫሎማናና ህጋዊው መሪ መሆናቸውን በማስታወቅ ደሴቲቱን ከምትገኝበት ቀውስ ለማላቀቅ ከሁሉም የሀገሪቱ ህጋዊ ፓርቲዎች ጋር ባንድነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ይሁንና፡፡የማርክ ራቫሎማናና ወደ ማዳጋስካር መመለስ ውዝግቡን ይበልጡን እንዳያባብሰው ነው ያሰጋው። ራቫሎማናና ከአካባቢው መንግስታትም ድጋፍ ለማሰባሰብ በወቅቱ ከፍተኟ ጥረት ጀምረዋል። የደቡባዊ አፍሪቃ መንግስታት የምት ትብብር ድርጅት፡ በምህጻሩ የሳዴክ መሪዎች የሽግግሩ መንግስት መሪ አንድሬይ ራዦሊና ስልጣኑን ለህጋዊው ፕሬዚደንት ማርክ ራቯሎማናና እንዲያስረክቡ ዲፕሎማቲካው ጥረት ጀምረዋል። ማዳጋስካርን ከአንድ ወር በፊት ከአባልነት ያገዱት ሳዴክ፡ የአፍሪቃ ህብረት፡ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሀገሮች ህብረትና ፈረንሳይ፡ ሁሉም ለአንድሬይ ራዦሊና መንግስት እስካሁን ትውቂያ አልሰጡም። እንደሚታወሰው፡ የአፍሪቃ ህብረት የሰላምና ጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጄፍሪ ሙጉሙያ በማዳጋስካር የተደረገውን የስልጣን ለውጥ ህገ መንግስቱን የተጻረረ ድርጊት ብለውታል።

« ምክር ቤቱ በማዳጋስካር የተከሰተውን የስልጣን ለውጥ ኢ ህገመንግስታዊ ብሎታል። እናም ምክር ቤቱ የአፍሪቃ ህብረትን ጽሁፍ መሰረት በማድረግ ማዳጋስካርን ከማንኛውም የህብረቱ እንቅሳሴዎች ተሳትፎ ለማገድ ውኖዋል። ባወጣነው መግለጫ ላይ በአጽንዖት እንዳስታወቅነው በሀገሪቱ ህገ መንግስታዊው ሁኔታ ባፋጣኝ ካልተመለሰ ሌሎች ርምጃዎችን እንወስዳለን፤ በማዳጋስካር ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ የምንጥልበትን ርምጃ ምናልባት እናሰላስላለን። »

የማዳስካር የሽግግር መንግስት መሪ አንድሬይ ራዦሊና ግን ስልጣናቸውን እንዲያስረክቡ ከያቅጣጫው የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ፡ በሀገሪቱ እአአ በ 2010 ዓም ምርጫ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

DW/AFPE/AA/MM

Audios and videos on the topic