1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን የጅምላ እስር ቀጥሏል

ዓርብ፣ ኅዳር 14 2016

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን መምህራን በጅምላ እየታሠሩ ነው ሲሉ የታሳሪ ቤተሰቦች ገለጹ ። የአካባቢው ባለሥልጣናት እሥሩን እየፈጸሙ የሚገኙት ከደሞዝ ከፍያ ጋር በተያዘ ሁከትና ግርግር ለማስነሳት ሞክረዋል በሚል የጠረጠሯቸውን መሁንን ተናግረዋል ።

https://p.dw.com/p/4ZOmr
በሃድያ ዞን፤ ሆሳህና
በሃድያ ዞን የምሥራቅ ባድዋቾ ፣ የምዕራብ ባድዋቾ እና የዱና ወረዳ የመንግሥት ሠራተኞች “ የሦስት ወራት የደሞዝ ከፍያ አልተፈጸመልንም “ በሚል ባለፈው የጥቅምት ወር መግቢያም ሥራ ማቆም አድማ አድርገው ነበር ። ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ሃድያ ዞን ምሥራቅ ባድዋቾ ወረዳ ተቃውሞና እስሩ ተደጋግሟል

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን መምህራን በጅምላ እየታሠሩ ነውሲሉ የታሳሪ ቤተሰቦች ገለጹ ። የአካባቢው ባለሥልጣናት እሥሩን እየፈጸሙ የሚገኙት ከደሞዝ ከፍያ ጋር በተያዘ ሁከትና ግርግር ለማስነሳት ሞክረዋል በሚል የጠረጠሯቸውን መሁንን ተናግረዋል ። 

ተቃውሞ እና እስር የተደጋገባት ባድዋቾ ወረዳ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን ምሥራቅ ባድዋቾ ወረዳ መምህራን በጅምላ የማሰሩ ድርጊት እየተፈጸመ የሚገኘው የመምህራን የደሞዝ ከፍያ እንዲፈጸም የሚጠይቁ ተማሪዎች ትናንት ጎዳና በመውጣት ሠልፍ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው ተብሏል ፡፡ የአካባቢው የፀጥታ ኃላፊዎች በበኩላቸው መምህራኑ የታሠሩት ህጻናትን በመቀስቀስ ያልተፈቀደ ሠልፍ ለማስደረግ በመሞከራቸው ነው ይላሉ ፡፡ መምህራኑ ከባለፈው ነሐሴ ወር ጀምሮ ደሞዝ ስላልተከፈላቸው በሙሉ እና በከፊል ሥራ ማቆማቸው ይታወቃል ።

የመምህራን እሥር በሃድያ ዞን 

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን ምሥራቅ ባድዋቾ ወረዳ መምህራን በጅምላ እየታሠሩ ነው ሲሉ የታሳሪ ቤተሰቦች ገለጹ ፡፡የመምህራኑ እሥር ተፈጽሟል የተባለው በሃድያ ዞን ምሥራቅ ባድዋቾ ወረዳ ሾኔ ከተማ ውስጥ ነው ፡፡ የዐይን እማኖች እንዳሉት በከተማው ፖሊስ አባላት የታሠሩት መምህራን ቁጥራቸው በመቶዎች ይገመታል ፡፡ እሥሩ የተካሄደው የመምህራን የደሞዝ ከፍያ እንዲፈጸም የሚጠይቁ ተማሪዎች  ትናንት  ጎዳና በመውጣት ሠልፍ ማድረጋቸውን ተከትሎ መሆኑን የአይን አማኞች ተናግረዋል ፡፡

በሾኔ ከተማ የታሳሪ ቤተሰብ አባል ነኝ ያሉ አንድ ነዋሪ የፀጥታ አባላቱ የተማሪዎቹን ሠልፍ ተከትሎ ባደረጉት አሰሳ ታናሽ ወንድማቸውንና የአጎታቸው ልጅ መታሠራቸውን ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል ፡፡ ወንድማቸውና የአጎታቸው ልጅ የታሠሩት ትናንት ሌሊት አሥር ሰዓት ላይ መሆኑን የጠቀሱት ነዋሪው” ቤቱን ከበው ካደሩ በኋላ ጠዋት ላይ ነው ይዘዋቸው የሄዱት ፡፡ እስከአሁን ድረስ የደረሳቸው የክስ ቻርጅ የለም ፡፡ ያለምንም ጥያቄ በፖሊስ ጣቢያ ታስረው ይገኛሉ “ ብለዋል ፡፡

የተማሪዎቹ ሠልፍ

በሃድያ ዞን ምሥራቅ ባድዋቾ ፣ ምዕራብ ባድዋቾ እና ሶሮ ወረዳ የሚገኙ መምህራንና ሀኪሞች ከባለፈው ነሀሴ ወር ጀምሮ በሙሉ እና በከፊል ሥራ እንዳቆሙ ይገኛሉ ፡፡ የሥራ ማቆማቸው ምክንያቱ ከባለፈው የነሀሴ ወር ጀምሮ ደሞዛችን አልተከፈለንም የሚል ነው። በዚህም የተነሳ በወረዳዎቹ የትምህርት ሥራ አለመጀመሩን ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ ፡፡ ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው ሁለት የከተማይቱ ነዋሪዎች የመምህራን ደሞዝ እንዲከፈል የሚጠይቁ ወጣቶች በሃድያ ዞን የምሥራቅ ባድዋቾ  ወረዳ ሾኔ ከተማ የጎዳና ላይ ሠልፍ ማድረጋቸውን በመጥቀስ “ ወጣቶቹ የከተማ አስተዳደሩን ከንቲባ በሥም እየጠሩ ጸያፍ ስድቦችን ሲሳደቡ ነበር ፡፡ እንዲሁም “ የመምህራን ደሞዝ ይከፍል “ በማለት  በጩኸት ሲናገሩ ነበር “ ብለዋል ፡፡

በደቡብ ክልል፤ ሾኔ ከተማ
በደቡብ ክልል ሃድያ ዞን የምሥራቅ ባድዋቾ ወረዳ እና ሾኔ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ መንግሥት ሠራተኞች ለሦስት ወራት ያልተከፈለን ደሞዝ እንዲከፈለን በመጠየቃችን ለእሥርና ለእንግልት እየተዳረግን ነው ሲሉ ከዚህ ቀደምም አቤት ብለው ነበር ።ምስል Shone city communication office

ፖሊስ ምን አለ ? 

የትናንቱ የወጣቶቹ ሠልፍ ያልተፈቀደ ፣ ሕገ ወጥ እና ከጀርባ የጥቂት መምህራን እጅ ያለበት ነው ሲል የሾኔ ከተማ አስተዳደር ዐስታውቋል፡፡ ዶቼ ቬለ በመምህራኑ እሥር ዙሪያ ያነጋገራቸው የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ አዛዣ ታረቀኝ ሶራቶ “ መምህራኑ የታሠሩት ህጻናትን በመቀስቀስ ያልተፈቀደ ሠልፍ ለማስደረግ በመሞከራቸው ነው “ ብለዋል ፡፡  በሕገ ወጥ ሠልፉ ተሽከርካሪዎችን በድንጋይ መስበርን ጨምሮ በተለያዩ የልማት ድርጅቶች ላይ ጉዳት ለማድረስ ሙከራ ተደርጓል ያሉት የፖሊስ አዛዡ የታሠሩ መምህራንን  ቁጥር ከመጥቀስ ግን ተቆጥበዋል ፡፡

የሾኔ ከተማ መምህራን ማኅበር ግን የፖሊስ አዛዡን ውንጀላ እንደማይቀበለው እየገለጸ ይገኛል ፡፡ የወጣቶቹ ሰልፍ ከመምህራኑ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም የሚሉት የማኅበሩ ሊቀ መንበር ከበደ ካባ «በእኛ በኩል መምህራኑ የታሠሩበትን ትክክለኛ ምክንያት ለማወቅ ከሚመለከተው የፀጥታ አካል ጋር እየተነጋገርን እንገኛለን ፡፡ ከዚህ ውጭ የወጣቶቹን ሠልፉ መርተዋል የተባለው መሠረት የሌለው ውንጀላ ነው » ብለዋል ፡፡የቀጠለው የሃድያ ዞን መምህራን አቤቱታ

ትምህርት የማስጀመር ጥረት

ዶቼ ቬለ በመምህራኑ እሥር ዙሪያ የሃድያ ዞን እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የትምህርት ቢሮና የፀጥታ ኃላፊዎችን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም ፡፡ የምሥራቅ ባድዋቾ መምህራን ማኅበር ግን ታሠሩ የተባሉ መምህራንን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለ እንደሚገኝ ዐስታውቋል ፡፡ ማኅበሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ከመምህራኑ ውዝፍ የደሞዝ ክፍያ ውስጥ አብዛኛው እንዲፈጸም መደረጉን የጠቀሱት የማኅበሩ ሊቀመንበር መንግሥቱ ጎዶሬ “ የነሀሴ እና ምስከረም ወር ደሞዝ የተከፈለ ሲሆን ቀሪውን የጥቅምት ወር ደሞዝን ለማስከፈል ከወረዳ እና ከዞን ትምህርት መምሪያዎች ጋር በመነጋገር ጥረታችንን ቀጥለናል ፡፡ አሁን ላይ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ትምህርት ለማስጀመር የሚያስችል ውይይት እየተደረገ ይገኛል “ ብለዋል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር