ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ እና የሰላም አስከባሪው ጓድ | አፍሪቃ | DW | 06.03.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ እና የሰላም አስከባሪው ጓድ

በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ውስጥ ራሱን ፀረ ባላካ(ቆንጨራ) ብሎ የሚጠራ የክርስትያኖች ቡድን አባላት በሙሥሊሞች፣ የቀድሞ የሴሌካ ዓማፅያን ደግሞ በክርስትያኖች ላይ በሚሰነዝሩት ጥቃት ዜጎች በየቀኑ ይገደላሉ።

ዓለም አቀፉ የቀይ መሥቀል በመዲናይቱ ባንጊ የብዙ ሰዎች፣ አልፎ አልፎም በቆንጨራ የተቆራረጡ ወይም ከነነፍሳቸው የተቃጠሉ አስከሬን ይሰበስባል። በመዲናይቱ ባንጊ የሙሥሊሞቹ ሠፈሮች ክርስትያኖች ከሚኖሩባቸው ሠፈሮች ብዙም አይርቁም። ይህም ፀረ ባላካ ሚሊሺያዎች እና የቀድሞ የሴሌካ ዓማፅያን አንዱ በሌላው እምነት ተከታይ ላይ የሚሰነዝሩት ጥቃት እየተባባሰ የሄደበትን ድርጊት ቀላል አድርጎታል። ያም ቢሆን ግን ይህንኑ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን ጥቃት ለማከላከል በክርስትያኖቹ እና በሙሥሊሞቹ ሠፈሮች መካከል የተሠማሩት የአፍሪቃ ህብረት ፀጥታ አስጠባቂ ወታደሮች ቁጥር እጅግ ንዑስ ነው። ለምሳሌ፣ በበርካታ የጦር ሠፈሮች ውስጥ አሁንም ሙሥሊሞቹ የሴሌካ ዓማፅያን የሚገኙ ሲሆን፣ በሰሜን ባንጊ በሚገኝ አንድ የጦር ሠፈር ደጃፍ ዓማፅያኑ እንዳይወጡ ለመከላከል አምሥት የርዋንዳ ወታደሮች ጥበቃ ቆመው ተመልክተናል።

እርግጥ፣ ከጎረቤት አፍሪቃውያት ሀገራት የተውጣጡ ወደ 6,000 የሚጠጉ ወታደሮች በአፍሪቃ ህብረት ተልዕኮ ሬፓብሊክ ስር፣ ወደ 2,000 የሚጠጉ የፈረንሳይ ወታደሮች በተመድ ውሳኔ በማዕከላይ አፍሪቃ ተሠማርተዋል። የአውሮጳ ህብረትም ተጨማሪ 1,000 ወታደሮች እንደሚልክ አስታውቋል። ይሁንና፣ የባንጊ ነዋሪዎች አሁንም ለደህንነታቸው ዋስትና አልተሰማቸውም። ሙሥሊሞቹ ለዓርቡ ፀሎት ወደ መሥጊድ መሄድ አይደፍሩም። በዚሁ ዕለት በዚሁ ለአደጋ በተጋለጠው ሠፈር አንድም የጦር ቡድን ጥበቃ አያደርግም በሚል አንድ ሙሥሊም የሠፈሩ ነዋሪ ወቅሰው፣ ፈረንሳውያኑ ክርስትያናውያኑን ሚሊሺያዎችን ይደግፋሉ በሚል ከሰዋል።

« እዚህ ተሸብረን ነው የምንኖረው። ፀረ ባላካዎች በየቀኑ ያጠቁናል። እኛ ፀጥታ እንዲጠበቅ ነው የምንፈልገው። ፈረንሳውያኑ ወታደሮች ከፀረ ባላካ ጥቃት እንደሚከላከሉን ነበር የተነገረን፣ በአንፃሩ፣ የኛን ደህንነት በሀገሪቱ የተሠማራውበምሕፃሩ ሚስካ የተባለው ሰላም አስከባሪ ጓድ እንደሚጠብቅልን ነው የሚሰማን። የቡሩንዲን ወታደሮች የሚያደርጉትን ሁሉ እናደንቃለን። ፈረንሳውያኑ ናቸው ፀረ ባላካዎችን የሚደግፉዋቸው። »

የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ነዋሪዎች የውጭ ጦር ኃይላትን ያን ያህል አያምኑዋቸውም። ለምሳሌ፣ ሙሥሊሞቹ ከካሜሩን እና ከኮንጎ፣ እንዲሁም ፈረንሳውያኑን ወታደሮች የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር እና ፀረ ባላካዎችን ለመደገፍ የተሠማሩ ናቸው በሚል ይወቅሳሉ።

በነዚህ አንፃር በተለይ በሙሥሊሞቹ ሠፈሮች የተሠማሩትን ከቡሩንዲ እና ከርዋንዳ የሄዱትን ወታደሮች ያምናሉ። የካሜሩን ጦር በባንግዊ በብዛት ከሥልጣን የተወገዱት የቀድሞው ፕሬዚደንት ፍራንስዋ ቦዚዜ ደጋፊዎች የሚኖሩበትን የቦራፕን ሠፈር ይጠብቃል። አንዳንድ ሙሥሊሞች እንደሚሉት፣ ቦዚዜ በስደት ከሚኖሩባት ካሜሩን የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ክርስትያን ወጣቶችን ለጥቃት ይቀሰቅሳሉ። በአንፃራቸው ክርስትያናውያኑ ከቻድ የተውጣጡት የሚስካ ጦር አባላት የቀድሞ የሴሌካ ዓማፅያንን ይደግፋሉ በሚል ይወቅሳሉ። ይህ ባጠቃላይ የሚያሳየው፣ ይላሉ የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ነዋሪዎች፣ ዓለም አቀፍ ሰላም አስጠባቂው ቡድን ገለልተኛ መሆን አለበት የሚለው ዓላማ ግቡን አለመምታቱ ነው። በዚህም የተነሳ የተመድ ወደ ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ይላክ ለሚለው ሰላም አስጠባቂ ጓድ ጦር የሚያዋጡ ሀገራት ከዚችው ሀገር ውዝግብ በቀጥታ ተጠቃሚ ናቸው የማይባሉ መሆን አለባቸው። የተመድ ዋና ፀሐፊ ፓን ኪ ሙን ለፀጥታ ጥበቃ ምክር ባቀረቡት ዘገባ በጠቅላላ 12,000 ሰላም አስከባሪ ወታደሮች እንዲላኩ ሀሳብ አቅርበዋል። ይህንኑ የዋና ፀሐፊውን ጥያቄ የሀገሪቱ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚደንት ሌያ ኮያሱም ዱማታ አሞግሰዋል።

«ዋና ፀሐፊው ተጨማሪ ሰላም አስከባሪዎች እንዲቀርቡ ይህን ጥያቄ በማሰማታቸው ትልቅ እፎይታ ተሰምቶናል። ምክንያቱም በሀገራችን የጦር ኃይል የለም ማለት ይቻላል። ሰላም አስከባሪዎቹ ወታደሮች ግን በሽግግር ላይ የምትገኘው ሀገራችን በቅርቡ ምርጫ ማካሄድ እንደምትችል ለሕዝቡ ሊያረጋግጡ ይችላሉ። የተመድ ዋና ፀሐፊ የፕሬዚደንታችንን ተማፅኖ መስማታቸው ለኛ የሽግግሩ ምክር ቤት አባላት ትልቅ እፎይታ ነው። ለማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ለሰጡት ሕዝብ ትኩረት እና ላሳዩት ሰብዓዊነት እናመሠግናቸዋለን። »

ይሁንና፣ ይኸው ሰላም አስከባሪ ጦር ፈጠነ ቢባል ከመስከረም ወር በፊት ሊሠማራ እንደማይችል ፓን ኪ ሙን በማስታወቅ፣ እስከዚያ ድረስ ሌላ መሸጋገሪያ መፍትሔ እንዲፈለግ አሳስበዋል።

ዚሞነ ሽሊንድቫይን/አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic