ማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፓብሊክና የቻድ ጣልቃ ገብነት | አፍሪቃ | DW | 13.02.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፓብሊክና የቻድ ጣልቃ ገብነት

የማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፓብሊክ ሰሜናዊ ጎረቤት ፣ ቻድ፣ ከአካባቢው ሃገራት ፤ በጦር ኃይል ይበልጥ የደረጀች መሆኗ ይነገርላታል። በፕሬዚዳንት ኢድሪስ ደቢ የምትራው ቻድ፤ የማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፓብሊክን ውዝግብ ለመፍታት ፤ ራሷ በምትፈለገው መልክ ውሳኔ

የምታስተላልፍ ሀገርም ሆናለች። ይሁንና ውዝግቡ እስካሁን ከመባባስ ሊገታ አልቻለም። አገሪቱን የጎበኙት የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን መሪ እንዳሉት፤ ህዝብን በጭካኔ ተግባር ፤ ማፈናቀሉ እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ነው። -

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ኀላፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ ፤ በጎሣና ሃይማኖት ልዩነት በማክረር ህዝብን ከቀየው የማፈናቀሉ እርምጃ ፤ አስደንጋጭ ፤ ዘግናኝ የሆነ የጭካኔ ተግባር የሚታይበት ሆኗል ነው ያሉት። አሁን የተቋቋመው አዲስ መንግሥትም ዜጎቹን ከጥቃት ለመከላከል የሚያስችል የተግባር ብቃት አላሳየም። አዲሷ የማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፓብሊክ የሽግግር ፕሬዚዳንት ካትሪን ሳምባ ፓንዛ፤ በበኩላቸው፤ «ፀረ ባላካ » በተሰኙት በአመዛኙ የክርስቲያኖች ሚሊሺያ ጦር ኃይል ላይ ዝተዋል። ይህ ቡድን ሙስሊም ዜጎች ቀየአቸውን እየለቀቁ እንዲሰደዱ አድርጓል። የመዲናይቱ የቦንጊ (ባንጊ)ሊቀ ጳጳስ ዲዮዶን እንዛፓሌይንጋ የሚሊሺያ ጦሩን ድርጊት በራዲዮ አውግዘዋል። የኃይል እርምጃ ከሃይማኖት ጋር አይጣጣምም፤ ወንድምህን እየገደልህ፤ ንብረቱን እያወደምህ ክርስቲያን ማለት በፍጹም የማይሆን ነገር ነው። ካቶሊካዊው ሊቀ ጳጳስ፣ «ኢማሞች፤ ሰባክያነ ወንጌልና እኔ ራሴ፤ አንድ ቋንቋ ነው የምንናገረው። ወጣቶች፤ ዜጎችን ከቀየአቸው እንዲያፈናቅሉ የሚቀሰቅሱ፣ የሚያሠማሩ ወገኖች፤ በአገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ በኅላፊነት ከመጠየቅ አያመልጡም» ሲሉ ተናግረዋል።

ለሰብአዊ መብት የሚታገለው ዋና ጽ/ቤቱ በለንደን የሚገኘው አምነስቲ ኢንተርናሽናልም በክርስቲያኖቹ ሚሊሺያ ጦር ቢያንስ 200 ሙስሊሞች መገደላቸውን እንደመዘገባ አስታውቋል። 4,6 ሚሊዮን ኑዋሪዎች ባሏት ማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፓብሊክ፤ ተባባሶ በቀጠለው ውዝግብ ሳቢያ አንድ ሚሊዮን ህዝብ ከቀየው ተፈናቅሏል።

አምና በመጋቢት በአመዛኙ በሙስሊሞች በተመሠረተው የሴሌካ አማጽያን ቡድን በመፈንቅለ መንግሥት በቦንጊ ሥልጣን ከጨበጠ ወዲህ አገሪቱ ስትታመስ ነው የከረመች።

ቀደም ባለው ጊዜም ሆነ አሁን በማዕከላዊት አፍሪቃ ጉዳይ ፣ ቻድ እጇን ያላስገባችበት ሁኔታ የለም። በቅርቡ የማዕከላዊት አፍሪቃን ውዝግብ ለመፍታት ሲመከር፤ሌላ ፕሬዚዳንት ያስፈልጋል ብለው የሽግግር ወቅት ፕሬዚዳንት የነበሩትን ሚሸል ጆቶዲያን ሥልጣን እንዲለቁ ያስገደዱ የቻዱ መሪ ናቸው። ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ደቢ፤ ማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፓብሊክን እንደ ጓሮአቸው ነው የሚመለከቷት። በፍርይቡርግ ፤ ጀርመን ፣ በአርኖልድ -በርግሽትረሰር ተቋም የማዕከላዊት አፍሪቃ ጉዳይ ተመራማሪ ሄልጋ ዲኮቭ እንዲህ ይላሉ።

«ደቢ ምንጊዜም ማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፓብሊክን እንደ ጓሮአቸው ነው የሚቆጥሯት።

የቀድሞው የማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፓብሊክ መሪ አንዥ ፌሊክስ ፓታሴ፣ ከዚያም በኋላ ቦዚዜ ሲተኩ፣ ቦንጊ ላይ አምባገነን መሪ እን,ነበሩ ቢታወቅምበቻዱ ፕሬዚዳንት ደቢ ድጋፍም ሆነ አበረታችነት ነበረ ሥልጣን ላይ ለመቆየት የቻሉት።»

ቻድ በአሁኑም ጊዜ በማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፓብሊክ ጦሯን እንዳሠማራች ትገኛለች። ከአፍሪቃው ኅብረት ሰላም አስከባሪ 5,500 ጦር ፣ አብዛኞቹ፣ የቻድ ወታደሮች ናቸው።

ከቻድ አምባገነነ መሪ እዲሪስ ደቢ ጋር ተባብራ የምትሠራው ፈረንሳይ ማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፓብሊክ ውስጥ 1,600 ያህል ወታደሮችን አሠማርታለች።

ህዝቡ የሆነው ሆኖ ፣ የውጭ ኃይሎችን በጥርጣሬ ዐይን ነው የሚመለከተው። ከሞላ ጎደል አንድ ሺ ኪሎሜትር ርዝማኔ ባለው የጋራ ድንበር የተሠማሩት የቻድ ወታደሮች፣ ጸጥታ ለማስከበር በሚል ፈሊጥ ወደ ማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፓብሊክ ግዛት ዘልቀው እንደሚገቡ በተባበሩት መንግታት የቀድሞው የማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፓብሊክ አምባሳደር፣ አሼክ ኢብን ዑመር ገልጸዋል። ቻድ፤ለማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፓብሊክ ውዝግብ መፍትኄ ፍለጋ ፣ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃው ም/ቤት ውሳኔ ተፈላጊ አይደለም በማለት መቃወሟም የታወቀ ነው። ስለምክንያቷ ሄልጋ ዲኮቭ እንዲህ ይላሉ።

«የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃው ም/ቤት ፣ ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዳይልክ የተቃወመች ሀገር ናት ። ውዝግቡ በራሳቸው በአፍሪቃውያን ይፈታል ነው የምትለው።»

ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ደቢ፣ ጦራቸውን አጠናክረው ለመገኘት ነው ሰፊ ጥረት የሚያደርጉት። አገራቸውን ጠንካራና የተረጋጋች እንደሆነችም ማሳየት ይሻሉ ። ይሁንና የታመቀ ችግር መኖሩን የሚጠቁሙ ሁኔታዎች አልታጡም። በድቡባዊው ወሰን ጦር ያከማቹት ፤

ከዚህ ቀደም በዳርፉሩ ውዝግብ ወቅት፤ ከሱዳን የተንደረደሩ አማጽያን ሥጋት ላይ ጥለዋቸው እንደነበረ የሚታወቅ ሲሆን፤ አሁንም እንጃሜናን የሚቃወሙ ወገኖች፤ ከማዕለላዊት አፍሪቃ ሪፓብሊክ ድንበር በኩል ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ የሚል ሥጋትም ሆነ ጥርጣሬ አላቸው። ሌላ ተጨማሪ ምክንያትም አላቸው። ሄልጋ ዲኮቭ፣

«ሌላው ዐቢይ ምክንያት፤ የቻድ የነዳጅ ዘይት ምንጮች በደቡባዊው የአገሪቱ ከፊል የሚገኙ መሆናቸው ነው። ማንኛውም በዚያ የድንበር አካባቢ የሚከሠት የፀጥታ መደፍረስ፤ የቻድን ነዳጅ ዘይት የማውጣት ተግባር ሊያሠናክል ይችላል።»

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic