ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ከሚሼል ጆቶዲያ በኋላ | አፍሪቃ | DW | 15.01.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ከሚሼል ጆቶዲያ በኋላ

ውዝግብ ያዳቀቃት የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ የሽግግር ምክር ቤት እንደራሴዎች ባለፈው ሳምንት የወረዱትን የቀድሞ ፕሬዚደንት ሚሼል ጆቶዲያን የሚተካ ለመመረጥ ጉባዔ ጀመሩ።

እንደራሴዎቹ አዲሱ ፕሬዚደንት ካለፉት አምስት ወራት ወዲህ የቀጠለውን እና አንድ አምስተኛውን የሀገሪቱን ሕዝብ ያፈናቀለውን ደም አፋሳሽ ግጭት በማብቃት ዕርቀ ሰላም ማውረድ የሚችል መሆን እንዳለበት ገልጸዋል። አርያም ተክሌ

በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ጉባዔ የጀመሩት 135 የሽግግሩ ምክር ቤት እንደራሴዎች የቀድሞውን ፕሬዚደንት ሚሼል ጆቶዲያን የሚተካውን ግለሰብ ቢፈጥን በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ያስታውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል። የምርጫው ሂደት በትክክለኛ መንገድ መከናወኑን ከሚያስተባብሩት እንደራሴዎች አንዱ የሆኑት ዠርቬ ላኮሶ ሀገሪቷን ከምትገኝበት ምስቅልቅል ሁኔታ የሚያላቅቅ እና የሕዝቡን ጥቅም የሚያስቀድም መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

«እኛ የሽግግሩ ምክር ቤት አባላት በተቻለን መጠን ባለን ኃላፊነት በመጠቀም የሚመረጠው አዲሱ ፕሬዚደንት የማዕከላይቱን አፍሪቃ ሬፓብሊክ ጥቅም የሚያስጠብቅ እንዲሆን እናረጋግጣለን። »

በመገናኛ ብዙኃን ዘገባ መሠረት፣ ለፕሬዚደንትነቱ ሥልጣን ወደ አስር የሚጠጉ ተፎካካሪዎች የቀረቡ ሲሆን፣ ከነዚሁ አንዱ የሽግግሩን ምክር ቤት ሊቀ መንበርነት የያዙትእና የጆቶዲያ መነግሥት አባል የነበሩት አሌግዞንድር ፈርዲnኖን ንጌንቴንዴ ይገኙባቸዋል። የመዲናይቱ ቦንግዊ ነዋሪዎች ስለአዲሱ ፕሬዚደንት ቀጣዩን ብለዋል።

« አዲሱ ፕሬዚደንት የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክን ማረጋጋት የሚችል አንድ የጦር ኃይል አባል፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ ደግሞ ሲቭል ባለሙያ መሆን አለበት። የሲቭሉ ማህበረሰብ እና ሀይማኖታዊ ቡድኖችም የራሳቸውን ዕጩ ማቅረብ ቢችሉ መልካም ሊሆን ይችላል።»

« አንድ የሀይማኖት ሰው የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክን አመራር መያዝ አለበት፣ ፖለቲከኞችን ካሁን ቀደም አይተናቸዋል። በአመራራቸው ቅር አሰኝተውናል። »

ይህ በዚህ እንዳለ፣ የቀድሞ የሴሌካ ዓማፅያንን መቆጣጠር እንዳልቻሉ ያመኑት የቀድሞው ፕሬዚደንት ሚሼል ጆቶዲያ ከጎረቤት ሀገራትና ከፈረንሳይ ባረፈባቸው ግፊት ሥልጣናቸውን ለቀው ወደ ቤኒን ከተሰደዱ እና አሌግዞንድር ፈርዲኖን ንጌንቴንዴ የሽግግሩ መንግሥት ፕሬዚደንት ከሆኑ በኋላ አሁን ሀገሪቱ በመረጋጋቱ ሂደት ላይ ብትሆንም፣ ሁኔታዎች አሁንም ተለዋዋጭ እና የማያስተማምን መሆኑን ታዛቢዎች ገልጸዋል።

የሽግግሩ መንግሥት ፕሬዚደንት አሌግዞንድር ፈርዲኖን ንጌንቴንዴ ምስቅልቅሉን ሁኔታ ለማብቃት ቃል ቢገቡም እና አንዳንዶቹ ተፈናቃዮቹ በአስከፊ ሁኔታ ላይ ወደሚገኙበት ቦታ በመሄድ ወደመኖሪያቸው እንዲመለሱ ለማግባባት ቢሞክሩም፣ እንዲሁም፣ የቀድሞ የሴሌካ ዓማፅያንን ጥቃት በመፍራት በመላ ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ለብዙ ሳምንታት ከስራ ገበታቸው ርቀው የቆዩ ወታደሮች እና ፖሊሶች አሁን ወደ ስራ ገበታቸው ቢመለሱም፣ ብዙዎች፣ አዲስ ግድያ ሊፈጠር ይችላል በሚል ስጋት ወደመኖሪያ ቀያቸው ለመመለስ አመንትተዋል።

የሴሌካ ጥምረት ዓማፅያን መጋቢት 2013 ዓም ባካሄዱት መፈንቅለ መንግሥት የቀድሞው ፕሬዚደንት ፍራንስዋ ቦዚዜ ካስወገዱ እና ጆቶዲያ ሥልጣን ከያዙ በኋላ በተከተሉት አምስት ወራት በቀድሞ በብዛት ሙሥሊሞቹ የሴሌካ ዓማፅያን እና ራሳቸውን ከሴሌካ ጥቃት ለመከላከል በተደራጁት የክርስትያን ሚሊሺያዎች መካከል ቀጥሎ የነበረው ደም አፋሳሽ ግጭትበግጭቱ ከ1000 የሚበልጥ ሰው ሲገደል፣ ከአንድ ሚልዮን የሚበልጡ ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። ለነዚሁ እጅግ በተጨናነቁት እና አስፈላጊው የመፀዳጃ አገልግሎት በሌለባቸው መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ለሚገኙት ተፈናቃዮች ባስቸኳይ ርዳታ ካልቀረበ፣ ለተላለፊ በሽታ ሊጋለጡ እንደሚችሉ አንድ የተመድ የአስቸኳይ ጊዜ ርዳታ አስተባባሪ መሥሪያ ቤት ባለሥልጣን አስጠንቅቀዋል።

አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic